ethiopian news

Artcles

ታዳሽ ኃይልና የአገራችን ጥረት

By Admin

August 10, 2017

ታዳሽ ኃይልና የአገራችን ጥረት

                                                        ደስታ ኃይሉ

የኢትዮጵያ መንግስት ከታዳሽ ኃይል ኤሌክትሪክ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረገ ነው። በተለይም አካባቢን ለመጠበቅ እንዲሁም በዘላቂነት ከአካባቢ ብክለት ነፃ የሆኑ ተግባራትን ለማከናወን እያደረጋቸው ያሉት ተግባሮች በዋነኛነት ተጠቃኝ ናቸው። ይህም ኢትዮጵያ በዘላቂነት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

መንግስት ይህን ቁርጠኝነቱን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ በሚገባ አስቀምጦታል። በእቅዱ ላይ የተነሱትን ዋና ዋና ነጥቦች ከማየታችን በፊት ግን ጥቂት ስለ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ማውሳት ያስፈልጋል።

ዓለማችን በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለውጥ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ለችግሩ መከሰት በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱት፣ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች መጨመርና የደን ሃብት እየተመናመነ መምጣት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ሆኖም ችግሮቹን ለመፍታት የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤን ማጎልበትና በደን ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተመራጭ መፍትሔ ናቸው። በተለይም በግብርና ምርታማነት ላይ መሰረቱን ለጣለ ኢኮኖሚ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው።

ታዲያ ይህን ሃቅ ቀድማ የተገነዘበችው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመከተል ላይ ትገኛለች።

በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያረጋግጡት፤ ኢትዮጰያ ታዳሽ ሃይልን በመጠቀም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መርሃ ግብርን በአግባቡ እየተገበረች ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን በግንባር ቀደምትነት እየተወጣች ነው። ታዳሽ ኃይል በኢትዮጵያ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የሚቀዳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ አራት ዋና ዋና መሰረታዊ ነጥቦችንም የያዘ ነው፡፡ የመጀመሪያው የግብርና ልማትና የመሬት አጠቃቀም ብቃትን ማምጣት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የደን ልማትና ጥበቃ ስራን ኢኮኖሚያዊና የስነ ምህዳር  ስርዓትን  በሚጠቅም አግባብ ያስኬዳል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ተገቢ፣ የተሻሻሉና ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአንዱስትሪ ልማት ለትራንስፖርት አገልግሎትና ለግንባታ ስራዎች መጠቀምን ይይዛል፡፡ አራተኛው ታዳሽና ንጽህ ሃይልን የማመንጨት ልማት ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦችም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ከግብ ያደርሳሉ የሚባሉ ናቸው፡፡

ስትራቴጂው ሦስት ተመጋጋቢ ዓላማቸዎችንም መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገትን ማምጣት በአረንጓዴ ልማት የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትን መቀነስና የሰከነ የአየር ንብረት ሁኔታን ማረጋገጥ ነው፡፡ የታዳሽ ሃይል ደግሞ ለዚህ ስትራቴጂ ዋነኛ መሰሶ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

ሀገራችን ያላት ሰፊ የታዳሽ ሃይል የማመንጨት እምቅ አቅም ልማትን ቀጣይነት ያለው የማስኬድ ዕድሉና የአካባቢ አየርን ጤናማ ለማድረግ የሚያስችል ዋነኛ አማራጭ በመሆኑ ነው፡፡

ታዳሽ ኃይል ከኢኮኖሚ ባሻገር ፖለቲካዊ አንድምታውም የሚናቅ አይደለም፡፡ አሁን አሁን የሀገራትን የርስ በርስ ግንኙነት እስከመወሰን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሶል፡፡ ከታዳሽ ሃይል ሌላ አማራጭ  ሆኖ ያለው የነዳጅ ሃይል ካለበት ውስንነት ወይም አላቂነት የተነሳ ታዳሽ ሃይልን የመምረጥ ጉዳይ በእርግጥም ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው ነው፡፡

የኃይል ዋስትና የማግኘት፣ የኢኮኖሚ መሰረቱንና የአካባቢ ጥበቃ ዋንኛ ጉዳይ በመሆኑም  የፖለቲከኞች ዋነኛ ትኩረት ነው፡፡ ስለዚህ ሀገራት የታዳሽ ሃይልን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ልማት የመገንባት ግፊት ውስጥ ናቸው፡፡

በተለይም ደግሞ የአካባቢ አየር ብክለት በሚያመጣው መዘዝ በየሀገሪቱ ያሉ ዜጎች በሚገጥማቸው የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት መጎዳታቸው በቀጠለ  መጠን ጉዳዩ  የዜጎች ብሎም የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑ አይቀርም፡፡

በተጨማሪም የማህበረሰቡ አንቀሳቃሽ የሆነው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ የትኩረት አቅጣጫውን እንዲለወጥ ይገደዳል ለማለት ነው፡፡ ሀገራት እርስ በርሳቸው የሚኖራቸው ግንኙነት፣ ትብብር፣ ተፅዕኖና የውድድር መንፈስም ይህንን መነሻ የማድረጉ ነገር በየጊዜው ማደጉ አይቀርም።

የአየር ንብረት ለውጥ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሃገራት ተፅዕኖው የጎላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመንደፍ ለታዳሽ ሃይል ትኩረት የሰጠችው ለዚህ ነው፡፡ የኃይል ልማት ፖሊሲው ከነባሩ ወይም ባህላዊ መንገንድን ተከትሎ ከሚደረገው የሃይል ማመንጨት ስራ ቀስ በቀስ ዘመናዊ የሃይል አጠቃቀምን መከተል እና መሸጋገር እንዳለባት ተቀምጧል፡፡

አስተማማኝ የሃይል አቅርቦትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም የማዳረስና ለኢኮኖሚውም ዕድገት በቂ ሃይል የማቅረብ ሃሳብም ያለው ነው፡፡ ፖሊሲው ለሀገር ውስጥ የሃይል ምንጭ ቅድሚያ በመስጠት ራስን መቻልን ያልማል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ንጽህ ሃይልን ቆጥቦ በብቃት በመጠቀም የአካባቢ የአየር ሁኔታ ጤናማነትን ከማስቀጠል ረገድ የሚሰራ ፖሊሲ ነው፡፡

ይህን ስኬታማ ለማድረግ የግብርናን ማርታማነት በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ልማቱ መሰረት ማድረግና የኤክስፖርት ደረጃን ለማሳደግ ታስቦም እየተሰራ ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ ራዕይዋን እውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ለአለም አቀፉ ማህብረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ፈተና ሆኖ የተጋረጠውን የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት መዋጋትና ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ሲቻል ነው። ይህን እውን ለማድረግም ሀገራችን ጠንክራ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ እንደተጠቆመው አስፈላጊ እርምጃዎች አስቀድሞ ካልተወሰዱ እ.ኤ.አ. እስከ 2050 ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የሙቀት መጠን ከአንድ ነጥብ 7 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እስከ 2 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊያድግ ይችላል የሚል ግምት አለ። ይህ የሙቀት መጠን የምግብ ዋስትና እንዳይረጋገጥ፣ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዲከሰቱ፣ የመሬት መጎሳቆልና የመሠረተ ልማት ውድመት እንዲከሰት ሊያደርግ የሚችል ነው።

ታዲያ አደጋውን ለመቀነስና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችልና ኢትዮጵያን በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ላይ ከደረሱ ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተቀመጠውን ራዕይ መሰረት ያደረገ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተቀርፆ ገቢራዊ ሆኗል።

በተለይም በተፋሰስ ልማት በህዝባዊ ንቅናቄ ሰፊ ጥረት የተደረገና አጥጋቢ ውጤት እየተመዘገበበት ነው። በእቅድ ዘመኑንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም ወጣቶች በስራው ላይ በስፋት ተሳትፈው ራሳቸውንና አገራቸውን በመጥቀም ውጤት እያመጡ ነው። እነዚህ በታዳሽ ሃይል አማካኝነት የሚከናወኑ ስራዎች አገራችን የራሷን ብሎም የዓለምን ችግር ለመፈታት የምታደርገው ጥረት አካል ናቸው።