ethiopian news

Artcles

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለድርድር አይቀርብም

By Admin

August 28, 2017

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት

ለድርድር አይቀርብም

ዮናስ

ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የተሃድሶ መስመሩ የህዝብ መስመር ሆኖ፣ ይህን መስመር በሚያቀነቅን ፓርቲና መንግስት እየተመራ አስገራሚ የሚባል ለውጥ እየተመዘገበ ቢመጣም፣ በመስመሩ ሰነዶች ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የመስመሩ ዋንኛ አደጋ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አለመደፈቁ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት በአጭሩ ያለአግባብ የመጠቀም አመለካከትና ተግባር ነው። በአቋራጭ የመክበር አስተሳሰብና ተግባሩ በግለሰብም ይሁን በቡድን የሚንፀባረቅ ለመሆኑ ከእኛይቱ ሃገር በላይ ማሳያ መጥቀስ አያስፈልግም። ሰሞኑን ያየናቸው እና በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ወደ 52 የሚጠጉ ግለሰቦች እና ወደ 209 የሚጠጉ ንብረታቸው የታገደባቸው ኩባንያዎችና ግለሰቦች የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው።

ህግና ስርአትን ተከትሎ ሰርቶ ከመበልፀግ ይልቅ ህግና ስርአትን በመናድ ጥቅሞችን እያግበሰበሱ፣ የአቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም ህገ-ወጥነትን ለማንገስ ቀን ከሌት ሲተጉ የነበረ ለመሆኑም የክስ ዝርዝራቸው በሚገባ አረጋግጧል። ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይልቅ የግል ተጠቃሚነትን በሚያጎለብት ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀው የነበረ ለመሆኑም የፖሊስ መረጃ በሚገባ አጠይቆልናል። ስርአት አልበኝነትን በማስፈን በስርአቱ ውስጥ ትናንሽ መንግስታትን ለመፍጠር የመሞከር መስመር ዘርግተው የነበረ መሆኑም ከቀረበው የክስ ጭብጥ ለመገንዘብ ተችሏል። ይህ እንቅስቃሴያቸው እና መጠላለፋቸው በሂደት ዜጎች በስርአቱ ላይ እምነት እንዲያጡ የሚያደርግ ለመሆኑም የማያከራክር ከመሆኑም በላይ፤ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ባይተዋር እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው።

የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ሰርተው መበልፀግ ለሚሹ ወገኖች መሠረተ ልማት ሳይሟላ፣ የመሬት አቅርቦትና የብድር አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ተደራሽነት ሳይሟላ ሲቀር ለመፋፋትና መስፋፋት ሰፊ እድል ያገኛል የሚል የባለሙያዎች አስተያየት አለ። በአገራችን ውስጥ ይህን እድል ለመዝጋትና ልማቱን ለማፋጠን በማሰብ በስፋት ተሠርቷል። ሙሉ ለሙሉ ባይባልም የመሬት፣ የብድር አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ ልማት ላይ፤ እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ ሰፊና ያልተቋረጠ ስራ ተሰርቷል። በሁሉም አቅጣጫ በሚባል ደረጃ አስፈላጊ የሚባለው የመሠረተ ልማት አቅርቦት ተሟልቷል፤ በመሟላትም ላይ ነው። ይሁን እንጂ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት በከተሞች የበላይነቱን የያዘበት ሁኔታ ስለመስተዋሉ እነዚህን ከላይ የተመለከቱ ተጠርጣሪዎች ጨምሮ በየክልሉ እየተካሄደ ከሚገኘው የጸረ ሙስና ዘመቻ ማረጋገጥ ይቻሏል ።

ስለሆነም በእነዚህና መሰሎቻቸው ላይ እየተወሰደ ከሚገኘው እርምጃ ባሻገር ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ስርዓትን በማጎልበት ዘላቂነት ያለውን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የሚገባ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ለምን ቢባል ግልጸኝነት የነገሰበት አሰራርን ማጎልበት  ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ሚናው የጎላ ነውና።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን  በተለይ  የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብንና ተግባርን  በዘላቂነት ማስወገድ የሚቻለው አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፤ የግልጽኝነትና ተጠያቂነት አሰራሮችን በማጎልበት ነው። መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ በተገቢ ማስረጃ ላይ  ተመስርቶ ለፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ  ሲያደርግ ቆይቷል፤ ይህ አካሄድ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ ወደፊትም  የሚቀጥል እንደሚሆን የማያከራክር እና በይፋም ቃል የተገባ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግለሰብ ወንጀለኞችን በማሰር ብቻ የታሰበውን ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ማመንና ስለአስተሳሰብ ለውጥ በርትቶ መስራት አስፈላጊ ይሆናል።

ይህ እንዳለ ሆኖ፤ መንግስት የህግ የበላይነትን ጉዳይ መቼም ቢሆን ለድርድር ማቅረብ የለበትም። የትኛውም አካል፣ የመንግስት የስራ ሃላፊም ሆነ ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ እስከተገኘበት ድርስ ከተጠያቂነት መዳን የሌለበት መሆኑን ተገንዝቦ መስራት ይጠበቅበታል። ስለሆነም ኢህአዴግ ቀድሞም ይሁን አሁን በድርጅትም ይሁን በመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ላይ  እያደረገ ያለውን የተጠያቂነት አሰራር በቀጣይም አጠናክሮ ሊቀጥል የግድ ነው።  

ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን መቅበር የሚቻለው ሙስናን የሚጠየፍ ህብረተሰብ ሲገነባ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል በማስተማር፣ ሙስናን በመታገል ረገድ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታለል። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል ዋንኛው ብልሀት በህብረተሰቡ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት መሆኑን መቼም ቢሆን መዘንጋት አይገባም። የአሁኑ ዘመቻም የዚህ አካል እንጂ ሌላ ሊሆን አይገባም። ይህ እንደመርህ ተይዛ ካልተሰራ ከዘመቻ የሚገኘው ውጤት ጊዜያዊ ማስተንፈስና ስራ መፍታት ነው።   

ሰሞኑን እንደተስተዋለው ዘመቻውም ሆነ የአስተሳሰብ ለውጡ እየተካሄደ ያለው የተሳሳተ የትምህርት ማስረጃን እና ሌሎች አገር ተረካቢ ትውልድን የሚያመክኑ አካሄዶችን በማጋለጥ ነው። ሁሉም ክልሎች ይህን ተግባር አጠናክረው መቀጠል አለባቸው። መንግስት   ተግባራዊ እያደረገ ያለው የትምህርት ማስረጃን የማጣራቱ ስራ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያደርገው ጥረት አንዱ  አካል ነው። ስለሆነም ሂደቱ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም ።

በዚህ አይነት ዘመቻ ወቅት ግን የዘመቻው ፊት አውራሪ የሆነው ህዝብ ሊዘነጋ የማይገባው መሰረታዊ ጉዳይ ያለ ሲሆን፤ እሱም የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለጋራ ልማትና አገር ግንባታ የሚያደርጉት ርብርብ ስለማይመቸው በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን ለማደናቀፍ የሚጥሩ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ዘመቻ ነው። ከሰሞኑ የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞም በእንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎች ላይ እነዚህን ሃይሎች አይተናልና።

ከሰሞኑ እርምጃ ጋር ተያይዞ ቀድሞ አደባባይ የወጣው የጥበት ሃይሉ ነው። ጠባብነት ሌላውን በጠላትነት የሚመለከት፣ ያለፈ በደልን ጭቶ እያከከ ቁስሉን በማመርቀዝ፣ በታሪክ  ሂደት ውስጥ ገዥ መደቦች የፈጠሩትን ስህተት የአንድ ብሄር አባላት እንደፈፀሙት አድርጎ በማቅረብ ዘዴው ሰዎችን ለብጥብና ለጥላቻ እያነሳሳ የሚጓዝ ሃይል ነው። እየሆነና እየታየ ስላለው እድገትና ህዝቦች በትግላቸው ስለተቀዳጇቸው መብቶች፤ ከመብቶቹም ስለተገኙ ጥቅሞች አብዝቶ ከመናገርና እነዚህን እድሎችና መብቶች አስፍቶ ከመጠቀም ይልቅ የፌዴራል ስርአቱ የአፈፃፀም ክፍተቶችን ለቅሞ በመቀመር፣ በአመራር፣ በመዋቅርና በፈፃሚው ሃይል የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችንና ከኢኮኖሚ እድገቱ ጋር ተያይዘው የመጡ የእድገት ፍላጎቶችንና ጥያቄዎችን አውገርግሮ የፖለቲካ ጥያቄ በማደረግ ሁሌም የመነጠል ጥማቱን ለማርካት ሲሰራ የሚስተዋልና ሰሞኑንም በዚሁ ድርጊቱ በመገለጥ ዘመቻውን ለማደናቀፍ እየተጋ መሆኑን መገንዘብ የዘመቻው ሞተር ከሆነው ህዝብ ይጠበቃል።

በዚህም ምክንያት በአስተሳሰቡ ዙሪያ ሰዎችን በማሰባሰብ፣ በማሰልጠንና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በመደለል ሁከትና ብጥብጥ ለመፈጠር ሰርቷል፤ አሁንም እየሰራ ያለው ይህንኑ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። የአገራችን ሰላም ለማደፍረስ የቻለውን ያህል ሄዷል፤ በልማታዊ መንገድ ሠርተው ለመበልፀግ የሚጥሩ ዜጎችን ሃብትና ንብረት አውድሟል፤ አሁንም እየሞከረ ያለው ይህንኑ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው። ብሄር ላይ ያነጣጠር የጥላቻ ዘር በመዝራት ሰዎች እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ እንዳይተማመኑና ከልማት ግስጋሴያቸው እንዲገቱ ባለ በሌለ ሃይሉ ተፍጨርጭሯል። የጥበት ሃይሉ በሚኖርበት አካባቢና አስተሳሰቡን በተሳሳተ መንገድ በሚሸምቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የዘራው ጥላቻና የጥፋት አመለካከት ውድምትን ከማስከተል አልፎ ማህበረሰባዊ ቅራኔዎችንና ጥርጣሬዎችን እስከመፍጠር ደርሷል።

በመሆኑም፣ ይህንን እኩይ ተግባርና አውዳሚ አስተሳሰብ በውል ተገንዝቦ በመንቀሳቀስ የተጠያቂነት አሰራር የሰፈነባት፤ የህግ የበላይነት ለድርድር የማይቀርብባት ሃገር መገንባት ተገቢና የወቅቱ አቢይ አጀንዳ ሊሆን ይገባል።