ኖርዌይ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና አየር ንብረት ለውጥ የሚውል የ1 ነጥብ 74 ቢሊዬን ብር ድጋፍ ለኢትዮጵያ ለገሰች፡፡
ድጋፉ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለምታከናውናቸው ሥራዎችና በቀጣይ 4 ዓመታት በሀገሪቱ ለሚተገበረው የኢትዮጵያና ኖርዌይ የአየር ንበረት ለውጥ የአጋርነት ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል ነው፡፡
ፕሮግራሙ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ የሚያስችሉ ሥራዎች የሚከናወኑበት ሲሆን የደን ሽፋን መመናመንና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
በዚህም በደቡብ፣ በጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች 66ዐ ሺ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ይከናወናል፡፡
በተመሳሳይም በአማራና ትግራይ ክልሎች ላይ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ የሚያስችል የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችም ይከናወናሉ ተብሏል፡፡
ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ በፕሮግራሙ 75 ሺ አባወራዎችና እማወራዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀዋል፡፡