Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተቀድቶ የማያልቀው የመለስ ስብዕና

0 425

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተቀድቶ የማያልቀው የመለስ ስብዕና

                                                                  ደስታ ኃይሉ

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩባቸው ጊዜያት ያስተላልፏቸው የነበሩትን አይረሴ አስተምህሮዎችንና ያከናውኗቸው የነበሩትን ተግባሮች ሁሌም በህያውነት የሚዘከሩ ናቸው። ይህ የመለስ ሁለንተናዊ ስብዕና ለዛሬው ትውልድ ትልቅ ፋይዳ ያለው ከመሆኑም በላይ፤ ህዳሴያችንን ለማረጋገጥም መሪ ብርሃንም ጭምር ነው። የመለስ ስብዕና ለወጣቶች አርአያ፣ ለአገር ደግሞ የህዳሴ ፋና ወጊ መሆኑም የሚካድ አይደለም።

አቶ መለስ ድርጅቱ ያፈራቸው የዘመናት ክስተት ናቸው። እንደሚታወቀው ሁሉ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ አሁን ለሚገኝበት ስኬታማ ምዕራፍ የበቃ ድርጅት ነው።

ድርጅቱን የመሰረቱ አብዩታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግዙፉን የደርግ ስርዓት በተናጠልም ሆነ በጋራ ለመፋለም ትግል ያካሄዱ ከነበሩበት ወቅት ጀምሮ በርካታ በሳል አመራሮችን ፈጥረዋል፤ መስዋዕትም ሆነዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ታጋይ ድርጅቶች ታላላቅ አመራሮቻቸውን ባጡባቸው ጊዜያት ሁሉ ከትግላቸው ወደ ኋላ ያሉበት አሊያል እንደጉም የተበተኑበት ሁኔታ አልተፈጠረም።

ይልቁንም የአመራሩን ሚና በመተካካት ትግሉን የቀጠሉበትና ለድል የበቁበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ከዚህ አኳያ አቶ መለስ በትግሉ ሂደት ውስጥ የተፈጠሩና የበቁ የኢህአዴግ አመራር ናቸው። በዓላማ ፅናታቸው፣ በብቃታቸውና በችሎታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ በመቻላቸው በድርጅታቸው ውስጥ የመሪነት ቦታን ተረክበው ለረጅም ጊዜያት አገልግለዋል።

ይህ ማለት ግን ድርጅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን (የራሳቸው ከፍተኛ ጥረት ታክሎበት)  እዚህ ታላቅ ደረጃ ላይ በማድረሱ ተግባሩን እንደ መጨረሻው ስኬት ቆጥሮ እጁን አጣጥፎ ተቀምጧል ማለት አይደለም። ስለሆነም እርሳቸውንም ሆኑ ሌሎች የድርጅቱ አመራሮችን የሚተኩ አመራሮችን በሂደት እየፈጠረ ጉዞውን የቀጠለበት አግባብ መፍጠር ችሏል።

በዚህም ዛሬ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስንና ድርጅቱን ዓላማ የሚያሳኩ በሺህዎች የሚቆጠሩ አመራሮችን መገንባት ተችሏል። እነዚህ አመራሮችም የአቶ መለስን የዱላ ቅብብሎሽ የትግል ሩጫ ይዘው ሂደቱን በማስቀጠል ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም የአቶ መለስ ራዕይ እየፈካና እየደመቀ ነው ማለት እንችላለን።

ይሁንና እኚህ በታሪክ ዑደት ውስጥ አንዴ ብቻ ሊፈጠሩ የሚችሉ የህዝብ ልጅ፤ ውስብስብ በሆነው የዲፕሎማሲው ዓለም ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካ ህዝቦች ድምጽ በመሆን ያበረከቱትን የማይተካ አስተዋጽኦን በጥቂቱም ቢሆን በመዳሰስ ተገቢ ነው፡፡

በቅድሚያ ግን ወትሮም ግጭትና አለመረጋጋት በማይለየው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ካበረከቱት ወደር የሌለው አስተዋጽኦ እንነሳ፡፡ አቶ መለስ የኤርትራ መንግሥት ሀገራችንንና ምስራቅ አፍሪካን የጦርነት አውድማ ለማድረግ የቀመረውን የሽብር ስትራቴጂ በቅርበት በመከታተልና ብቃትና ብስለት ባለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እየተመሩ የአስመራው አስተዳደር ለመፍጠር የሞከረውን ቀጣናዊ ቀውስ ለማርገብ በቁርጠኝነት ሲሰሩ የነበሩ አፍሪካዊ ናቸው፡፡

አቶ መለስ ኢትዮጵያን ሲመሩ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በላይቤሪያና በሱዳን ዳርፉርና አብዬ ግዛት መከላከያ ሠራዊታችንን በማሰማራት ለአፍሪካውያን ሰላም መረጋገጥ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ የተጉ የአፍሪካዊያን ተቆርቋሪ ነበሩ፡፡

በእርሳቸው አመራር ሰጪነት የተሰማራው ሠራዊታችንም የተሰጠውን ግዳጅ በብቃትና በፍጹም ወታደራዊ ዲስፕሊን በመታገዝ የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑን በተግባር አረጋግጧል፡፡

እርግጥ እኚህ ባለራዕይ፣ የአፍሪካ ኩራትና ዲፕሎማት ዓለምን ያስደመሙ በሳልና አርቆ አስተዋይ መሪ ዛሬ በህይወት የሉም፡፡ የሀገራችንን ስም በዓለም አደባባይ የማደስ፣ የአፍሪካን ዘላቂ ጥቅሞች የማስጠበቅ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ገንቢ ሃሳቦችን የማቅረብ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ሥራዎቻቸው ግን ዛሬም ከእኛ ጋር ናቸው፡፡

ግና እዚህ ላይ ‘የአቶ መለስን የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እንደምን ማስቀጠል ይቻላል?’ የሚል ጥያቄን እንደ ዜጋ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ አቶ መለስ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ሀገራችንን በመሩባቸው ጊዜያት ያስተማሩን ታላቅ ጥበብ አለ፡፡ ይኸውም በማንኛውም ወቅት ሁሉም ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር በመሆን  በግለሰብ ደረጃ የሀገራችንን ገፅታ መገንባት የሚችል መሆኑን ነው፡፡

ማንኛውም ዜጋ በሚሰማራባቸው የስራ አካባቢዎች ሁሉ የብሔሩ ብሎም የሀገሩ አምባሣደር በመሆን የሀገራችንን ገፅታ መገንባት ይችላል፡፡ ስራውን በሚያከናውንበት ወቅት እንደ ግለሰብ የምንፈፅማቸው ማናቸውም ተግባራት የሀገራችን መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡ ባህላችንን፣ ወጋችንን፣ ትውፊቶቻችንን በየተሰማራንበት ቦታ ስናስተዋውቅ ደግሞ እግረ-መንገዳችንን እኛነታችንን እንገልፃለን፡፡

እኛነታችንን ስንገልፅም ሀገራችንን የቱሪስት መዳረሻ እናደርጋለን፡፡ይህም ገቢያችን እንዲጨምር ያደርጋል። በዚያው ልክም ወደ መካከለኛ ገቢ የምንደረደርበት አቅም ይጨምራል።

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚያከናውን ማንኛውም ግለሰብ የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሁነኛ የዲፕሎማሲ ተዋናይ ይሆናል፡፡ የዕድገታችን ዋስ ጠበቃ መሆኑም እንዲሁ። አቶ መለስ እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ መሪ ያስተማሩን ይህንኑ ነው፡፡

እናም ‘እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ አምባሣደር ነው’ የሚለውን አባባል ሁሌም በማስታወስና በመተግበር፣ ታሪካቸው ለዝንተ- ዓለም የማይፋቀውን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን የዲፕሎማሲ ራዕይ በየደረጃችን ልናስቀጥል እንችላለን፡፡

እነሆ ተወዳጁ፣ የሩቅ ህልም ያላቸው፣ አስተዋዩ፣ ሁለመናቸውን ለህዝብ የሰጡት፣ የአፍሪካና የዓለም መከታ ዛሬ በህይወት ባይኖሩም፣ ትግል እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚሸጋገር ነውና  ጅምር የዲፕሎማሲ ስራዎቻቸው ከእኛው ጋር ህያው ሆነው ይኖራሉ፡፡ ገና ሚሊዮን “መለሶችንም” ይፈጥራሉ፡፡

የአቶ መለስን ተዝቆ የማያልቅ ስብዕና በአምስተኛው ዝክረ ሙት ዓመታቸው ላይ በጥቂቱም ቢሆን በዚህ መንገድ መዳሰስ የእኚህን ብርቅዬ አፍሪካዊ ስብዕና በተገቢው ሁኔታ ለመገንዘብ የሚያስችል ይመሰለኛል፡፡ አቶ መለስ ለአገራችን ያበረከቷቸው በርካታ ጉዳዩችን በይበልጥ ካበረከቷቸው የተለያዩ ሰነዶች መረዳት ቢቻልም፤ ነገም ቢሆን የእርሳቸውን ስብዕና ተከትለን የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ በራዕያቸው ልንመራ ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy