Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዋጁ ዘላቂ የሆነ ትርፍ አግኝተናል

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዋጁ ዘላቂ የሆነ ትርፍ አግኝተናል

ዮናስ

 

በሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ  ለ10 ወራት በሥራ ላይ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰሞኑን ተነስቷል። በህገ መንግስቱ ድንጋጌ አግባብ ሃገሪቱ ገጥሟት ለነበረው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የተደነገገው አዋጅ እንዲነሳ ያስቻሉ ምክንያቶች በኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት ሃላፊ ተዘርዝረዋል። አዋጁ እንዲነሳ ምክንያት የነበሩ የህዝብ ሚናዎች ወደፊትም ለዚህች ሃገር ሰላም ወሳኝ ናቸውና ስለሃገሪቱ ልማት ወደፊት ከሚያስፈልጉን እሴቶች መካከል የተወሰኑትን ማንሳትና ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።  

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተልዕኮ መሳካት ህብረተሰቡ የጎላ ድርሻ እንደነበረው የሚጠቅሰው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በቀጣይም ህዝቡ የሰላም ባለቤትነት ሚናውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩን መንግስት እንዳረጋገጠ ገልጿል።  እንደኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት ከሆነ፤ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቀሪ ስራዎች አሉ። እነዚህን ቀሪ ስራዎች በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር ከሚቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱ  ከሃገሪቱ ገጽታና የውጭ ኢንቨስትመንታችን ፍሰት አንጻር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መደረጉ ተገቢ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአዋጁን የ10 ወራት አፈፃጸም በመገምገም መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባም።

ሴክሬተሪያቱ በሰጠው ማብራሪያና በውሳኔ አሰጣጥ ቦርድ በተረጋገጠው አግባብ ለአዋጁ መደንገግ መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች መቀልበሳቸውን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች አንዳንድ ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን፣ ከሁሉ በላይ ለአዋጁ ተልዕኮ መሳካት ዓይነተኛ ሚና የተጫወተው ህዝባችን የሰላም ባለቤትነት ሚናውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩን የተመለከተው ማረጋገጫ ነው ጠቃሚያችን እና ልናሰፋው የሚገባን።

አዋጁ ሲደነገግ በዚሁ ምክር ቤት ላይ ተገኝተው ስለተደነገገበት ምክንያት ሲያብራሩ በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝብ ያነሳቸው የነበሩትን ህጋዊና ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጽንፈኛ ኃይሎች የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ ወደ ነውጥና ግርግር በመቀየር ሲያካሂዱት የነበረው አፍራሽ እንቅስቃሴ እጅግ አደገኛና በመደበኛ የጸጥታ ማስከበር ሥራ መግታትና መቆጣጠር አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ መሆኑን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። ከአዋጁ በፊት ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ለመመለስ የሚሳቀቁበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ፍጹም የተገፈፈበት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚታወቁበት የመከባበርና የመቻቻል ዕሴት በጸረ ሰላም ሃይሎች ህገወጥ ድርጊት የመሸርሸር ዝንባሌ የታየበት እንደነበር፤ እንዲሁም፣ ሁኔታው በዚያው ቢቀጥል በአንዳንድ አገሮች የታየው ዕልቂት በአገራችን ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና ያልነበረን እንደሆነም ከአዋጁ መነሳት በኋላ በሴክረቴሪያቱ ሃላፊ በኩል ተብራርቷል።

ከላይ ለተመለከቱት ጉዳዮችና ለዚህ አዋጅ መውጣት ምክንያት የነበሩ ጽንፈኞች እንደሚያራግቡት ሳይሆን አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሳይታወክ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማትም ያለአንዳች ስጋት ስራቸውን ማከናወን የቻሉበት እድል ተፈጥሯል። በአዋጁ አስባብ ሰላማዊ እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ሃይሎችን ማፈን ነው ተብሎ በነዚሁ ጽንፈኞች ዛሬም ድረስ እየተናፈሰ ቢሆንም በሁከትና ብጥብጡ የተሳተፉ አካላት በፈጸሙት የወንጀል ክብደት ልክ በህግ እንዲጠየቁና ሰለባ የነበሩት ደግሞ ተሃድሶ ወስደው የስራ ሰው መሆን እንዲችሉ መደረጉንም በየመንደራችን ከምናውቃቸው የግርግሩ ሰለባ የነበሩ ግለሰቦች የአሁን ሁኔታ ተነስተን መመስከር ይቻላል። ሰላማዊ እና ጊዚያቸውን በስራ ላይ ጠምደው ሌት ተቀን ይለፉ ለነበሩ ዜጎች ስጋት የነበሩ በርካታ  ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠር መቻሉ የአዋጁን ምክንያታዊነትና ፋይዳ የሚያጠይቅ ነው። በአመጽ ተግባር ከተሳተፉት እጅግ የሚበዙት የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሱ መደረጉ ከጽንፈኞቹ አሉባልታ በተቃራኒው መንግሥት ለህዝብ ያለውን ተቆርቋሪነትና ወገንተኝነት የሚያረጋግጥ  ህዝባዊ ተግባር መሆኑንም መካድ አይቻልም። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ተጠርጣሪ ቢሆንም እንኳ የአንዳችም ዜጋ ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ እንዲቋቋም ተደርጎ  በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ ይታዩ የነበሩ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችል አካሄድ ከመጀመሪያው ተዘርግቶ ሥራው በግልጽነት በተከናወነበት አግባብ ነቆራው በእርግጥም ከግርግሩ ለማትረፍ አሰፍስፈው የነበሩ ሃይሎች ቁጭት የወለደው ነው የሚሆነው።

አዋጁ በሥራ ላይ እያለ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎችን የማስፈጸም አቅም የሚያጠናክሩ ተከታታይ ሥራዎች መሰራታቸውም ሌላው ስኬት ነው። በተለይም የክልል የጸጥታ አካላት በሂደት የየአካባቢያቸውን የጸጥታ ሁኔታ በራሳቸው አቅም ለማስጠበቅ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ መደረጉ ዛሬ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ከመደበኛ የጸጥታ ሥራ አቅም በላይ እንዳይሆን ማድረጉም የአዋጁን ምክንያታዊነት ከሚያጠይቁ ጉዳዮች መካከል ሊጠቀስ የሚገባው ነጥብ ነው ።  

በመንግሥት የተያዘው የጥልቅ ተሃድሶ ዕቅድ ከበላይ አመራሩ ጀምሮ እስከታችኛው ህብረተሰብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲወርድና ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመለየትና በተቀመጠው አቅጣጫ ከራሱ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት የሚያስችል ምቹ መደላድል ለመፍጠር ማስቻሉም ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆን አገራችን የተያያዘችው የልማትና የሰላም አቅጣጫ እንዳይደናቀፍ ማድረግ አስችሏል። ይህ ደግሞ ያለ ህዝቡ ንቁ ተሳትፎና የባለቤትነት ሚና የተገኘ አይደለም። የአንዲት አገር ሰላም ለዘለቄታው የሚረጋገጠው በሠራዊት ቁጥር ብዛትና በአዋጅ እንዳልሆነም ያረጋገጥንበትን እድል የፈጠረ እና ያለህዝቡ ተሳትፎ አንዳች ነገር ፈቀቅ ማድረግ የማይቻል እንደሆነ ለመንግስትም ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ አዋጅ ነውና ከአዋጁ አስቀድሞ ብንጎዳም በአዋጁ እንደህዝብም ሆነ መንግስት ዘላቂ የሆነ ትርፍ  አግኝተናል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy