Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትግሉን አልሰማሁም፣ አላየሁም  ማለት አይቻልም!

0 596

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…ትግሉን አልሰማሁም፣ አላየሁም  ማለት አይቻልም!

ወንድይራድ ኃብተየስ

አመልካች ጣታችንን ወደሌላው ስንጠቁም ቀሪዎቹ አራቱ ጣቶቻችን ወደራሳችን እንደሚያመለክቱ  መገንዘብ  ተገቢ ነው።  ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ዘርፍ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ስለኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተው የንግዱ ማህበረሰብ  የሚጠበቅበትን  ያህል  ተሳትፎ እንዳላደረገ  ተናግገረዋል። የንግዱ ማህበረሰብ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በተገናኘ ጊዜ ሁሉ ስለህገወጥ ንግድ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ግብር አወሳሰን፣ ወዘተ ሲያማርር አድምጠናል፣ ተመልክተናልም። ይሁንና አሁን ላይ መንግስት ሁኔታዎችን ለማስተካከል በተነሳበት ወቅት የንግዱ ማህበረሰብ መንግስትን ለመደገፍ ሲንቀሳቀስ አልተመለከትንም። … አልሰማሁም፣ አላየሁም  ማለት አይቻልም።  

አዎ በኪራይ ሰብሳቢዎች ህጋዊው የንግዱ ማህበረሰብ ከፍተኛ ጉዳት  የደረሰበት ዘርፍ  ነው። መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ለህዝብ የገባቸውን ቃልኪዳኖች ደረጃ በደረጃ በመወጣት ላይ ነው። የጸረኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት አንዱ አካል ነው።መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይቀርፋል ያለውን አሰራር ከመዘርጋት ጎን ለጎን ሌቦችንም ወደ ህግ በማቅረብ ላይ ነው። ይሁንና ሙስና እጅግ የረቀቀና ውስብስብ አስተሳሰብና ተግባር በመሆኑ በዚህ ዘርፍ መንግስት ብቻውን የፈለገውን ያህል ቢሮጥ  የሚያመጣው  ለውጥ አይኖርም።

ጉቦ መስጠትና መቀበል በስውር የሚካሄድ ተግባር በመሆኑ መንግስት የፈለገውን ያህል  ቢሮጥ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ለውጥ አያመጣም። የንግዱ ዘርፍ የተፈጥሮው ሁኔታ ከሌሎች መስኮች በከፋ መልኩ ለኪራይ ሰብሳቢነት  የተጋለጠና የተጠቃ ዘርፍ ነው። በመሆኑም መንግስት ይህን ዘርፍ ከኪራይ ሰብሳቢዎች ለማጽዳት እያደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይጋበል። በአገራችን በርካታ የሚያገግጉ ለውጦች አሉ። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም በህጋዊ መንገድ ሰርቶ መለወጥ የሚችልበት ሁኔታዎች ያሉ በመሆናቸው ህገወጥ ስራ ውስጥ መዘፈቅ አይገባም። ይዋል ይደር እንጂ ሰርቆ የከበረ ከህግ አያመልጥም።      

ኢትዮጵያ  በሁለቱ በርካታ ተከታዮች ባሏቸው  ኃይማኖቶች  ቅዱስ  የምትባል፣ ቀደምት የሃይማኖት  አገር  ትሁን እንጂ  የስርቆት ተግባሩ ተጧጥፎባታል። በኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች ድርጊታቸውን ቆም ብለው ቢያስቡት ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ የተረዱት አይመስለኝም። ሌብነትን ለልጆቻችን ማስተማር የወረደና የዘቀጠ ተግባር ነው።

መንግስትና ህዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው ደሃን ሲሰርቁና ሲያሰርቁ የነበሩ የስራ ሃላፊዎች  ይዋል ይደር እንጂ ከህግ ተጠያቂነትን አያመልጡም። ኪራይ ሰብሳቢዎች የሰረቁት ደካማ እናታቸውንና አባታቸውን መሆኑን ይገነዘቡት ይሆን? እንደእኔ እንደኔ በሙስና የተሰማሩ ግለሰቦች የህግ ተጠያቂነት ከሚያስከትልባቸው ጉዳት ይልቅ ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው የሞራል መላሸቅ ያስፈራኛል።  አሁን አሁን የሚፈጸሙ የሙሰሽነት  ተግባራትን ስንመለከታቸው  ኃይማኖታዊነታችን ዋጋ አጥቷል፤  ስነምግባራዊነታችን ጠፍቷል፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መስረቅ አሳፋሪ ድርጊት መሆኑ ተዘንግቷል።  

አሁን ላይ አዲሲቷ ኢትዮጵያ በመልካም የዕድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጎዳና ላይ ነች። ከያዝነው የልማት  መንገድ  ሊያደናቅፈን  የሚችል  ማንኛውም ነገር ልንታገሰው አይገባል።  የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ድርጊት ለአገራችን ቀጣይ ህይወት ጠንቅ ተብሎ ከተለዩ ነገሮች መካከል ነው።  መንግስት የጀመረውን የኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ከስኬት ለማድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል። ሁላችንም ይህን ማድረድ የሚጠበቅብን ለራሳችን ብለን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።  በመሆኑም  የተጀመረውን የጸረ-ሙስና ትግልን በምንችለው ነገር ሁሉ መደገፍና ከዳር ማድረስ  ተገቢ ነው። ይህን ትግል  አልሰማሁም፣ አላየሁም  ማለት አይቻልም። አልሰማሁም፣ አላየሁም  ማለት በራሱ ተጠያቂ ያደርጋል።

የፅረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል የታሰበለትን ዓላማ የሚመታው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ግልፅኝነትን በማስፈንና ተጠያቂነትን በማንገስ እንጂ ግለሰቦችን በማሳደድ ብቻ ሊሆን አይችልም። ይህ ሲባል ግለሰቦች ለሰሩት ጥፋት ተጠያቂ አይሆኑም ማለት አይደልም። የህግ የበላይንት መቼም ቢሆን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ከድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ኢህአዴግ ከአመጣጡ ጀምሮ ከህዝብ ጋር  ያለኝን  ግንኙነት  ያሻክራሉ፣ ቅሬታ ያስነሳሉ   ያላቸውን ማንኛቸውንም ተግገባራትን የማጥራት አቅምም ሆነ የቆያ ልምድ ያለው ፓርቲ ነው።  አሁንም የፅረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ የተለያየ አሰራሮችን ከመዘርጋት ጎን ለጎን አጥፊዎችን ወደ ህግ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። ይህን  የመንግስት ጥረት ሁላችንም  ልንደግፈው ይገባል። የንግዱ ማህበረሰብም  የዚህ ወሳኝና  ታሪካዊ የትግል  አካል ሊሆን ይጋባል።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የንግዱ ዘርፍ የኪራይ ስብሳቢነት ተግባርና አስተሳሰብ የሚታይበት አንዱ ዘርፍ ነው። አንዳንድ ነጋዴዎች ከጥቅመኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመቀራረብ የማይገባቸውን ጥቅም ሲያሳድዱ ታይተዋል። በዚህም ድርጊታቸው ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንደይኖር በማድረግ የህዝብንና የመንግስትን ጥቅም ጎድተዋል። ህጋዊና አገር ወዳድ የሆነውን ግብር ከፋይ  ነጋዴም ከመስመር እንዲወጣ አድርገዋል። በመሆኑም ልማታችንን ጎትተዋል።

አሁን ላይ መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ለህዝብ የገባውን ነገሮች  ደረጃ በደረጃ እያከናወነ ይገኛል። መንግስት ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት ላይ ነው። ከላይኛው የአመራር እርከን ጀምሮ በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቀይሯል። በርካቶቹ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል፣ ቀላል የማይባሉትም ላጠፉት ጥፋት ወደ ህግ እየቀረቡ ናቸው። ይሁንና ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ ብቻ   የተፈለገው  ነገር ይመጣል ማለት  አይቻልም። ህብረተሰቡም በተሃድሶው ወቅት  ለመልካም አስተዳደር መስፈን የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ቃል ገብቶ ነበር። ሙስናን በዘላቂነት መከላከል የሚቻለው ጠንካራና አስተማማኝ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት ሲቻል ብቻ ነው።

አንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት  ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በመቀራረብና በመመሳጠር የሚያገኙትን ጥቅም ለመዝጋት መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ልናግዘው ይገባል። ጥቅሙ የሁላችንም ነው። አገር ስትለወጥ እጠቀማለሁ የሚል ቅን አስተሳሰብ በሁላችንም ሊዳብር  ይገባል።  ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የንግዱን ማህበረሰብ ባወያዩበት ወቅት  እንዳሉት አንዳንዶች ከዜሮ  ተነስተው በብረሃን ፍጥነት  ሚሊኒየር ሲሆኑ አንድም  የንግዱ ማህበረሰብ  አባላት ለምን? እንዴት? ብሎ የጠየቀ የለም። አሁንም መንግስት እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ምንም አላላችሁ።  

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግስት በበቂ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ በኪራይ ሰብሳቢነት የተሳተፉ ማንኛውም የስራ ሃላፊዎች  ጭምር ላይ  እርምጃ  እንዲወሰድ ማድረጉ አይቀርም።   ይህንንም መንግስት በተግባር በማሳየት ላይ ነው። አሁን ላይ በርካታ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የንግድ ማህበረሰብንና ደላሎችን በቁጥጥር ሥር ውለዋል። መንግስት የህግ የበላይነትን  በማረጋገጥ ረገድ መቼም ቢሆን ለድርድር አያቀርብም። የፅረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ይቀጥላል። ይዋል ይደር እንጂ  ማንም በዚህ ሂደት የተሳተፈ አካል ከተጠያቂነት አይድኑም።

አንዳንድ ነጋዴዎች የተበላሹ የመንግስት ባለስልጣናትን ከለላ በማድረግ በንግዱ ዘርፍ ላይ ፍተሃዊ  ተወዳዳሪነት እንዳይኖር በማድረግ የማይገባቸውን ጥቅም ሲሯሯጡ ታይተዋል፤ ፍትሐዊ ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት እንዳይኖር አድርገዋል። በዚህም አገር ወዳዱና ህግ አክባሪው ልማታዊ ነጋዴዎች ተጎጂ ሆኗል። አገርም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳጥተዋል። በመሆኑም  የንግዱ ማህበረሰብ መንግስት የጀመረውን የፅረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል መደገፍና ከዳር ማድረስ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy