አደገኛው ነገር የፖለቲካ ሙስናው ነው
ስሜነህ
34 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ግብረ አበሮቻቸውን በቁጥጥር ስር በማዋል የተጀረው የጸረ ሙስና ዘመቻ ወደ 51 መድረሱን መንግስት ይፋ አድርጓል። እነዚህን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ እንደተጀመረ በኢፌድሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በሰጡት መግለጫ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ለረጅም ጊዜ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን፤ ተጠርጣሪዎቹንም በቁጥጥር ስር ወደ ማዋል መሸጋገሩን አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ መግለጫቸው በከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጠው ከደላሎችና ከባለሀብቶች ጋር በማበር የህዝብን ገንዘብ ያለ አግባብ ሲጠቀሙ የነበሩ ግለሰቦችን ተከታትሎ ከመያዝ አኳያ ስራው መጀመሩን ይፋ ካደረጉ በኋላ ጉዳዩ የሃገር መነጋገሪያ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
ዶክተር ነገሪ ካሁን በፊት በአገሪቱ ይስተዋሉ የነበሩ ከሙስና ጋር የተያያዙ የፍርድ ሂደት መጓተቶች እንዳይኖሩ የመረጃ ዝግጅቶችና ተገቢው ቅድመ ሁኔታ መደረጉን የገለጹ ሲሆን፤ መንግስት ከጥልቅ ተሃድሶ በፊት ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ ከፍተኛ የሙስና ችግሮች መኖራቸው እና በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የአመራር አካሉ አልተነካም የሚሉ ቅሬታዎች ሲነሱ መቆየታቸው ይታወሳል። የዚህ ፅሁፍ መነሻም እርምጃውን እና የቅሬታውን ተገቢነት ማጠየቅ ነው።
ከላይ ስለተነሳው ቅሬታ በምክንያትነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል በሃገሪቱ ሥር ለሰደደው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ምንጩ የኪራይ ሰብሳቢው ኃይል “ልዩ ችሎታና” ጥንካሬ ሳይሆን የመንግስትና የፓርቲ ስልጣንን በመጠቀም ለኪራይ ሰብሳቢው ኃይል የሚደረግ የበላይ ጠባቂነት ነው የሚለው አንዱና ዋነኛው ነው። የኪራይ ሰብሳቢው ኃይል በሚደረግለት የቅርብ የበላይ ጠባቂነት ድጋፍና እገዛ እንዲሁም ከአመራሩ ጋር በጥቅም በማስተሳሰርና በመሞዳሞድ፣ ራሱን ወደ ከበርቴ መደብ በመቀየር፣ በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት በመፍጠር ከኢኮኖሚውም አልፎ ፖለቲካውን ሙሉ በሙሉ ለመዘወር ፍላጎት ያለው ኃይል በሥርዓቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ይገኛል የሚሉ አስተያየቶችም እየተደመጡ ነው። ይህንኑ ሰሞንኛውን አጀንዳ በተመለከተ ይህ ጸሃፊ ባደረገው የቀጥታ ስልክ የሬዲዮ ውይይት ላይ ከቀረቡ አስተያየቶች መካከልም ከላይ ለተመለከተው ቅሬታ አስረጅ የሚሆን ነጥብ ተነስቷል።
ይኸውም ከስኳር ኮርፖሬሽን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙን ግለሰቦች የተመለከተው ጉዳይ ነው። የኮርፖሬሽኑን የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጨምሮ ከኮርፖሬሽኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በርካታ ቢሆኑም ስለዚህ ጉዳይ በቀጥታ ስልክ ውይይቱ ላይ በአስረጂነት የቀረቡት ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ፕሮጀት ጋር ተያይዞ ክስ የተመሰረተባቸውን ሃላፊዎች እና ደላሎችን የተመለከተው ነው። እነዚህም የፕሮጀክቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩ አቶ መስፍን መልካም፣ ወይዘሮ ሳሌም ከበደ ገብሩ የግል ባለሃብት ወይም ጉዳይ አስፈፃሚ፣ የውጭ ዜጋ የሆኑት የኩባንያ ወኪል ሚስተር ጁ ዩኪን፣ ጸጋዬ ገብረእገዚያብሄር የክስታት ኢንጅነሪንግ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ፣ ፍሬው ብርሃኑ አረጎት ጉዳይ አስፈጻሚ ወይም ባለሃብት ናቸው።
እነዚህ ግለሰቦች እና የስራ ሃላፊዎች በኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ፋብሪካ በ2005 ዓ.ም መጨረሻ ከቻይና ኤግዚም ባንክ ለፕሮጀክቱ ወጪ የሚሆን የገንዘብ ብድር አስፈቅዷል በሚል ጄ.ጄ.አይ.ኢ.ሲ ለሚባል የቻይና ኩባንያ በ700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውል እንዲፈረም አድርገዋል። ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር እንዳይፈረምና እንዳይጸድቅ በሃላፊዎች በኩል ለሁለት ዓመት ገንዘቡ እንዳይለቀቅ ከተደረገ በኋላ ጉዳይ አስፈጻሚ በሆኑ ሰዎች ገንዘቡን ለማስለቀቅ እንችላለን በሚል ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተቀንሶ ከቀሪው 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ላይ 180 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኮሚሽን እንዲከፈላቸው በማድረግ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ እንዲገባ አድርገዋል። እነዚህ የስራ ሃላፊዎችና ጉዳይ አስፈፃሚዎች የኮሚሽን ክፍያቸውን ወደ 30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ እንዲል አድርገዋል። ክፍያውም በውጭ አገር ባንኮች እንዲፈጸም ስለማድረጋቸው በክስ ዝርዝራቸው ተመልክቷል። ጥያቄውም የሚመጣው እዚህ ጋር ነው።
እንደሚታወቀው፤ የውጭ ብድር ስምምነት የሚከናወነው በመንግስታዊው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል ነው። ይህም ቢሆን መጀመሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊፀድቅና በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ ሊወጣ ይገባል። ከላይ የተመለከተው የክስ ዝርዝር ደግሞ የሃገሪቱ የበላይ የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይቀር በነዚሁ ከላይ የተመለከቱ ደላሎች ስራውን ተነጥቆ የደላሎች መቀለጃ መሆኑ የደላሎቹን ወይም ከላይ የተመለከቱ ተጠርጣሪዎቹን አቅም ሳይሆን ከጀርባ ያለውን የፖለቲካ ሃይል ነው። የሚለው ውሃ የሚያነሳና ተገቢ ቅሬታና ጥያቄ ነው።
የፓርቲና የመንግስት ባለሥልጣናት በሚሰጡት የበላይ ጠባቂነት እና ልዩ ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር መንግስት ባለበት ሃገር እንዲህ ያለ ጉዳይ አስፈጻሚነት ባላስፈለገም፤ ገንዘቡም እንዲሁ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከሚያንገላታት ሃገር ተቦጭቆ ቀልጦ ባልቀረም ነበር። ነገር ግን ሆነ፤ መሆኑም ጥያቄን አስነሳ። መነሳቱም ህዝቡን አይነኬዎች አሉ እስከማለት አደረሰው፤ እየተወሰደ ያለውን እርምጃም በጥርጣሬ እንዲመለከተው አደረገው።
የፖለቲካ ሙስና በመፈጸም እንዲህ ያለው ነውረኝነት መፈጸሙ ሳያንስ ከዚህ ሴራ በስተጀርባ ያለውን ሃይል በቁጥጥር ስር አለማዋል የመንግስት አሰራርን እና ተጠያቂነትን የተመለከተው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 12 ላይ ወንጀል መፈጸም ነው።
የፓርቲና የመንግስት ሥልጣንን በጨበጡ የተወሰኑ ባለሥልጣኖች ወይም ቡድኖች ቡራኬና ልዩ ድጋፍ የሚካሄድ ኪራይ ሰብሰቢነትና ሙስና ተቋማዊ ባህሪ ሲላበስ የሕግ የበላይነትን በመናድ፣ የዲሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሂደቱን እንዴት ከመቀመቅ ሊጥለው እንደሚችል መገመት አይከብድም።
መሪ ድርጅቱም ሆነ መንግስት በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ርእዮተ አለማዊ ፍልስፍና ሲቃኝ በልማቱ ውስጥ በተለይ በግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች (የግል ባለሃብቱ በማይችላቸው) ውስጥ እጁን ማስገባቱ የሚታወቅና የርእዮቱ መርህ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ የህዝብ ሃብት ለኪራይ ሰብሳቢዎች ተጋላጭ የመሆኑ እድል የሚሰፋ እንደሆነ የሚገልጸው የርእዮቱ መርህ የመንግስት ዋና ስራ ይህንን የህዝብ ሃብት መጠበቅ እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት ቢመክርም አለመጠበቁ ሳያንስ ከላይ በተመለከተው አግባብ ሀላፊነት የተሰጠው አካል ተዘፍቆበት ሲገኝ በጣም አደገኛ እና ከህዝብ አልፎ እራሱን ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ ይጥለዋል።
ገንዘብ አንቀሳቃሾቹ በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት ናቸው ብሎ ማለፍ እራስን ማሞኘት ካልሆነ በስተቀር ህዝቡ ሁሉንም ጠንቅቆ ይረዳል። በዚህ መልኩ የሚሰጥ ማስተባበያም ንጹሃኑን ባለሃብቶች የሚያሸማቅቅ እና አብረው መጨፍለቃቸውም በቀጣዩ ስራቸው ላይ ዋጋ የሚያስከፍላቸው እንደሆነም በቀጥታ የሬዲዮ ስልክ ውይይቱ ላይ ተነስቷል። ያለጨረታና በጨረታ ሽፋን በሚሰጡ ፕሮጀክቶች ለምን እንደተሰጡና እንደሚሰጡ እንዲሁም የነዚህን ፕሮጀክቶች የብድር ስምምነት አካሄድ መፈተሸ ከተቻለ ግንዱ ላይ መድረስ እንደሚቻልና ማስረጃ ፍለጋ የሚያስማስን አንዳችም ምክንያት እንደማይኖር የቀጥታ ስርጭቱ ተሳታፊ የነበሩት አድማጮች ገልፀዋል።
እነዚህ መንግስት ስላነሳቸው ተነሱ እንጂ ተሳትፎው በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቅ እንደሆነ በመንግስት በኩል ጥሪ እየተደረገለት የሚገኘው ህዝብ በውይይቱ ላይ ሌላም ነገር አንስቷል። በመንግስት ባንኮች የተንሰራፋው ሙስና የፖለቲካና የመንግስት ሥልጣንን ከለላ በማድረግ በበላይ ጠባቂነት የሚፈፀም ሙስና ስለመሆኑ ጥቂት ፋይሎቻቸውን ማገላበጥ በቂ እንደሆነም ተነግሯል። የፖለቲካ ሙስና ከሌለ ደግሞ ይህንንም ሄድ ብሎ ማየት ተገቢ ነው። እድሜው 23 እንኳ ያልደረሰ አንድ ጎረምሳ አንድ ብር ሳያወጣ ያለምንም ወይም በቂ ዋስትና ከፍተኛ ገንዘብ በብድር ስም እያገኘ በአቋራጭ ባለሀብት የሚኮንበት አካሄድን ማየት ሙስናው አደገኛው የሆነው የፖለቲካ ሙስና መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። የፖለቲካ ሹመኞችን ጋሻና መከታ በማድረግ የፋብሪካና የእርሻ ባለቤትነት በቀላሉ የሚኮንበት፣ ከፍተኛ ሙስና የሚፈፀምባቸው የመንግስት ባንኮች ውስጥ የተንሰራፋው ጠያቂ የሌለው አሰራር ምክንያት መሆኑን ለአፍታም መጠራጠር አይቻልም። ቅርንጫፉም ግንዱም በቅንጅት የሚሰሩበት የሙስና ምሽግ ለማፍረስ ተነሳሽነቱ ካለ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም ፍላጎቱ ካለ የፋይናንስ ሴክተሩን በሚገባ መፈተሸ ይልቁንም ከፖለቲካ ሙሰኞች ማላቀቅ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ይህ ሲሆን ህዝብ ተሳታፊ ይሆናል፤ ስለሃገሩ ያለው ምልከታ ይቀየራል፤ ተስፋው የለመለመ ተነሳሽነቱም የናረ ይሆናል። አልያ ግን ከጀርባ ያለውን ሙሰኛ በመተው የሚወሰድ እርምጃ ወርቃማ ለሆነው ህገ መንግስታችን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱ አደጋ ነውና፤ እኛ ዜጎች እየሰጋንና እየተጠራጠርን ብንቀጥል ሊፈረድብን አይገባም።