Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አይነፋም፤ የልብ አያደርስም

0 384

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አይነፋም፤ የልብ አያደርስም

ስሜነህ

ሰሞኑን በከተማችን አዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ በተለይም በወጣቱ ዘንድ “አይነፋም” የሚል  ወቅት አፈራሽ ቃል/ምላሽ መስማት ከመለመድም አልፎ የበርካቶች መግባቢያ በመሆን ላይ ይገኛል። “አይነፋም” የሚነገረው፣ የሚሰማው ጉዳይ ከሚጠበቀው ውጤት ጋር አልሰምር፤ አልጥም  ሲል የሚሰነዘር የቅሬታ ቃል/የሚሰጥ ምላሽ በመሆኑ እኔም እዚህ ልጠቀምበት ፈቀድሁ፤ አይነፋም

መንግስት ጉዳዩን አንድ ብሎ ካሳወቀበት ጊዜ ጀምሮ የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ምህዳሩን አስፍቶ፤ ምንጠራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ስልቱን የቀየረው ይህ አገር አቀፍ ዘመቻ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ (fake degree) ባለቤቶችም ጡንቻውን በማሰረፍ ላይ ይገኛል። በያንዳንዱ ክልል እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ይህ ነው የማይባል ቁጥር ያለው (የተማረ፤ የተመራመረ?) ሃይል በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው።

በህገ መንግሥታችን አግባብ የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልፅ መሆን አለበት። ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ወይም የህዝብ ተመራጭ ጥፋት ፈጽሞ ሲገኝ ከሃላፊነቱ እንደሚነሳና ተጠያቂ እንደሚሆን ሁሉ የትኛውም ዜጋ በሃሰተኛ ሰነዶች ሲጠቀም በማታለል ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ተደንግጓል። የዚህኛው አይነት የማታለል ወንጀል ደግሞ የከፋ የሚሆነው ባልተማሩትና በማያውቁት ሙያና መስክ ህዝብን ለማገልገል መሻታቸው ነው። ይህ ሁሉ የመልካም አስተዳደር ችግር፤ ይህ ሁሉ ህዝብን ማንገላታት ሲፈጠር የነበረው ለካንስ በማይመጥናቸው ቦታ ላይ ተቀምጠው ሲቀልዱ የነበሩ እንደዚህ አይነቶቹ ስለነበሩ ነው። በተለይ ከአማራና ከደቡብ ክልሎች የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በየክልሉ ከተሞች ላይ ብቻ ያለደረጃቸው በሃሰተኛ ሰነዶች ህዝብን ሲያንገላቱና ሲያመናጭቁ የኖሩት ሃይሎች እጅግ በጣም የበዙ ናቸው።

በአጠቃላይ ስልጣን የሚመነጨውም ሆነ ጥቅም ላይ የሚውለው ከህዝብና ለህዝብ የመሆኑን ያህል የመንግስት ሰራተኝነትም ህዝብን ለማገልገል እንጂ ባልተፈጠሩበት ገብተው መፈትፈት አይደለም። ማንኛውም ባለስልጣን ከህዝብ በታች መሆኑንና ጥፋት መፈጸሙ በማስረጃ ሲረጋገጥበትም ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጥ ሁሉ የትኛውም ፈጻሚ ባጠፋው ጥፋት ልክ ምሱን ማግኘት ይገባዋል። የማይችሉትን እችላለሁ ብለው ህዝብን ሲያስለቅሱ የኖሩ ሃይሎች ጥፋት በቀላሉ ሊታይ የማይገባው ነው። እኒህ እኮ ተምረውም ቢሆን በአመለካከት የላሸቁ ስለሆነ ለመገመት ይከብድ የነበረ ዘረፋ ውስጥ ተነክረው የሚገኙ የነበረ መሆኑ አያጠያይቀንም።  

የመንግሥትን እና የህዝብን ሃብትና ንብረት ያላግባብ በመመዝበር የተጠረጠሩ ባለስልጣናት እና ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የሚውሉበትና ለህግ የሚቀርቡበት ሁኔታ ታይቷል። ወደፊትም ይኸው ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ቢባልም ግን በፌደራል ደረጃ እዚያው 52ቱ ላይ ቸክሎ ከሳምንት የዘለሉ ቀናትን ማስቆጠሩ ጉሩምሩምታ እየፈጠረ ነው ።

52ቱ ላይ ተመስርተን ነገሩን ያየን እንደሆነ እነዚህ ተጠርጣሪዎችና ከተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር በዘረፋ የተጠረጠሩ ባለሃብቶችም ይሁኑ የንግድ ኩባንያዎች ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ በተግባር እየተረጋገጠ መጥቷል። ግን፣ አራዶች እንደሚሉት አይነፋም። በአዲስ አበባ ከመሬት ጋር ተያይዞ ከገቢዎችና ጉሙሩክ ጋር በግልጽ የምናውቃቸው በርካታ ጉዳዮች እያሉ በውስን ተቋማት እነዚህን ክልሎችን እንኳ ስናያቸው የፌደራላችን የዘመቻ ጉዳይ አይነፋም።

በደቡብ ክልል በ2009 ዓመተ ምህረት ከሙስና እና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው 413 ናቸው። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደዘገበው ክስ መመስረት ብቻ አይደለም በተከሳሾች ላይ እስከ 17 ዓመት የሚደርስ ፅኑ የእስራት ቅጣት መተላለፉንም የክልሉን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል። በክልሉ 291ሚሊዮን 299ሺህ 512 ብር ከምዝበራ ማዳን መቻሉን የሚገልጸው ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት የተመዘበረው ገንዘብ  እንዲመለስ የተደረገ፤ በተለያዩ ጥቆማዎችም የቅድመ መከላከል ስራ መስራት የተቻለ መሆኑንም አመልክቷል። ከሙስና ጋር በተያያዘ መኖሪያ ቤቶች፣ ባለ ሁለት እና ባለ አራት ወለል ህንፃዎች፣ ፔኒሲዮን፣ ጥሬ ገንዘብ እና ተሸከርካሪዎች መታገዳቸውንም በተመሳሳይ። ከገንዘብ ባሻገር በገጠር 10ሺህ ሄክታር እና በከተማ 1ሚሊየን ካሬ ሜትር መሬት ተመላሽ ተደርጓል፡፡

አሁን ደግሞ የፌደራላችን የጸረ ሙስና ዘመቻ ሆድ አይነፋም ያልንበትን ምክንያት ተገቢነት ለማጠየቅ ወደአማራ ክልል ሄደን አንዳንድ አብነቶችን እናንሳ።

በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በህዝብና በመንግስት ሃብት ላይ የሙስና ወንጀል የፈፀሙ  320 ግለሰቦች እስከ 14 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የክልሉ የስነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ማስታወቁን የተመለከቱ ዘገባዎች አረጋግጠዋል። በስልጣን መባለግ፣ ደንብና መመሪያ በማይፈቅደው መሰረት ግዠና ጨረታ መፈፀም፣ በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ መጠቀም፣  ግለሰቦቹ ከተከሰሱባቸው ወንጀሎች መካከል  ጥቂቶቹ ናቸው።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ ግለሰቦቹ በሙስና ያካበቱት 16 ነጥብ 5ሚሊዮን ብርም ለመንግስት ተመላሽ እንዲሆን፤ 1ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ እንዲመለስ መደረጉን የገለፁት ኮሚሽነሩ 9ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታ፣ 186 የመኖሪያ ቤቶች፣ ዘጠኝ ድርጅቶችና 17 ተሽከርካሪዎች ደግሞ ጉዳያቸው እስኪጠራ እንዲታገዱ ተደረጓል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል በተሰራ ስራ ሊመዘበር የነበረ 16 ነጥብ 2ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና 2ሺህ 100 ካሬ ሜትር ቦታ ማስቀረት የተቻለ ሲሆን፤ በተጨማሪም በባህር ዳር ከተማ በተጋነነ የጨረታ ዋጋ ሊገዙ የነበሩ 12ሺህ 300 የውሃ ቆጣሪዎችን ጨምሮ ሌሎች አግባብ ያልሆኑ የግንባታ ጨረታዎች እንዲቋረጡ  ተደርጓል።

በኦሮሚያና በትግራይስ? የሚሉ ጥያቄዎችን ከማስነሳት አልፎ በፌደራል ከተማችን ከመሬት ወረራና ከህገወጥ ቤቶች ጋር ተያይዞ ችግር የሌለ ይመስል እስካሁን ያየነውም ሆነ የሰማነው ነገር የሌለ መሆኑ ዘመቻውን አይነፋም (የልብ አያደርስም) እንድንለው ያስገድደናል። ከላይ በተመለከተው አግባብ በገጠር ያ ሁሉ ሄክታር እየተወረረ በአዲስ አበባ ስንቱ በመሬት ወረራ የሃብቶች ማማ ላይ እንደተሰቀለ እያወቅን 52ቱ ቀጥ  ማለቱ አይነፋም።

ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም በመንግስትና በህዝብ ኃብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ መደረጉ በአገራችን የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ስርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገንባቱ ዓይነተኛ ማሳያ ነው። በሌላ በኩል ተፈጽመዋል የተባሉ የሙስና ወንጀሎችን በዝርዝር በማጥናት እና በማጣራት ረዘም ያለ ሂደት እንዲያልፉ መደረጉም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይሸራረፉ የተደረገውን ጥንቃቄ አመላካች ነው። ያም ሆኖ ግን ከላይ በተመለከተው አግባብ ክልሎቹ በዚያው በተመለከተው አግባብ ዘመቻውን እያፋፋሙና ውሳኔውንም እያቀላጠፉ ሳለ በአዲስ አበባና በፌደራል ደረጃ እያየንም ሆነ እየሰማን ያለውን ሁኔታ አይነፋም ከማለት ሌላ እንድንል አያበረታታንም።

የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ከምንጩ ማድረቅ የምንችለው በአቋራጭ መበልፀግን የሚፀየፍ እና በምትኩም ልማታዊ አስተሳሰብን በተሟላ አኳኋን የሚቀበል ህብረተሰብ መፍጠር ስንችል ነው። ይህ ሲሆን ብቻም ነው ለዘላቂ ድል የምንበቃው። የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም የሚባለውም በዚሁ ምክንያት መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል። ጉዳዩ የተዛባ አመለካከትን የመለወጥ እና ልማታዊ አስተሳሰብን የመገንባት ሂደት እንደመሆኑ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ አያጠያይቅም።  ያም ሆኖ ግን ከጀመሩት ኋላ ላይ ላዩን መሄዱ ለሌላ ቅልበሳ አማራጭ መንገዶችን መስጠት ከመሆኑም በላይ የዘመቻው አካል እንዲሆን በትልቁ የሚጠበቀውን ህዝብ ከጥርጣሬ ላይ ስለሚጥለው በፌደራል ደረጃም የሚያረካ (የሚነፋ) ተግባር በመፈጸም በእርግጥም መንግስት ህዝባዊ ወገንተኝነቱን እንዲያረጋግጥልን እንጠብቃለን።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy