NEWS

ሳውዲ ህግ እና ስርአት በሚተላለፉ ግለሠቦች ላይ የሚጣልባቸውን ቅጣት ይፋ አደረገች

By Admin

August 03, 2017

የሳውዲ አረቢያ መንግስት የምህረት አዋጁ ከተጠናቀቀ በኋላ ህግ እና ስርአቱን በሚተላለፉ ግለሠቦች ላይ የሚጣልባቸውን ቅጣት ይፋ አደረገ፡፡

በቅጣቱ ሀገሪቱን ለመልቀቅ የመውጫ ቪዛ ከወሠዱ በኋላ ሳይጓዙ ለቀሩ ዜጎች የ15ሺ ሪያል ቅጣት፣ ከአሠሪ ውጭ ለግል ጥቅም ሌላ ቦታ ሲሠራ የተገኘ ግለሠብ የ1ዐሺ ሪያል ቅጣት እንዲሁም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ሲገባ የተገኘ ግለሠብ የ15ሺ ሪያል ቅጣት እና የ1 ወር እስራት የሚጣልበት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዳቸው ተይዘው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሡ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ ግለሠቦችን ሲያጓጉዝ እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ ሲያግዝ የተገኘ ግለሠብ የ25ሺ ሪያል ቅጣት እና የ6 ወር እስራት እንደሚጠብቀው የተገለፀ ሲሆን ለመጓጓዣ የተጠቀመበት መኪናም በመንግስት ውርስ እንዲሆን ክስ ይቀርብበታል፡፡

የመውጫ ቪዛ የተሠጠው ግለሠብ ቪዛው በመቃጠሉ ምክንያት ያልተጓዘ መሆኑን ሪፖርት ያላደረገ 15ሺ ሪያል ቅጣት እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነ ወደሀገሩ እንዲመለስ ይደረጋል፡፡

የሀጂ እና ዑምራ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለስርአቱ የመጣው ግለሰብ ወደሀገሩ በወቅቱ ሳይመለስ መቅረቱን ለሚመለከተው አካል ያላሳወቀ ከሆነ የ25ሺ ሪያል ቅጣት እንደሚጠብቀው ተቀምጧል፡፡

በእነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ህግን ተላልፈው በተገኙ ግለሰቦች እንዲሁም ድርጅቶች ጊዜው እየጨመረ በመጣ ቁጥር ቅጣቱም እንደሚከብድ በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያደረሠን መረጃ ያሳያል፡፡

ጉዳይ አስመልክተው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚንስትሩ አማካሪ አምባሳደር ሙሃሙድ ድሪርን በኢቢሲ ስቲድዮ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።