Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በመሞት ላይ ያለ አመለካካት አራማጆች ህልም

0 340

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በመሞት ላይ ያለ አመለካካት አራማጆች ህልም

ኢብሳ ነመራ

እያንዳንዱ ዘመን የሶስት ትውልድ አመለካከቶች ህልውናቸውን ለማስጠበቅ የሚፋለሙበት መድረክ ነው። እነዚህም አሁን ያለው ገዢ አመለካካት፣ ያለፈውና በመሞት ላይ የሚገኘው አመለካካት እንዲሁም ልወለድ የሚለው የመጪው ዘመን አመለካከቶች የሚፋለሙበት መድረክ ነው። የማህበረሰብ እድገት በተለየ አጋጣሚ ለተወሰነ ጊዜ ሊገታ ወይም ሊጓተት የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩ ባይካድም፣ ዋናው አቅጣጫው ግን በጊዜ ጎዳና ላይ አሮጌውን እየለወጠ ወደፊት የሚዘልቅ ነው። የማህበረሰብ እድገት ታሪክ ወደኋላ አይመለስም፤ ወይም አይቀለበስም።

በዚህ ጉዞ ውስጥ አሮጌው በቀላሉ አይሞትም፣ መጪውም በቀላሉ አይወለድም። አሮጌው፣ የአመለካከቱ ባለቤት የሆነው ትውልድ ከጠፋም በኋላ በርዝራዦች ውስጥ ቀርቶ ብዙ ይንፈራገጣል። የዘመኑን ገዢ አመለካካት ለመቀልበስ፣ መጪው እንዳይወለድ ለማጨናገፍ ይፋለማል። መጪውም በዘመኑ ገዢ የሆነው አመለካካት ውስጥ ይፈጠርና ፈልቅቆ ለመውጣትና የገዢነቱን ስፍራ ለመረከብ ይታገላል። የዘመኑ ገዢ አመለካከትም ስፍራውን ለማስጠበቅ በመሞት ላይ ያለውን አሮጌውንና በመለለድ ላይ ያለውን አዲሱን አመለካከት ይፈለማል።

ይህን የአመለካከቶች ፍልሚያ ተጨባጭ አስረጂ እየጠቀስን እንመልከት። ለምሳሌ በበለጸገችውና የአመለካካት ነጻነት መከበር ናሙና ተደርጋ በምትወሰደው አሜሪካ አሁንም የነጭ የበላይነት፣ የባሪያ አሳዳሪ ስርአት አመለካካት አራማጆች አሉ። በአውሮፓም እንዲሁ የኒዮናዜ አመለካካት አራማጆች አሉ። በሌላ በኩል አሁን ገዢ የሆነው ገበያ አክራሪ ሊበራል አመለካካት አለ። ከዚህ ገበያ አክራሪ አመለካከት ውስጥ ለመውጣት የሚታገል አዲስ አመለካከትም አለ። ይህ የሊበራል ዴሞክራሲን ጫና ፈልቅቆ ለመውጣት የሚታገለ የመጪ ዘመን አመለካከት አልፎ አልፎ ባልተደራጀም መልክ ቢሆን ሊበራል ዴሞክራሲ የፈጠረውን 90 በመቶ የሃገሪቱ ሃብት 1 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች የተቆጣጣሩበትን የፋይናንሻል ኦሊጋርኪ አምባገነናዊነት (dictatorship of the financial oligarchy) በአደባባይ በመቃወም ብቅ ሲል ይስተዋላል። ይህ የመጪው ዘመን አመለካካት ነው። በተለይ ወቅት እየጠበቀ የሚመጣው የኢኮኖሚ ቀውስ ሲያጋጥም በመጪውና በዘመኑ ገዢ አመለካከቶች መሃከል ያለው ፍልሚያ ጎልቶ ይታያል።

ወደሃገራችን ኢትዮጵያ እንመለስ። አሁን ያለው ገዢ አመለካከት የዘመናት የህዝብ ብሶት የነበረውን የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ፣ የሃይማኖትና የአመለካካት ብዝሃነትን ለሚያስተናግድ የእኩልነት ስርአት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ነው። ከዚሁ ጋር የዘመናት ድህነት የፈጠረውን አስከፊ ህይወት የመቀየር የመልማት ፍላጎት የወለደው አመለካከት አለ። ልማትና ዴሞክራሲ የሚጠይቋቸው የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም የዘመኑን ገዢ አመለካካት ከገነቡት ዋልታና ካስማዎች መሃከል ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ አሮጌውና በመሞት ላይ ያለው አመለካካትም ህልውናውን ለማቆየት እየተፍጨረጨረ ይገኛል። ይህም የአንድ ብሄራዊ ማንነትና ሃይማኖት የበላይነትን የሚሰብክ የአሃዳዊ ስርአት አመለካካት ነው። ይህ አመለካካት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አመለካካትን ሃገር አፍራሽ፣ ታሪክ አጥፊ፣ ልዩነትን የሚያሰፋ፣ የእርስ በርስ ግጭት የሚያስከትል ወዘተ እያለ በማጥላላት ራሱን ለማክረም እየተፍጨረጨረ ይገኛል። ይህ አሮጌ አመለካካት የፊውዳል ነገስታትን በማወደስ በይፋ ሲገለጽ ይስተዋላል።

በኢትዮጵያ ከዚህ የተለየ ሌላም አሮጌ አመለካካት አለ። ይህ የአሃዳዊ ስርአት ትምክህታዊ አመለካካት የወለደው የጠባብ ብሄረተኝነት አመለካካት ነው። ይህም የጋራ ነገሮችን በሙሉ በመጠየፍ እንዲሁም የመገንጠልን አጀንዳ በማራመድ አሁን ያለውን ገዢ አመለካካትና እንዲወለድ ያስገደደውን ከጎኑ ያለውን አሃዳዊ ስርአት እይተፋለመ ይገኛል። እነዚህ ሁለት ተቃራኒ አመለካካቶች በዋናነት በየራሳቸው የዘመኑን ገዢ አመለካካት ስለሚፋለሙ ሳያስቡት የጋራ ግብ ያላቸው መስለው የሚቀርቡባቸው አጋጣሚዎች አሉ። በመሃከላቸው ያለውን ሁለት ጽንፍ ላይ የረገጠ የማይታረቅ ቅራኔ እንደተሸከሙ ግንባር ስለመመስረት የሚያወሩት በዚህ አጋጣሚ ነው። ግንባር የመመስረታቸው ጉዳይ ግን በመርህ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ግብታዊ ነው። እናም የትም አይደርስም።

በሌላ በኩል በበጀትም በፖለቲካ ስልጣንም አሁን ካለው የበለጠ ራስገዝ (outonemes) የመሆን አቅም ያላቸው የክልል መንግስታት እንዲኖሩ፣ ራስገዞቹ ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲኖራቸውና ይህን ግንኙነት የሚመጥን ፖለቲካዊ ትስስር እንዲኖር የማድረግ ፈላጎት ላይ የተመሰረተ የመጪ ዘመን አመለካካት ተፈጠሯል። ይህ የመጪ ዘመን አመለካከት አንድ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ የመመስረት ራዕይ ያለው ነው። የበለጠ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ነጻነት የተረጋገጠበት፣ መንግስት እጁን ሙሉ በሙሉ ያወጣበት ፍጹም የገበያ ፉክክር (perfectly competitive market) የሰፈነበት የኢኮኖሚ ስርአት እንዲኖርም ይሻል። አዲስ የተፈጠረው የመጪ ዘመን አመለካከት። ይህ የመጪው ዘመን አመለካካት ወደ ገዢነት ለመሸጋጋር እየተፋለመ ነው።

አሁን ገዢ በሆነውና በመጪው መሃከል ያለው ግንኙነት የመጠፋፋት ቅራኔ (antagonistic contradiction) ስላልሆነ የጎላ ግብግብ አይታይም። ውስጥውስጡን ግን ፍትጊያ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ በአሮጌውና አሁን ባለው ገዢ አመለካካት መሃከል ያለው ፍልሚያ የሞት ሽረት ግብግብ ነው። ፍልሚያው የሞት ሽረት ግብግብ የሆነው አሁን ያለው ገዢ አመለካካት፣ በአመለካካቶች ፍትጊያ በአዝጋሚ ለውጥ የወጣ ከመሆን ይልቅ፣ በርቅሶ በአብዮት መልክ ስፍራውን በመያዙ የመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ፣ በየዘመኑ የነበሩና ያሉ የአመለካካቶች ፍልሚያ ጉዳይ በአንድ የጋዜጣ ጽሁፍ የሚሸፈን ባለመሆኑ፣ ለተነሳሁበት ጉዳይ መንደርደሪያ ያህል ይህን ያህል ብዬ  ወደጉዳዬ ለመለስ።

ጉዳዬን ማረፊያ ላብጅለት ብዬ እንጂ ዋናው ጉዳዬ በቅርቡ በአሜሪካ የተሰባሰቡ ጥቂት ግለሰቦችን የያዙ ቡድኖች አንስተውት የበረው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ምስረታ ወሬን የሚመለከት ነው። የሽግግር መንግስት ለመመስረት በሂደት ላይ ነን ያሉት ቡድኖች በቀድሞው የኦነግ አመራሮች የተመሰረተው የኦሮሞ ዴሞክራሲ ግንባር፣ በተስፋ ለአሃዳዊ ስርአት ርዝራዦች የተመሰረተው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ በህዝብ ድምጽ የተገኘን ስልጣን ትተው በሃይል ስልጣን ለመመስረት ከሃገር በኮበለሉ ግለሰቦች የተደራጀው ግንቦት 7፣ በኢሰፓ ቅሪቶች የተፈጠረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦቸ ህብረት (የከፋ ጠቅላይ ግዛት ቡድን) ወዘተ ናቸው።

እነዚህ ቡድኖች ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ የተሰኘ ጥምረት መመስረታቸውን ነግረውናል። ሰሞኑን ማለትም ሃምሌ 29፣ 2009 ዓ/ም  መስራች ጉባኤ አካሂደናል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ የተሰኘው ጥምረት አመራሮች የጥምረቱ ዓላማ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት መመሰረት የሚቻልበትን ሁኔታ ማጥናት መሆኑን ተናግረዋል። የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ያነጋጋረቻው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክትል ሊቀመነበርና የጥምረቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሊቀመነበር ዶ/ር ዲማ ነገዎ፣ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ የተሰኘውን ቡድን ዓላማ ሲገልጹ፣ የሽግግር ስርአቱ ምን ሊመስል ይችላል፣ እንዴት ነው የሚዋቀረው፣ ተሳታፊዎቹ እንዴት ይሆናሉ የሚለውን ጥናት እያደረገ ነው፣ በግድ ወይም በውድ የሽግግር መንግስት መመስረት ያስፈልጋል ብለዋል።

የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እነደሚነግረን አሁን የሽግግር መንግስት ስለለመስረት የሚነግሩን ዲማ ነገዎ፣ በ1983 የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን በመምራት የሽግግር መንግስት ከመሰረቱት መሃከል አንዱ ናቸው። ዲማ ነገዎ የሽግግር መንግስቱ ውስጥ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሆነው ለወራት አገልግለዋል። በዚህ የሽግግር መንግስት ውስጥ ዲማ ነገዎ ሲመሩት የነበረው ኦነግ፣ የሽግግር መንግስቱ ምክር ቤት ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩ ሁሉም ፓርቲዎች የበለጠ መቀመጫ ነበረው። ይህ የሆነው ህዝብ ድምጽ ሰጥቶት አልነበረም። ኦነግ እወክለዋለሁ የሚለው የኦሮሞ ህዝብ ሰፊ በመሆኑ ያገኘው ነበር።

ኦነግ በዚህ የሽግግር መንግስት ውስጥ፣ የሽግግር መንግስቱ እንደህገመንግስት ሲጠቀምበት በነበረው ቻርተር በተረጋጋጠው የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መሰረት የኦሮሞ ህዝብ የሚኖርበትን አካባቢ (ኦሮሚያን) ከሌሎች የኦሮሞ ህዝብ ድርጅቶች ጋር በመሆን የማስተዳደር ስልጣን አግኝቶ ነበር። ኦነግ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ እያስተዳዳረ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በምትባለው ምድር ውስጥ የሚኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን እጣ ፈንታ የሚወስነውን ህገመንግስት የመቅረጽ እድልም በእጁ ገብቶ ነበር።

አሁን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተሰኘ አዲስ ፓርቲ መስርተው የሽግግር መንግስት ስለመመሰረት የሚያወሩልን ዲማ ነገዎ ግን ፓርቲያቸው በሽግግር መንግስት ውስጥ እወክለዋለሁ ያለውን ህዝብ እያስተዳደረ መጪ እጣ ፈንታውን የሚወስንበትን ህገመንግስት እንዲቀርጽ ማድረግን አልፈቀዱም። ኦነግን እንደድርጅት በፕሮግራምና እቅድ መምራት ባለመቻል በየአካባቢው ጀብደኛ ጠባብ ብሄረተኞች ህዝቡ ላይ በተለይ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ ዘግናኝ እርምጃ በመወሰድ ታሪካዊ ስህተት እንዲፈጸም አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ኦነግ የመገንጠል አጀንዳ ላይ ተቸንክሮ የሽግግር መንግስቱ ቻርተር በሚፈቅደው መሰረት ወይም በሽግግር መንግስቱ ወቅት በሚቀረጸው ህገመንግስት የኦሮሞ ህዝብ እጣ ፈንታ እንዲወሰን ከማድረግ ይልቅ፣ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ መሆኑን በማያረጋግጥ ሁኔታ ኦሮሚያን በሃይል የመገንጠል አካሄድ ማራመድን መረጠ።

በመጨረሻም ዓላማውን በሃይል ለማሳካት በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮችና የሌሎች አመለካካት አራማጆች የተዋቀረው የሽግግር መንግስት ላይ ጦርነት አወጀ። ጦርነት ያወጀው በይፋ ነበር። አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ ጠርቶ፣ በወቅቱ ሊቀመንበሩ በነበሩት ኦቦ ጋላሳ ዲልቦ ባደረጉት ንግግር ነበር የጦርነቱ ከተት የታወጀው። ይህን ተከትሎ አመራሮቹ፣ ዲማ ነገዎን ጨምሮ ጦርነቱን ለመምራት ከአዲስ አበባ ሲወጡ አንድም የነካቸው አልነበረም። ደርግ ሲወድቅ በራሳቸው ፍቃድ እንደመጡት፣ ማንም ሳያሳድዳቸው በራሳቸው ፍቃድ ሹልክ ብለው ወጡ።

በክተት አዋጁ መሰረት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሽግግር መንግስቱ ላይ ጦርነት ቢከፈቱም፣ ጦርነቱ ህዝባዊ ስላልነበረ ማሸነፍ አልቻሉም። ይህን ተከትሎ አመራሮቹ ሃገር ለቀው አሜሪካና አውሮፓ ገቡ። ኦነግም በትናንሽ ቡድኖች ተከፋፍሎ ተበታተነ። የኦነግ መስራችና አንጋፋ የሚባሉት እነዲማ ነገዎም በሰተርጅና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተሰኘ አዲስ ፓርቲ መስርተው እነሆ ድሮ ያለፋቸውን የሽግግር መንግስት ዳግም ስለመመስረት እያወሩ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ በመሞት ላይ ያለን አሮጌ አመለካከት ለማስተናገድ ወደኋላ እንዲመለስ የሚያደርገው አንዳችም ምድራዊ ምክንያት እንደሌለ ማስተዋል አልቻሉም።

የሽግግር መንግስቱን እንመሰርታለን የሚሉት ደግሞ የብሄር መብት ጥያቄን የመስማት ፍላጎት ከሌላቸው የፊውዳል ነገስታትን ገድል እያወሩ አንድ ብሄራዊ ማነነት የነገሰባት አሃዳዊ ሃገር ለመመስረት ከሚያልሙ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከተሰኘ ቡድን ጋር ነው። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለአማራ ህዝብ መብት የሚከራከር ቡድን ሳይሆን፣ የሌሎች ብሄራዊ ማንነት ተጨፍልቆ ስለሚመሰረት አሃዳዊ መንግስት የሚዘምር የትምክህት ቡድን ነው።

አሁን የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን የሚሉት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሁለቱም በተቃራኒ ጽንፍ ላይ የቆመ የማይታረቅ አቋም ያላቸው የአሮጌና በመሞት ላይ ያሉ የትምክህትና የጠባብ ብሄረተኝነት አመለካካቶች አራማጆች ናቸው። እነዚሀ አሮጌ አመለካካቶች ካሁን በኋላ ለምልመው የበላይ የመሆን እድል ባይኖራቸውም፣ ለአንድ ክፍለዘመንና ከዚያም በላይ በጥቂቶች ዘንድ በትዝታ ሊኖሩ ይችላሉ፤ አጋጣሚ ሲገኝ እየተዘመሩ። በአሜሪካ የባሪያ አሳዳሪ ስርአት አመለካከት አራማጆች እስከአሁን እንዳሉት አይነት መሆኑ ነው። የባሪያ አሳዳሪ አመለካካት ክፍለዘመናትን የተሻገረ እድሜ ቢኖረውም፣ ካሁን በኋላ ገዢ አመለካካት ሊሆን ግን አይችልም።

ከ1983 እስከ 1987 ዓ/ም ኢትዮጵያ የተዳደረችበትን የሽግግር መንግስት አሻፈረኝ ብሎ የወጣው የተገንጣዩ ኦነግ አዛውንት አመራሮች የመሰረቱት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የጠባብ ብሄረተኝነት አመለካካትና ጥቂት መቶ ሰዎችን ይዞ በኤርትራ በረሃ የሚባዝነው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የትምክህት አመለካካት፣ እንዲሁም በጭፍን ጥላቻ ላይ ተመስርቶ የኢፌዴሪ ስርአትን ከማፍረስ ያለፈ ምንም ግልጽ የከርሞ ራእይ የሌለው ግንቦት 7 ካሁን በኋላ እየሞቱ እንጂ እየለመለሙ አይሄዱም። የአሮጌና አመለካካት ቅሪቶች ናቸው። በኢትዮጵያ ገዢ መሆን የሚያስችላቸው ስፍራም አቅምም የላቸውም።

የእነዚህ በመሞት ላይ ያሉ አሮጌ አመለካከት አራማጆች ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ባለ ቁጥር ስርአት የፈረሰ ይመስላቸዋል። እነርሱ ያልፈጠሩትን ኮሽታ ባህሪ መገንዘብ ስለማይችሉ፣ እንደሎተሪ እጣ ለእነርሱ የመጣ የስልጣን ሲሳይ ይመስላቸዋል። ይሄኔ ላያቸው ላይ እየወረደ ያለውን የመቃብር አፈር እያራገፉ የሽግግር መንግስት ስለመመስረት፣ ስለጥምረት ማውራት ይጀመራሉ። ኮሽታው የእነርሱን ትንሳኤ ስለማያመጣ ጥቂት ቆይተው መለሰው ያሸልባሉ።

እነዚህ አሮጌ አመለካከቶች ህይወት ዘርተው ገዢ መሆን የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ የሚሄድ ስፍራ ይኖራቸው ነበር። በተጨባጭ የሚታየው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ጥቂት መቶ ሰዎችን ይዘው በኤርትራ ዱር ውስጥ እንዲቀሩ ያደረጋቸው ይህ ነው። የኤርትራ መንግስት ማንቀላፊያ ምሽግ የሰጣቸው ያንሰራራሉ በሚል እምነት ሳይሆን፣ ቢያንስ በሽብር ጥቃት ኢትዮጵያን ያተራምሳሉ በሚል ቀቢጸ ተስፋ ነው።

ማንሰራራት የማይችሉት የኢፌዴሪ መንግስት ስለተጫናቸው አይደለም። አዳጊ አመለካካት በመግስት ሊታፈን አይችልም። ለጥቂት ጊዜ ሊዳፈን የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም አይከስምም። ፈንድቶ የወጣል። በአሜሪካና አውሮፓ፣ በኤረትራ ዱር የሚያንቋርሩ አሮጌ የትምክህትና የጠባብ ብሄረተኝነት አመለካከቶች ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን እየከሰሙ ነው የሄዱት። አልፎ አልፎ ልዩ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ብቻ ነው ቀና ብለው ድምጻቸውን የሚያሰሙት፤ እንዲህ እንደሰሞኑ።

አሁን የሽግግር መንግስት ምስረታ በሚል አፈራቸውን እያራገፉ ቀና ለማለት የሞከሩት ባለፈው ዓመት ህዝብ ያነሳቸውን የልማት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ የልማት ጥያቄዎች ተከትሎ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ነው። ይህን ተቃውሞ የአሮጌ አመለካካት አራማጆቹ አልፈጠሩትም። እርግጥ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል። ስላልፈጠሩት ባህሪውን አያውቁትም፣ እናም መረተው የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ወደሚያስችል ደረጃ ማሸጋጋር አልቻሉም። ተፈጥሯቸውም ይህን ማድረግ አያስችላቸውም። ተቃውሞው የፈጠረው ኮሽታ እንደጎመጁት ሳይሆን ቀርቶ ተረጋገቷል። እነርሱም ኮሽታን ተከትሎ ከሚቀሰቀስ የአንድ ሰሞን የሽግግር መንግስት ምስረታ ወሬ ወጥተው ወደሸለብታቸውና በኤርትራ ዱር ወደመባዘን መመለሳቸው አይቀርም። ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ፣ ዴሞክራሲና ሰላም የሰፈነባት የበለጸገች ሃገር መሆን የምትችለው በመጪው ተራማጅ አመለካከት እንጂ በአሮጌዎቹ የትምክህትና የጠባብ ብሄረተኝነት አመለካከቶች አይደለም።

በአጠቃላይ ሰሞኑን ከወደአሜሪካ የሰማነው የሽግግር መንግስት መስረታ ጉዳይ የአሮጌና በመሞት ላይ ያሉ አመለካከቶች አራማጆች ሊቆም፣ ሊጨበጥ፣ ሊፋፋ የማይችል ህልም ነው።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy