Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቆም ብሎ ላሰበው! ግብር ማለት ከቀኝ  ወደ ግራ ኪስ…

0 602

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቆም ብሎ ላሰበው! ግብር ማለት ከቀኝ  ወደ ግራ ኪስ…

አባ መላኩ

ሰሞኑን በቀን ገቢ ግምት   አንዳንድ  ቅሬታዎች  አድምጠናል፣ ተመልክተናልም። እውነተኛ ቅሬታ አይኖርም ብዬ መከራከር አልፈልግም። የተበደሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በርካቶች  ደግሞ ሌላውን ከለላ አድርገው የማይገባ ጥቅም ሲሹ ተመልክተናል።  የቀን ገቢ ግምት   ከስያሜው ብንነሳ  “ግምት” ነው።   ሳይንሳዊ  ግምት በራሱ  ለዕውነታ ይቃረባል እንጂ  ሁሌም ትክክለኛና ተጨባጭ  ሊሆን አይችልም።  መንግስትም ይህን የቀን ገቢ ግምት  ሲጥል  በቂ ጥናት አካሂዷል ባይባልም በዳበሳ እንዳላካሄደው ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በመሆኑም ይህ ግምት  መቶ በመቶ ትክክለኛ ይሆናል ባይልም  ተቀራራቢ እንደሚሆን  ግን መናገር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።   

በአገራችን ባለው ሁኔታ  የመንግስት ተቀጣሪው ወይም ሰራተኛው  ከሚያገኘው ውሱን ክፍያ ላይ  ተገቢውን ግብር በመክፈል በመንግስት ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡ በራሱ  ተመስክሮለታል።  በርካታ ነጋዴዎች  የመንግስት ሰራተኛ ገቢ  ምን አላት ሲሉ ይደመጣሉ።  አንድ የመንግስት ተቀጣሪ  የሆነ  ወዳጄ ያጫወተኝን ላካፍላችሁ። ነገሩ እንዲህ ነው። ወዳጄ አባቱ  የመርካቶ  ነጋዴ ናቸው። እኚህ ሰው ታዲያ  ቢያንስ የሚጓጓዙበት  የቤት መኪና እና መኖሪያ  ቤት አላቸው። ይሁንና እኚህ ሰው የመንግስት ተቀጣሪ  ከሆነውና   የስምንት ሺህ ብር የወር ደሞዝተኛው  ልጃቸው  ያህልን እንኳን  ግብር ሲከፍሉ እንዳልነበር ወዳጄ አጫውቶኛል። ይህ ወዳጄ ከአባቱ ድጎማ እንደሚደረግለት ጭምር አጫውቶኛል።  

እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  በአሁኑ ወቅት በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ   የደረጃ  “ሐ” ግብር ከፋዮች ቢሆኑ  እንኳን   ደህና ተከፋይ ከሚባሉ  የመንግስት ሰራተኛ  የተሻለ ገቢ የላቸውምን? የተሻለ ኑሮ ደረጃ ላይ አይደሉምን? በዚህ የነጻ የገበያ ስርዓት  የተሻለ ተጠቃሚ አይደሉምን?  ለዚህ ጥያቄ ምላሽ  መፈለግ የዋህነት ይመስለኛል። በተግባር ተመልክተናል።    እንግዲህ  ፍትሃዊነት  ከዚህ ይጀምራል።  በእርግጥ  በርካታ ነጋዴዎች  የተጣለባቸውን ግብር በታማኝነትና  በወቅቱ በአገር ወዳድ ስሜት  በመክፈል እነሱም ተጠቅመው አገርን እየጠቀሙ እንዳሉ  በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በግልባጩ ደግሞ በሚሊዮኖች  ካፒታል እየተንቀሳቀሰ የንግድ ፍቃድ የሌለው እንዳለም ተመልክተናል።   

ግብር መክፈል  ግዴታ ብቻ ሳይሆን  ብሄራዊ ኩራትም ነው። የመንግስት ገቢዎች እኮ እኛው ዜጎቹ ነን። መንግስት አገር የሚጠብቀው፣ ልማት የሚያመጣው፣ ዴሞክራሲን የሚያረጋግጠው፣ ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል የሚያስፍነው በሚሰበስበው ግብር ነው።   ግብር የምንከፍለው ሰላምን ላሰፈነ፣ ልማትን ላረጋገጠ፣ ውሃና መብራት፣ መንገድና  ባቡር ለሰራ መንግስት ነው።  ግብር መክፈል የሰላማችን ዋስትና  የጋራ መገልገያዎቻችን ሁሉ ምንጭ መሆኑን ተገንዝበን ተገቢውን ግብር በወቅቱ በመክፈል የአገራችንን ልማት ማፋጠን ይኖርብናል። መንግስት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ከእኛ የሚሰበስበውን ገንዘብ  በሌላ መልኩ ለእኛው የሚሰጥበት ስርዓት ግብር  ነው። በመሆኑም ለመንግስት  ያልሰጠነውን  ነገር እንዲመልስልን  መሻት ተገቢ አይደለም።        

አሁን በተካሄደው የቀን ገቢ ግብር ግመታ ወቅት የተከሰቱ አንዳንድ  የተዛነፉ ነገሮች የሉም ማለት ባይቻልም፤  በበርካታ ነጋዴዎች በኩልም  ያልተገቡ ተግባራትን ተመልክተናል፤ ሰምተናል። የቀን ገቢ ግብርን ለማሳነስ ወይም ከነጭራሹ ግብር ላለመክፈል ሲባል በአንዳንድ ግለሰቦች ከፈጸሟቸው    ተግባራት መካከል  ለአብነት እቃ ማሸሽ፣  በስራ ቦታ አለመገኘት፣ ህጻናትን ወይም እንግዳን ሰው በስራ ቦታ በማስቀመጥ ገማቹ ኮሚቴ  ተገቢ መረጃ እንዳያገኝ  አድርገዋል።  

እቃ  ማሸሽን በተመለከተ አንድ  እውነታን ላካፍላችሁ።   በበእኛ ሰፈር አንድ ሁለት ተካፋች  መስኮት  ሞቅ ደመቅ ያለ  ሱቅ አለ።  ነገሩ ሱቅ ይባል እንጂ ለበርካቶቻችን ከሱፐር ማርኬትም የተሻለ ነው። በቀድሞው ጊዜ በዚህ ሱቅ የለም የሚባል ነገር አልነበረም። እንኳን ሱቁ በረንዳው ሁሉ በተለያዩ  ሸቀጣ ሸቀጦች  የተሞላና   ሁለት ወንድም አማቾች  በመተጋገዝ  የሚሸጡበት፣ ገበያው እጅግ የደራ  ሱቅ  ነው።  ይህ ሱቅ  አጠቃላይ  ሰፈረተኛው  ያሻውን እቃ   በፈለገበት  ጊዜ የሚሸመትበት፣  በዚህ ሱቅ የለም  የሚባል እቃ  ካለመኖሩም  ባሻገር  ዋጋውም በአንጻራዊነት  የተሻለ ነው።  

ታዲያ ይህ ሱቅ አንድ ሰሞን   ወና ሆነ። ያ በሸቀጣ ሸቀጥ የተሞላ ሱቅ መደርደሪያው ብቻ አገጠጠ፣ በረንዳው ያአላፊ አግዳሚው ዝናብ መጠለያ፣ ለውሾች ማንጎላጃ ሆነ።  በእውነት  በርካታ ደንበኞች ግራ ተጋባን። የምንፈልገውን ነገር ባሻን ጊዜ ስንሸምትበት የነበረ ሱቅ  በአጭር ጊዜ ባዶውን ሲቀር እንዴት ግራ አንጋባ።   የብዙዎቻችን  ግምት የነበረው  ከስረው አሊያም  ስራ ሊቀይሩ  ነው እያልን ራሳችንን ስንጠይቅ ነበር።  ነገሩ ለካ ወዲህ ነው።  የቀን ገቢ ግምት  ሰጪዎች ይመጣሉ ሲባል   እቃ ማሸሻቸው ነበር።  እንዲህ ያለ የወረደ ተግባር  የሚፈጽሙ የአገርና የህዝብ ወገንተኝነት የማይሰማቸው ስግብግብ ነጋዴዎችም እንዳሉ ተመልክተናል።    

መንግስት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ሁሉ ብቸኛው ገቢው ግብር ነው። በመሆኑም  መንግስት  ፍተሃዊ የግብር አከፋፈል እንዲኖር ከማድረግ  ጎን ለጎን የግብር ከፋዮችን ቁጥር ማስፋት የሚያስችል ስራዎችን መስራት ይኖርበታለ።  ዘንድሮ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ብቻ ከዘጠና ሺህ  በላይ  አዳዲስ ግብር ከፋዮች ወደ  ግብር ሰንሰለቱ ማስገባት መቻሉ  መልካም ነገር ነው።  ነጋዴዎች በበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑት የአገሪቱ ዕድገት ሲፋጠንና ዘላቂ ሰላም ሲሰፍን  በመሆኑ  መንግስት  መሰረተ ልማት እንዲያሟላ ድጋፍ ልናደርግለት ይገባል። ለንግዱ ማህበረሰብ የመብራት መቆራረጥ አንዱና ትልቁ ችግር ነው። ይህ ችግር  መፍትሄ የሚያገኘው መንግስት የጀመራቸው ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ብቻ ነው።

መንግስት ህጋዊ የንግድ ስርዓትን ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት በንግዱ ማህበረሰብ መካከል ተወዳዳሪነትን  ያጎለብታል።  ግብርን በታማኝነት መክፈል  አገራዊና ህዝባዊ ግዴታ መወጣት ከማስቻሉም  ባሻገር  አገራዊ ፍቅር  የሚገለጽበት ተግባር  ነው።   አገር ወዳድ ዜጋ  የአገርንና የህዝብ ጥቅም አይሰውርም።  መንግስት የተሻለ አገልግሎት እንዲያቀርብ  ሁላችንም የተጣለብንን ግብር በታማኝነትና በወቅቱ  መክፈል ስንችል ብቻ ነው።  መንግስት የተሟላ  አገልግሎት  እንዲያቀርብ፣ ዘለቄታ ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲፋጠን፣ ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ሁላችንም ግብርን  በተገቢው ሁኔታ መክፈል ይኖርብናል። እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  ሁላችንም በመሰረተ ልማት ተጠቃሚዎች ብንሆንም  ከመንግስት ተቀጣሪው ይልቅ  ሌላው አካል የተሻለ ተገልጋይ አይደለምን?

በቀን ገቢ ትመና የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በውይይትና በመግባባት  የሚፈቱ ናቸው። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት መንግስት ያካሄደው  የቀን ገቢ  ግብር  በቂ ነው ተብሎ  ባይወሰድም በጥናት ላይ የተመሰረተ ግምት ነው።  በእርግጥ ግምት  የራሱ እጥረት አይኖረውም አይባልም። በዚህ የቀን ገቢ ግምት የተጎዱ አካላት መኖራቸውን መንግስት ራሱ  አምኖ ነገሮች እንደገና  በማየት  ለበርካቶች  እንዲሻሻልላቸው አድርጓል። በመሆኑም   ማንም ቅሬታ ያለው አካል ቅሬታውን በተገቢው መንግድ በማቅረብ መፍትሄ ማግኘት ይኖርበታል።  አንዳንዶች  አግባባዊ ያልሆኑ ቅሬታዎችን በማቅረብ የሌሎች ትክክለኛ ቅሬታ እንዳይስተናገዱ በገማቾች ላይ የስራ ጫና ሲፈጥሩ ተመልክተናል።  ይህ አይነት አካሄድ  ስግብግብነት ነው።  ራቅ አድርጎ ላሰበው  እውነትም ግብር ከቀኝ ኪስ ወጥቶ ግራ ኪስ እንደመክተት ነው።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy