ነብሩን በመረብ
ነብሩን በመረብ
ክፍል አንድ
ኢብሳ ነመራ
ሰሞኑን የኤርትራ መንግስት የፈጠራቸውና የሚመራቸው፤ መረጃ ዶት ኮም፣ ዘሃበሻ፣ ኢትዮጵያ ዲጄ ወዘተ የተሰኙ ማህበራዊ ሚዲያዎች ስራ በዝቶባቸው ሰንብተዋል። ባለቤትነቱ የአሜሪካ መንግስት የሆነው ቪኦኤ የአማርኛ ፕሮግራምም ሲያጋፍር ነው የሰነበተው። ለአነዚሀ ሚዲያዎች ስራ የሰጣቸው፣ ከመቀባጠር ያለፈ የኦሮሞን ህዝብ የት ሊያደርስ እንዳሰበ ምንም የማያወቅ፤ የማወቅ ፍላጎትም፣ አቅምም የሌለው በስሜት ስካር የሚነዳ ጃዋር መሃመድ የተባለ አንድ ግለሰብ ነው። ጃዋር ኦሮሚያ ውስጥ የስራ ማቆም አድማ አውጇል። እንግዲህ የጃዋርን አዋጅ በማስተላለፍ ስራ የተጠመዱት መረጃ ዶት ኮም፣ ዘሃበሻ ወዘተ የተባሉት ማህበራዊ ሚዲያዎች በኤርትራ መንግስት የሚመሩ በመሆናቸው የተፈጠሩበትን ዓላማ ነው ያስፈጸሙት። ኢትዮጵያን ዳግም ሃገር ልትሆን በማትችልበት ሁኔታ ማፈራረስነው ዓላማቸው። በመሆኑም አድማውን ማወጃቸው፣ አድማውን የሚያስፈጽሙት የሚወስዱትን የሽብር ርምጃ እንደስኬት ማውራታቸው ምንም አይገርምም።
የአሜሪካ መንግስት የሚመራው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም ወይም ቮኦኤ አጋፋሪ ሆኖ መቅረቡ ግን ግራ አጋቢ ነው። ቪኦኤ ጉዳዩን በገለልተኝነት ተመልክቶ ለኢትዮጵያውያን ትክክለኛ መረጃ መስጠት፣ ጉዳዩ ላይ ትክክለኛ እይታ እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠበቅበታል። ይሁን እንጂ በሚያሳዝን፣ በሚያሳፍርም ሁኔታ ይህን አላደረገም። አድማው አንደኛ፣ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል ብሎ ይጀምራል፤ የቮኦኤ ዘገባ። በመቀጠል አድማው ተካሄደ ከተባለባቸው ጥቂት ከተሞች ሰዎችን በስልክ ያነጋግራል። አድማው ተካሄደባቸው በሚልባቸው ከተሞች አድማውን የሚደግፉ የመኖራቸውን ያህል የሚቃወሙ መኖራቸው እርግጥ ቢሆንም፣ ቪኦኤ የሚያነጋግረው ግን አድማውን የሚደግፉትን ብቻ እየመረጠ ነው። ወይም ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ፣ አመቺ ሁኔታ ሲያገኙ ግን ህገወጥነትን የመከተል ልማድ ያላቸውንና ጃዋር የጠራውን ወይም አብረው የጠሩትን አድማ እንደመልካም አጋጣሚ የሚመለከቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ብቻ ነው።
ቪኦኤ አድማው በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች የተቀሰቀሰ አስመስሎ ነበር ሲያቀርብ የነበረው። አድማ ያልተደረገባቸውን በርካታ ከተሞች መኖራቸውን መናገር አልፈቀደም። አድማ የተደረገባቸው ከተሞች ውስጥ አብዛኞቹ ሱቃቸውን የዘጉ ነጋዴዎች፣ መኪናቸውን ጊቢያቸው ውስጥ ያቆሙ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ይህን ያደረጉት ወደው በምርጫቸው ሳይሆን፣ አድማውን የጠሩት ቡድኖች አሰማርተናቸዋል ያሉትን ቦምብና ድንጋይ ወርዋሪዎች ፈርተው መሆኑ እየታወቀ፣ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ያነሳው ነገር የለም።
የቪኦኤ ጋዜጠኞች አድማውን በተመለከተ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ሲያነጋግሩ ስለአድማው ህጋዊነት አላነሱም። የቪኦኤ ጋዜጠኞች አድማው የተጠራው በህገወጥ ቡድኖች መሆኑን ያውቃሉ፤ ነዳጅ ማደያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ወዘተ የመሳሰሉ ተቋማት አድማ ማድረግ የማይችሉ መሆኑ በህግ መደንገጉንም ያውቃሉ። ይሁን እንጂ አንዴም ስለአድማው ህጋዊነት አላነሱም። ጃዋር አሰማርቼያቸዋለሁ የሚላቸው ቡድኖች ህዝቡ ሱቁን እንዲዘጋ የሚያደርጉትን በማስፈራራት መሆኑ ይታወቃል። በጅማ ከተማ የአድማውን ጥሪ ችላ በማለት በተከፈቱ ሱቆች ላይ የተፈጸመው የእጅ ቦምብ ጥቃት ለዚህ አስረጂ ነው። ይህ ሁኔታ የቪኦኤን ጋዜጠኞች በአድማው አጋፋሪነት እንድንጠረጥራቸው ያደርገናል። ይህን ድርጊት መንግስታቸው እንዲያጤነው ማደረግም አስፈላጊ ይመስለኛል።
እርግጥ ይህ አጋፋሪነት እዚያ አሜሪካ የሚኖሩ ጥቂት ግለሰቦችን ጭብጨባ ሊያስገኝላቸው ይችላል። እዚህ ሃገር ቤትም አድማውን ተስፋ ያደረጉ ጥቂት ቡድኖችንና ግለሰቦችን ሊያስደስት ይችል ይሆናል። አብዛኛው ተገዶ ሱቁን ዘግቶ እቁብ የሚጥለው ገንዘብ ያጣ ነጋዴ ግን በበጎ እንደማይመለከታቸው ግልጽ ነው። መኪናውን የገዛበትን የባንክ ብድር ለመመለስ ከንጋት እስከውድቅት እየተራወጠ የሚሰራ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ እንደባለጋራ የሚመለከታቸው መሆኑም እንዲሁ ግልጽ ነው። እንዲያው ለትዝብት ያህል አነሳኋቸው እንጂ የቪኦኤ ጋዜጠኞች ይህን ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው አይደለም። ጋዜጠኘነታቸው ነጥፎ የሁከት አጋፋሪነት ከለማባቸው ከራርመዋል።
ወደዋናው ጉዳይ ልመለስ። የሃይማኖት አክራሪነትም ይሁን የጠባብ ብሄረተኝነት ሳይመርጥ ሁከት ሊያስነሳ የሚችል ማንኛውንም አጀንዳ በመለቃቀም የሚታወቀው ጃዋር መሃመድ፣ ልክ እንደእርሱ በእውቀት ሳይሆን በጭፍን ስሜታዊነት ታውረው የሚንቀሳቀሱ አፍላ ወጣቶች በከተሞች አድማ እንዲያስፈጽሙ ትእዛዝ አስተላልፏል። ጃዋር እነዚህን በድንጋይ፣ በስለት፣ በእጅ ቦምብ . . . በከተሞች አድማ እንዲያስፈጽሙ ያሰመራቸውን ወጣቶች ቄሮ የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል። ቄሮ የኦሮሚኛ ቃል ነው፤ ቄረንሳ የሚለው ቃል የቁልምጫ አጠራር። ቄረንሳ ድግሞ ነብር ማልት ነው። የቄሮ የአማርኛ አቻ ቃል ነብሮ የሚለው ነው።
ጃዋር፣ ቄሮ ወይም ነብሮ የሚለውን ስያሜ ያለምክንያት አልመረጠውም። ኦነግ ቅድመ 1983 ዓ/ም በትጥቅ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት፣ ከዚያም በኋላ የሽግግር መንግስቱን አሻፈረኝ ብሎ የትጥቅ ትግልን በመረጠበት ወቅት የሚመካበት ምናልባት ከአንድ ሻለቃ የማይበልጥ ቄረንሳ የተባለ ሃይል ነበረው። ይህ የኦነግ ሃይል በኋላ እንደድርጅቱ ከመበታተን ባይተርፍም፣ የኦነግ መመኪያ ነበር። በተለይ በዚያን ወቅት የነበሩ አፍቃሪ ኦነግ ወጣቶች የአሁን ጎልማሶች ልብ ውስጥ የቀረ ስያሜ ነው። ቄሮ ያኔ የፈጸመውም፤ ያልፈጸመውም ጀብድ ተደበላልቆ የሚነገርለት የበርጫና የመሸታ ቤት ጫወታ ማድመቂያ ነበር። አሁን ጃዋር ያነሳው ይህ ቄሮ የሚል ስያሜ፣ የኦነግን መንኮታኮት ተከትሎ የበርጫና የመሸታ ቤት ማድመቂያ ሆኖ የቀረን ስያሜ ነው።
ይሁን፤ ጃዋርና ተባባሪዎቹ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች ከነሃሴ 17፣ 2009 ዓ/ም ጀምሮ ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኝነት የተሰኘ የስራ ማቆም አድማ አውጀዋል። አድማው የታወጀው በመላው የኦሮሚያ ከተሞች ነው። ይህን ጃዋር በተባለ አንድ ግለሰብና የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች የታወጀ አድማ ያስተላለፉት በዋናናት የኤርትራ መንግስት ማህበራዊ ሚዲያዎች ናቸው። የአድማው ቀዳሚ ዓላማ በማደግ ላይ ነው የሚባለውን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በመሸርሸር እድገቱን መግታት መሆኑን ጃዋር ተናግሯል። የኢኮኖሚ እድገቱ መገታት መንግስትን ያዳክመዋል ባይ ነው ጃዋር። ከዚሁ ጋር መንግስትን በማስገደድ ምላሽ እንዲሰጥባቸው ያላቸውን ጥያቄዎቸ አቅርቧል።
እርግጥ ነው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ተከታታይ እድገት አስመዝግቧል። ይህን ለመረዳት የአርሶ አደሩ ኑሮ የነበረበትንና አሁን ያለበትን መመልከት በቂ ነው። በሃገሪቱ የተስፋፉት የትራንስፖርትና የሃይል መሰረተ ልማቶች፣ የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ ወዘተ እድገቱን የሚያረጋግጡ ቋሚ ምስክሮች ናቸው። አምና ጃዋር ጠርቶት በነበረው ሁከት ኦሮሚያ ውስጥ ጉዳት የደረሰባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች ባለፉ አስራ አምስት ዓመታት የተቋቋሙ ናቸው።
እርግጥ ነው ይህን እድገት መግታት መንግስት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተዋቀረ መንግስት ጠንካራ ነው። የደሃ ሃገር መንግስት ደግሞ ደካማ ነው፤ ህግ የማስከበር፣ ሃገርን ከጠላት ጥቃት የመከላከል፣ በልማት የህዝቡን ኑሮ የማሻሻል አቅም የሌለው ደካማ። ታዲያ የሃገር ድህነት የሚገለጸው በህዝቡ ኑሮ ነው። የአንድን ሃገር ኢኮኖሚ እድገት መግታት ወይም እንዲያሽቆለቁል ማድረግ የህዝቡን ኑሮ ወደድህነት እንዲያሽቆለቁል ከማደረግ የተለየ ውጤት የለውም። በመሆኑም ጃዋር መንግስትን የማዳከም ውጤት አለው በሚል ስሌት የወጠነው ኢኮኖሚውን የማዳከም ፍላጎት እንማይሳካ እርግጠኛ ቢሆንም፣ መድረሻው ግን ህዝብን ማደህየት ነው። እናም ኢኮኖሚውን ይሸረሽራል በሚል ግምት የታወጀው አድማ በህዝቡ ኑሮ ላይ የታወጀ መሆኑ መታወቅ አለበት።
ይቀጥላል