Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትኩረትን እየሳበች የመጣች አገር

0 447

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ትኩረትን እየሳበች የመጣች አገር

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ሥርዓቶች የእርስ በርስ ግጭትና ሥር የሰደደ ድህነት ተምሣሌት ተደርጋ ትታወቅ ነበር። አሁን…አሁን ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግሥት ትክክለኛ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በመንቀሳቀሱ ኢትዮጵያ በዓለም በአርአያነት ተጠቃሽ አገር ለመሆን በቅታለች።

 

ከዚህ ቀደም በነበራት መጥፎ ገጽታዋ የተሳለችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ነገሩ ሁሉ ተቀይሮ የአገራት ተሞክሮ አቋዳሽ ለመሆን በቅታለች። መንግሥትና መላው ህዝቦቿ አንድነት ፈጥረውና እጅ ለእጅ ተያይዘው ባለፉት 26 ዓመታት ባከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት በዓለም አቀፍ መድረክ በአዲስ ገፅታ መታየት ጀምራለች፡፡ የለውጥ አብነት ተደርጋም መወሰድ ጀምራለች።

 

በኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ያላሰለሰ ጥረት ጠንካራና ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከመመዝገቡ ሌላ አገሪቱ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ መድረኮች ጭምር ተደማጭነቷ እየጎላ መጥቷል፡፡ አገሪቱ እነዚህን ስኬታማ ድሎችን ለመጎናፀፍ የቻለችው ባለፉት 26 ዓመታት በተለያዩ መስኮች ተቀርፀው ተግባራዊ በተደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አማካይነት ነው፡፡

በአገሪቱ ውጤታማ ከሆኑት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መካከል የውጭ ጉዳይና የአገራዊ የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በዋናነት ተጠቃሽ ነው። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 86 ላይ የተዘረዘሩትን የውጭ ግንኙነት መርሆዎች መሠረት በማድረግ ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂ የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም፣ ህልውናና ደህንነት ከአደጋ ለመከላከል፣ ገጽታዋን በበጎ ለመገንባትና የምጣኔ ሀብት ዕድገቷን ለማስቀጠል እንዲሁም የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሥርዓትን ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ ተቀርጾ በተግባር ላይ ውሏል፡፡

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባህሪ፣ ይዘትና ቅርጽ አገሮች እንደሚያራምዱት ርዕዮተ ዓላማዊ መስመርና እንደሚከተሉት የዕድገት አቅጣጫ ይለያያል፡፡ ከዚህ አንጻር ያለፉት ሥርዓቶች የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲቃኝ በተለይም የወታደራዊው ደርግ የውጭ ግንኙነት ከሥርዓቱ አምባገነናዊ ባህሪይ የመነጨ ነው። በዚያው ልክም በርካታ ጉድለቶች ነበሩበት። ይህም ውጤት አገሪቷን ለከፋ ምጣኔ ሀብታዊ ድቀትና ለማያባራ ጦርነት ዳርጓታል፡፡ አገሪቱ በሠላም እጦት ስትታመስ ቆይቷል። በዚህም ከሠላም ታገኝ የነበረውን ጥቅም አጥታለች።  

 

ደርግ ይከተለው በነበረው አምባገነናዊ ሥርዓት ምክንያት ኢትዮጵያና ዜጎቿ ከጎረቤት አገሮች ሕዝቦች ጋር የነበራቸው ግንኙነት በጥርጣሬ መንፈስ የተሞላ ነበር። ግንኙነታቸው ወታደራዊ አቅምን በማፈርጠም በጠብ መፈላለግ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ በዓይነቱም፣ በይዘቱም ሆነ በባህሪው ፍፁም ተለውጧል፡፡ ኢትዮጵያ ከአገሮች ጋር የሚኖራት ግንኙነት በጋራ ጥቅምና ህልውና ላይ የተመሠረተ ሆኗል። በህዝብ ልጆች መስዋዕትነት የፀደቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት አገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሠረት ጥሏል፡፡

 

የዛሬዋ ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደ ቀድሞዎቹ የአገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለት ውጭ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። ይልቁንም ቅድሚያ የአገር ውስጥ ሠላምን በማስፈን በከባቢ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲኖርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡

 

ይህ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅና አገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም አገር ጋር የሚኖረው ግንኙነት በመሠረታዊ አገራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የተመሠረተ፤ የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ሥር እየሰደደና የአገሪቱ ዕድገትም እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የአደጋ ተጋላጭነትን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ደህንነትን በአስተማማኝ ደረጃ ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በአገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነም ይታመናል፡፡

 

በዚህ ሁኔታ ተመስርቶም አገሪቱ የምትከተለው ዲፕሎማሲ ላይ በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ ያልተፈቱትን  ለመከላከል አቅም መገንባት ተተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው በግልጽ አስፍሯል።

 

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በሠላምና በዕድገት ጎዳና መጓዝ በጀመረችባቸው ዓመታት ፖሊሲውና ስትራቴጂው በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና  በማህበራዊ እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት መስኮች ያስገኛቸው ስኬቶችን መመልከት ይገባል። የፖሊሲውና የስትራቴጂው አንዱ የትኩረት አቅጣጫም የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ነው፡፡

በዚህ ተግባር ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ልማታዊ ዲፕሎማሲው ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቶቿን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ተግታ እየሰራች ነው፡፡ በዚህም ውጤታማ ሆናበታለች።

የአገሪቱን የውጭ ግንኙነት በማጎልበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሥፍራ የበለጠ ለማሳደግ ባለፉት 26 ዓመታት ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል። በአገሪቱም ሆነ በቀጣናው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሠላማዊ ጥረት ብቻ እንዲፈቱ  ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እየሰራች ትገኛለች፡፡

 

ኢትዮጵያ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሠላም ዲፕሎማሲ መርህ መሠረት በዓለም ዙሪያ ካሉት አገሮች ጋር ያላት ትስስር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነቷ ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች አገሮች ጋር ትልቅ ሥፍራ ላይ ደርሷል፡፡

 

ታዲያ ይህ ሊሆን የቻለው የኢፌዴሪ መንግሥት ቀደም ሲል አገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተና ጎረቤት አገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድ ላይ በጽንሰ ሀሳብም ሆነ በተግባር መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚል ጽኑ እና ቁርጠኛ እምነት በመያዝ በሁሉም ዘርፎች የላቀ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።  

 

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የሥጋት ምንጮች ነጻ ልትሆን የምትችለው በአገሪቱ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ሲካሄድ ነው፡፡ ከዚህም ህዝቡ የዕድሉ ተጠቃሚ ሲሆን ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አሁንም ህዝብና መንግሥት በቅርበት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy