አዋጁ የህዝቡን ጥያቄዎች ለማዳመጥና ለመመለስ አስችሏል!
ደስታ ኃይሉ
ላለፉት አስር ወራት በአገራችን ውስጥ ስራ ላይ እንዲውል ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተተገበረና ከተነሳ በኋላ ህዝቡ፣ በተለይም ወጣቶች ያነሱት የነበረውን ህጋዊ ጥያቄ በአግባቡ ለማዳመጥና አዳምጦም ምላሽ ለመስጠት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ጥያቄው የተመለሰለትና እየተመለሰለት ያለው ህዝብ ደግሞ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለሁከትና ለብጥብጥ ሊነሳ አይችልም። ሆኖም አንዳንድ ዕንፈኞች የአዋጁን መነሳት ተመርኩዘው በቀቢፀ-ተስፋ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ። ይሁንና ይህ ፈላጎታቸው ሰላም ፈላጊውን ህዝብ ያላማከለ በመሆኑ ሊሳካ የሚችል አይደለም።
አዋጁ ገቢራዊ በነበረበት ጊዜ ውስጥ የተገኙት ሰላምን ዕውን የማድረግና የህዝቡን ዕለታዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎችን የማይፃረሩ ድርጊቶችን የመከላከል ብሎም አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ አማካኝነት ሀገራችን ወደ ምትታወቅበት የሰላም ተምሳሌትነታችን ተመልሰናል።
እንኳንስ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውና ላለፉት 26 ዓመታት የተገኘውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶች በማናቸውም ሳንካዎች እንዳይደናቀፉ በሚሻ ህዝብ ባለበት ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ቢሆን ይህን መሰሉ የህዝቡን ሰላም የሚያረጋግጥ አዋጅ ተፈፃሚ መሆኑ አይቀርም።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህዝቡ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉትን ብዥታዎች ለማጥራት አስችሏል። አዋጁ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ በህዝቡ ድጋፍ እየፈጠረ ያለው የሰላም ድባብ ስላበሳጫቸው በአዋጁ ዙሪያ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ቢያራምዱም ህዝቡ ይህን ሳይሰማ ለአዋጁ ድጋፍ ሰጥቷል።
እርግጥ የየትኛውም ሀገር ህዝብ ሁሌም ከማናቸውም ተግባር በፊት ግራና ቀኝ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን የሚያጤን እንዲሁም የአካሄዶቹን አሉታዊና አዎንታዊ ጎን በመገንዘብ ሚዛናዊ ውሳኔ የሚሰጥ ነው። የሀገራችንም ህዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው ሀገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሆኑን ስለሚያውቅ፤ ሁሌም ሰላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆም ነው።
የሰላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ከምንግዜውም በላይ በየአካባቢው ለሰላሙ ዘብ እንደቆመ ነው። ባለፉት አስር ወራቶች ከኮማንድ ፖስቱና ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ያከናወናቸው ሰላምን የማረጋገጥ ተግባሮች የዚህ እውነታ አረጋጋጭ ናቸው።
በእነዚያ ወራቶች ህዝቡ የየቀየውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ ዋነኛ መሰረት ሆኗል። የቀየው ለሚከሰት ማናቸው የፀረ ሰላም ሃይሎች ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን መሆኑን ስለሚያውቅ ለሰላሙ ተግቶ ሰርቷል።
የአገራችን ህዝብ ከሰላም ምን ሊገኝ እንሚችል ባለፉት 26 ዓመታት፣ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በሚገባ ተገንዝቧል። ሰላሙ የልማቱ፣ ሰላሙ ዕድገቱ፣ ሰላሙ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ሀገር በቀል በሆነ መንገድ ስር እንዲሰድ መሰረት መሆኑን በሚገባ ያውቃል።
ይህ ህዝብ ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ ነው። ወጣቶችን ከጥፋታቸው የመመለስ፣ የተሃድሶ ትምህርት ከወሰዱም በኋላ ወደየቀያቸው ሲመለሱ ምክርና ተግሳፅ በመስጠት እንዲሁም ወጣቶቹ የየአካባቢያቸውን ሰላም በኃላፊነት ስሜት እንዲጠብቁ አድርጓል። ታዲያ ይህ የህዝቡ ስሜት መነሻው ከምንም የተነሳ አይደለም— የሰላምን እሴት በምንም ሊለካው እንደማይችል ያለፉት ተጨባጭ የኑሮ ውጣ ውረዶቹን በሚገባ ስለሚገነዘብ እንጂ።
‘ከህይወት ተሞክሮ የተሻለ ትምህርት ቤት የለም’ እንደሚባለው፤ ህዝቡ ላለፉት አስር ወራቶች የሰላሙ ዘብ ሆኖ መቆሙ ትክክልም ተገቢም ነው። ሁከቱን ለመቀልበስ በሀገራችን የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስፈጻሚው አካል ታውጆ ተግባራዊ በሆነበት በእነዚያ ወራቶች የህዝቡ ሚና የማይተካ ነበር። እናም በአስሩ ወራት ውስጥ በሀገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ በማድረግ ረገድ ህዝቡ የላቀ ተግባር አከናውኗል።
ህዝቡ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት የተራመዳቸው ተስፋ ሰጪ መንገዶች እንዲሁም አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ ዛሬ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ በማድረግ መግለፅ የሚችል ነው።
የሀገራችን ህዝብ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ በተከናወኑት ልማት ተግባራት ራሱ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ሀገሩም በልማቱ መስክ የአፍሪካ ተምሳሌት ሆናለች። የቀጣናውን ሀገራት በልማት ለማስተሳሰር በምታደርገው ጥረት ተጠቃሽ መሆኗንም ያውቃል። በአረንጓዴ የልማት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተችም እንደሆነ ይገነዘባል።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም እያስከበረችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት እንዳላትም ይረዳል። ይህ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቁመናችን እንዳይሸራረፍም ሰላምን በፅኑ እንደሚሻ እሙን ነው። ባለፉት አስር ወራቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ገቢራዊ ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የዚህ እውነታ ማሳያ ነው።
ይህ አገራችን ሰላም መረጋገጥ መሰረቱ ህዝቡ መሆኑ አይካድም። በዚህም ሳቢያ ባለፉት አስር ወራቶች የሀገራችን ሰላም በመደበኛው ህግ ሊፈቱ ከሚችሉ ጥቃቅን ጉዳዩች ውጪ በአብዛኛው ወደ ነበረበት የተመለሰው ህዝቡ ለሰላም ካለው የማይናወጥ ፍላጎት የመነጨ ነው።
ሰላምን በፅኑ የሚሸው የሀገራችን ህዝብ ደሙን ዋጅቶና አጥንቱን ከስክሶ ያመጣው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገድ እንዳይደናቀፍ እንዲሁም የኋሊት እንዳይቀለበስ አይፈቅድም።
ከዚህ በላይም ህዝቡ ቀደም ሲል ያነሳቸው የነበሩት ጥያቄዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተመለሱለት ስለነበሩ ጠቀሜታውን በሚገባ ይገነዘባል። በወቅቱ የወጣቶች ህጋዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ መፈታቱ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘቱና ከህዝቡ ጋር በመሆን እርምጃ መወሰዱን ህዝቡ ያውቃል። እናም በወቅቱ እነዚህና ሌሎች የህዝቡ ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ በዳመጥና ምላሽ በመስጠት ረገድ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ስለነበርም በዚያን ወቅት የተገኘውን ጠቀሜታ ስለሚረዳ ለአዋጁ ተግባራዊነት ድጋፍ አድርጓል።