Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አረንጓዴ ልማትና ፋይዳው

0 622

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አረንጓዴ ልማትና ፋይዳው

                                                              ዘአማን በላይ

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመከተል በግንባር ቀደምትነት ዓለም አቀፋዊ  ኃላፊነቷን እየተወጣች ያለች ሀገር ናት። ሀገራችን በዚህ የኃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ ያተረፈችው ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ከራሷ አልፎ አፍሪካን ጭምር ያኮራ ነው። በተለይም ሁሌም በድርቅ አደጋ የምትጠቃው አፍሪካ ያለ አንዳች አስተዋፅኦዋ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ መሆኗን በመከራከር የምዕራባዊያንን ሀገሮች ጭምር ማስደመም የቻለች ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ። በዚህ ፅሑፌ ላይ ስለ አረንጓዴ ልማት ምንነትና ፋይዳ በመጠኑም ቢሆን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመንደፍ ለታዳሽ ሃይል ትኩረት የሰጠች ሀገር ነች። የኃይል ልማት ፖሊሲው ከነባሩ ወይም ባህላዊ መንገንድን ተከትሎ ከሚደረገው የሃይል ማመንጨት ስራ ቀስ በቀስ ዘመናዊ የሃይል አጠቃቀም መከተልንና መሸጋገርን ማዕከል ያደረገ ነው።

አስተማማኝ የሃይል አቅርቦትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም የማዳረስና ለኢኮኖሚውም ዕድገት በቂ ሃይል የማቅረብ ሃሳብንም የያዘ ነው።  ፖሊሲው ለሀገር ውስጥ የሃይል ምንጭ ቅድሚያ በመስጠት ራስን መቻልን ያልማል። እንዲሁም ንፁህ ሃይልን ቆጥቦ በብቃት በመጠቀም የአካባቢ የአየር ሁኔታ ጤናማነትን በማስቀጠል የበኩሉን ሚና ለመጫወት ያለመ ነው።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ባልተራዘመ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ ራዕይ አላት። የኢትዮጵያ መንግስትና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ በተከታታይ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ያላት የኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር ሆኖ እንደምትቀጥልም አየተነበዩ ነው፤ ሁሌም በየዓመቱ።

ይህን ስኬታማ ለማድረግ የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ልማቱ መሰረት ማድረግና የኤክስፖርት ደረጃን ለማሳደግ ታስቦም እየተሰራ ነው። ውጤትም እየተገኘ ነው። ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ ራዕይዋን እውን ማድረግ የሚቻለውም  ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ፈተና ሆኖ የተጋረጠውን የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት መዋጋትና ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ሲቻል መሆኑ ከግንዛቤ እንዲገባ ተደርጎ ስራው በመከናወን ላይ ይገኛል።

የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ሃብት እጥረት ነዳጅን በማስገባት በሚወጣ የውጭ ምንዛሬ ምክንያት የሚመጣ የተፈጥሮ ክስተት ነው። ይህ ክስተት በተለይ ልማታቸውን በተፈጥሮ ዝናብ ላይ ጥገኛ ያደረጉ ሀገሮችን የሚጎዳ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።

በዚህ ስትራቴጂ የሚወሰዱ ርምጃዎች ሁሉ ለኢንቨስትመንት አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጡና የኢኮኖሚ ዕድገትን በቀጥታ ከሚያፋጥኑ ከተጨማሪ እሴቶች ጋር የስራ ፈጠራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስትራቴጂው የዓለም የሙቀት መጠንን በመቀነስ ረገድ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ሃላፊነቷን እንድትወጣ የሚያስችል ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የስራ ዕድልን ይፈጥራል።   

ርግጥ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ኢትዮጵያ በቀጣዩቹ ዓመታት 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋታል። ታዲያ ይህን ግብ ለመድረስ በሁለትዮሽ ግንኙነት አማካኝነት ከሚካሄዱ የዲፕሎማሲ ስራዎች፣ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ እንዲሁም የግሉ ሴክተር ከሚጫወተው ሚና ጋር ተገናዝቦ ገቢራዊ እየሆነ ነው። እንዲሁም ሀገሪቱና አህጉሪቱ ለአለም አየር ንብረት ለሚያደረግት የታዳሽ ሃይል ስራዎች በጎ አስተዋጽኦ ማካካሻ የገንዘብ ድጋፎች ታሳቢ ሆነው ይቀርባሉ።

ያም ሆኖ እዚህ ላይ ‘ለኢትዮጵያታዳሽ ሃይል ለምን ያስፈልጋታል?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ይህም የአረንጓዴን ልማት ስትራቴጂ ፋይዳ የሚያመላክተን ይሆናል።  በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉት ሀገራት ውስጥ ቻይናን እና ህንድን ብቻ ብንወስድ፤ እያንዳንዳቸው ከዚህ በፊት የዓለም ፍጆታን በሞኖፖል ከያዘው ክፍል በእጥፍ የሚበልጥ ህዝብ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሀገሮች በፍጥነት እያደጉ በሄዱ ቁጥር የተፈጥሮ ሃብት ምርቶች ፍላጎታቸው በዚያው ፍጥነት አድጓል።

ርግጥ በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተኪ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ማፍራት የሚቻል ቢሆንም፤ የተፈጥሮ ሃብትን ሙሉ በሙሉ መተካትና ህዝቦች ያላቸውን ፍላጎት በፍጥነት መቀነስ ግን አይቻልም። እናም አዳዲስ የኢኮኖሚ ማዕከሎች እየተፈጠሩ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ የተፈጥሮ ሃብት ምርቶች በተለይም የማዕድናትና የግብርና ምርቶች ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይህም የተፈጥሮ ሃብት ተፈላጊነቱ እየጨመረ እንጂ እያነሰ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታም የተፈጥሮ ሃብት እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም። የዓለም የተፈጥሮ ሚዛን ክፉኛ ሊናጋም ይችላል። እናም የተፈጥሮ ሃብትን በከፍተኛ መጠን ለመቆጠብ የሚያስችሉ እንደ የታዳሽ ሃየል ምንጮችን መፍጠር የግድ ይላል።

ታዳሽ ሃይልን መጠቀም በአየር ጠባይ ለውጥ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው።  ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ የሚከተሉት የዕድገት አቅጣጫ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ኢነርጂ አላቂ ከሆኑት የካርቦን ኬሚካሎች በማመንጨት ላይ የተመሰረተ ነው። እነዚህ የሃይል አማራጮች አላቂ ከመሆናቸውም በላይ የሚለቁት ካርቦንዳይአክሳይድ መጠን አየር ላይ እየተከማቸ የመሬትን ሙቀት ይጨምራል።

ይህም አሁን ባለው ልኬት መሰረት የካርቦን መጠኑ የዓለምን ሙቀት ቢያንስ በአማካይ ሁለት ዲግሪ ሴንቲግሪድ እንዲጨምር ያደርገዋል ተብሎ ይገመታል። በዚህ ሳቢያም በሰሜንና በደቡብ ዋልታዎች የተከማቸው ከፍተኛ ቦረዶ ኮረብታዎች ይቀልጣሉ። በዚህም ሳቢያ ውቅያኖሶችም ከአንድ እስከ ሶስት ሜትር እንዲጨምሩ ያደርጋቸዋል። ይህም መላው ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ሀገሮችን የአየር ንብረት በመለወጥ ለድርቅ ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ አህጉር ምንም እንኳን በኢንዱስትሪ ከበለፀጉት ሀገራት ጋር እኩል ካርቦንዳኦክሳይድ በመልቀቅ በአየር ንብረት ላይ አሉታዊ ሚና ያላት ባይሆንም፤ በሚደርሰው የአየር ንብረት ብክለት ግን ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ እየሆነች ነው።

በተለይም የአየር ንብረቱን ለመቀጣጠርና ሚዛናዊ ለማድረግ የሚጠቅሙትን ደኖች በመጨፍጨፍ ለተለያዩ ሃይል መጠቀሚያነት እንዲውሉ ማድረግ አህጉሪቱን በድርቅ አደጋ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት ነው። በሀገራችን በየጊዜው የሚከሰተው የድርቅ አደጋ የዚህ እውነታ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። እናም ኢትዮጵያ ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይና ከስኳር ተረፈ ምርቶች እንዲሁም ከጂኦተርማል ታዳሽ የሃይል ምንጮች ሃይልን በማመንጨት የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር የወሰነችው ከዚህ በመነሳት ነው።

ኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይልን በማመንጨት ከራስ ፍጆታ በላይ የሆነውን ለሌሎች ሀገራት ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማግኘት ይቻላል። ከዚህ ባሻገር ታዳሽ ሃይል በአረንጓዴ ልማት ላይ ያለውን ሚና በመመርኮዝም በአየር ፀባይ ለውጥ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው።

በዚህ ተግባሯም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው። የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን የሚያከናውን መስሪያ ቤትን በሚኒስቴር ደረጃ አቋቁማ እየሰራች ነው። ይህመ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ሀገር እንድትሆን አድርጓታል።

የአካባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የእንስሳትና የሰብል ምርታማትን በማሳደግ፣ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፣ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ደንን በመጠበቅና በማልማት፣ ከታዳሽ ኃይል ምንጭ የኤሌክትሪክ ኃይል በሰፊው በማመንጨትና ዘመናዊና ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በትራንስፖርት፣ በኢንዱስትሪና በህንፃ ኮንስትራክሽን ዘርፎች በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አስፈላጊ ርምጃዎች አስቀድመው ካልተወሰዱ እ.ኤ.አ. እስከ 2050 ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 7 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እስከ 2 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይጨምራል ተብሎ ይገመታል። ይህ የሙቀት መጠን መጨመር የምግብ ዋስትና እንዳይረጋገጥ፣ እንደ ወባ፣ ትኩሳትና ኮሌራ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዲከሰቱ፣ የመሬት መጎሳቆልና የመሠረተ ልማት ውድመት እንዲፈጠር ሊያደርግ እንደሚችልም ይታሰባል። እናም ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ልማት መገንባት ለኢትዮጵያ ፋይዳው ሁለት ነው። ቀዳሚው ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ታሳቢ ሀገራዊ ችግሮችን መቋቋም ሲሆን፤ ለጥቆም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቷ ላይ የወደቀ ይሆናል ማለት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy