በሠላም መቀለድ አይቻልም!
በሠላም መቀለድ አይቻልም!
ታከለ አለሙ
የሀገርና የስልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ሀገራችን ከድሕነት ለመውጣት ባካሄደችው ትግል ሰፊ ድሎችና ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡የተሰሩትንም ሆነ የተጀመሩትን ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከዳር ለማድረስ ልማትና የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡በሰላም መቀለድ አይቻልም፡፡
በሕዝቡ ውስጥ ተነስተው የነበሩ የመብቴ ይከበርልኝ የተለያዩ ጥያቄዎች ከመንግስት መልስ እያገኙ ይገኛሉ፡፡በቅርቡ ከግብር ጋር ተያይዞ በሕዝቡ የቀረበውን ቅሬታ በሕዝቡ ውስጥ የብሶት መነሻ በማድረግ የተቀጣጠለ እሳት ለማንደድ ሲሞክሩ የነበሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ያሰቡት አልተሳካላቸውም፡፡አጀንዳ አድርገው ሊያነሱት የሞከሩት ርእስ ከሽፎአል፡፡
በግምት ላይ የተመረኮዘው የግብር ትመና በሕብረተሰቡ ውስጥ ቅሬታ በማስነሳቱ ይህን ጉዳይ መንግሰት በቅርበት ሲከታተለው ቆይቶ ውሳኔ ሰጥቶአል፡፡ዜጎች ግብርን በወቅቱ መክፈል የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን ያውቃሉ፡፡ዘመናዊ የሀገር ግንባታን ለማካሄድ ዋናው ወሳኝ አስተዋጽኦ ሕዝብ ለመንግስት የሚከፍለው ግብር ነው፡፡
ለሀገራዊ የተለያዩ ግንባታዎች ለትምህርት ለጤና ለማሕበራዊ አገልግሎት መስፋፋት ለመንገድ ለድልድዮች ለግድቦች ስራና ልማት ለኮንስትራክሽን ስራዎች ለሰራተኛ ደመወዝ ለብሔራዊ መከላከያና ለፖሊስ ለደሕንነት በጀት ወዘተ አንድ ሀገር ገቢዋን የምትሰበስበው ከሕዝቡ ግብር ነው፡፡አዲስ ነገር የለውም፡፡
በእርግጥ በእኛ ሀገር ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ስርአት የተዘረጋው በቅርብ ግዜ ቢሆንም ዜጎች ይህንን ሀገራዊ ግዴታቸውን በወቅቱና በስርአቱ መወጣት የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን አይዘነጉትም፡፡ ግብር ሲከፍሉም ኖረዋል፡፡ ቅሬታ ሰፈጠር ጥንትም ዛሬም የግብር ቅሬታን የሚሰማና መፍትሄ የሚሰጥ መንግስታዊ አካል ነበረ፡፡አለም፡፡በሕዝቡ የቀረቡትን ግብሩ ከአቅማችን በላይ ነው የሚለውን ቅሬታ መንግሥት ሰምቶአል፡፡ አዳምጦአል፡፡ ችግሩ እንዲፈታም አድርጎአል፡፡
በግምት ግብሩ ላይ ከፍተኛ ማሻሻያ በማድረግ መንግስት ከዜጎቹ የተነሱትን ጥያቄዎች መልሶአል፡፡በተለይ በዚህ የግምት ግብር ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ ያነሳው የታችኛው አነስተኛ ነጋዴ ከመሆኑም አንጻር መንግስት ራሱ ሱቅ ሰርቶ ሰጥቶ እንደአቅማቸው እንዲሰሩ ስራ የፈጠረላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡በዚህ መልክ መንግስት በመላው ሀገሪቱ ለብዙ መቶ ሺህ ዜጎች አዳዲስ የስራ እድሎችን ከፍቶ ራሳቸውን ችለው ሰርተው እንዲኖሩ ማድረግ ችሎአል፡፡ይህም የስርአቱ ውጤት ነው፡፡
በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ከሚሰሩት ሌላ በግብር ጉዳይ በግምት የሚከፍሉት በትኬት የማይጠቀሙ ናቸው፡፡የግምት ግብር የሚከፍሉትም ለዚህ ነው፡፡የግብር ግመታው ትክክል አይደለም ከአቅማችን በላይ ነው ወቅት መንግስት ችግራቸውንና ያቀረቡትን አቤቱታ አዳምጦአል፡፡ተገቢና ትርጉም ያለው ማስተካከያም እንዲያገኙ አድርጎአል፡፡
ይህ የሕብተረተሰብ ክፍል ስርአቱ በፈጠረው የስራ አድል ተጠቃሚ በመሆን እየሰራና እያደገ ያለ ሲሆን ተደራጅቶ አቅም ገንብቶ ወደተሻለ አደረጃጀት በመቀየር አቅሙን ሊያሳድግ የሚችልም ነው፡፡በስርአቱ ተጠቃሚ የሆነና ስርአቱንም መጠበቅ ያለበት የሕብረተሰብ ክፍል ነው፡፡
በግምት የግብር ትመናው መነሻነት ሕብረተሰቡን ወደ አመጽና ሁከት ለመክተት ሲጥሩ የነበሩት ጽንፈኞች ያልተሳካላቸው ዋናው ምክንያት ሕብረተሰቡ የስራ እድሉን አመቻችቶ የፈጠረለት መንግስት መሆኑን እንደገናም ችግር አለ በሚልበት ሰአት መንግስት ችግሩን አዳምጦ መፍትሄ እንደሚሰጥ ስለሚያውቅ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ጉዳዩ የአመጽ መቀስቀሻ የሚሆንበት እድል ተዘግቶአል፡፡በሌሎችም አካባቢዎች የተስተካከለ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ቀድሞ በነበረው እንዲከፍሉ የተደረገበትም ሁኔታ አለ፡፡የግብሩ ዋና አላማ ዜጎች ሰርተው አግኝተው ካገኙትም ላይ መልሶ ለሀገር ግንባታና ጥቅም በብዙ መልኩ የሚውል የበኩላቸውን ግብር መክፈል ግዴታ እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡
እየሰሩ እያገኙ ግብር ለመንግስት አለመክፈል ግብርን መደበቅና ማጭበርበር ዞሮ የሚጎዳው ሀገርንና ሕዝብን ነው፡በዚህ መልኩ አየር በአየር እየነገዱ በመደበኛ ሁኔታ በሕግ ተመዝግቦ እየሰራ ግብር የሚከፍለውን ነጋዴ ስራ እየነጠቁ በሕገወጥነት የሚሰሩ የሚከብሩ እንዳሉ መንግስት በበቂ ሁኔታ ያውቃል፡፡እርምጃም ወስዶአል፡፡
ግብር መክፈል የዜግነት ሀገራዊ ግዴታ ነው፡፡ከአሁን በኃላም ከሕብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት እነዚህ ክፍሎች በሕጋዊ መስመሩ እንዲገቡ ይህ ካልሆነ በሕግ እንዲጠየቁ የማድረጉን ስራ አጠናከሮ ይቀጥላል፡፡ትልቁ ነጥብ ጽንፈኛውና አክራሪው የተቃውሞ ኃይል የግብርን ጉዳይ የመቀስቀሻ መሳሪያ አድርጎ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት የሄደበት መንገድ መክኖአል፡፡
በዚህም ሳያበቃ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከተነሳ በኃላ በአንዳንድ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት፤ የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ፤ የንግዱ ማሕበረሰብ ሱቁን እንዲዘጋ፤ መኪኖች እንዳይተላለፉ ለማድረግ ቢሞክሩም ይህም በሕዝቡ ከሽፎአል፡፡በሕብረተሰቡ ወሳኝ ትግል እየመከነ ይገኛል፡፡ከዚህ በኃላ በነጀዋር መሀመድ ቅሰቀሳ የሚታለል በስሜት የሚነሳ ወጣት የለም፡፡የሶሻል ሚዲያዎቻቸው ሰለባ በመሆን ለጥፋት የሚሰለፍ ዜጋም አይኖርም፡፡
የአክራሪዎቹና የጽንፈኞቹ ተላላኪዎች በውጭ ሀይሎች ሴራና ግፊት በገንዘብ ኃይልም በመገፋት የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ የሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ የሚመከተው በሕዝቡ በመሆኑ ነው ሕዝቡ ሴራቸውን እያከሸፈ ያለው፡፡የሀገሩ ጠባቂና ባለቤት የሰላሙም አስተማማኝ ዋስትና ሕዝብና ሕዝብ ብቻ ነው፡፡
ሀገራችን በብዙ መስኮች ከፍተኛ ልማትና የእድገት ስኬቶችን እያስመዘገበች በግስጋሴ ላይ ትገኛለች፡፡ይህንን ፈጣን ግስጋሴ ለማሰናከል ተኝተው የማያድሩ የውጭና የውስጥ ኃይሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡የግብጽን የኤርትራን ስውር እጆች በመጠቀም በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግዱ ክፍሎች የሀገሪቱን ሰላም ለማናጋት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ይታወቃል፡፡
ባሕር ማዶ ሁነው የውጭ ጽንፈኛ ኃይሎች በሚነዙት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የተነሳ በተደጋጋሚ ባደረጉዋቸው አመጽ የማነሳሳት ሙከራዎች ምን ያህል የሰው ሕይወት እንደጠፋ የሀገርና የሕዝብ ንብረ እንደወደመ ሕዝባችን በተደጋጋሚ አይቶታል፡፡የማይቀበላቸው መሆኑን ሊያውቁት ይገባቸዋል፡፡የሀገርና የሕዝብ ሰላም ለድርድርና ለወይይት የሚቀርብ አጀንዳ አይደለም፡፡ሆኖም ተደርጎም አያውቅም፡፡በግብጽና በኳታር ብር አይለወጥም፡፡
የሻእቢያና የግብጽ ቅጥረኞች ለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ለሕዝቡም መብት የመቆምም ሆነ የመከራከር የሞራል ብቃቱ የላቸውም፡፡በመጀመሪያ ደረጃ ጸረ ኢትዮጵያዊነታቸውን አይደለም ኢትዮጵያውያን ይቅርና በአለም ደረጃ ይታወቃል፡፡ትልቁ አጀንዳቸው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሰናከል ማድረግ ነው፡፡ይህ ደግሞ አይታሰብም፡፡
የሕዝቡ ሀገራዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ስራው በፍጥነት በመሄድ ላይ ያለ ሲሆን ለአፍታ የሚቆምበት እድል የለም፡፡አይኖርምም፡፡ከዚህ ሌላ ሀገራችን የደረሰችበት የልማትና የእድገት ማማ በአሕጉሩም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጀ ያገኘችው ተቀባይነት በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ተጽእኖ ፈጣሪና ልእለ ኃያል እየሆነች መምጣትዋ የጠላቶችዋን ሴራ አሳድጎታል፡፡
የቱንም ያህል ቢያሴሩ ኢትዮጵያን ማንበርከክ አይቻላቸውም፡፡ይህን እውነት እነሱም ያውቁታል፡፡እኛም እናውቀዋለን፡፡ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የአረብ ሀገራት በአመጽና በግርግር የምትፈርስ ሀገር አይደለችም፡፡ይልቁንም በኃያልነትና በድል አድራጊነት የጀመረችውን ታሪካዊ የእድገትና የሕዳሴ ጉዞ በብቃት ታሳካለች፡፡
ማጠቃለያ
በውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች እርጥባን የሚረዳው አክራሪውና ጽንፈኛው የተቃዋሚ ስብስብ የሀገሪቱን ሰላም ለመደፍረስ ደፋ ቀና እያለ ይገኛል፡፡እነጀዋር መሐመድ ከኩዌትና ከግብጽ በተሰበሰቡት ገንዘብ በሶሻል ሚዲያ በሚያካሂዱት ተራ ቅስቀሳ የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ አይችሉም፡፡ወጣቱ ከትላንት ስህተቱ የተማረ በመሆኑ ለእነሱ እሳት ማቀጣጠያነት በመሳሪያነት አይሰለፍም፡፡በእብደትና በጀብደኝነት በጦዘው የአክራሪዎች ፖለቲካ ተገፋፍቶ የሀገሩንና የሕዝቡን ንብረት አያወድምም፡፡ሰላሙን ነቅቶ ይጠብቃል፡፡ በሀገርና በሕዝብ ሰላም መቀለድ አይሞከርም፡፡የሰላሙ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ሰላሙንና መረጋጋቱን ያስጠብቃል፡፡