Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ እና ንጹህ የኃይል ማመንጨት ጥረቷ

0 483

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ እና ንጹህ የኃይል ማመንጨት ጥረቷ

አባ መላኩ

 

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስሟ በበጎ እየተነሳ ነው። በአፍሪካ ከኮንጎ ዴሞክራክቲክ ሪፐብሊክ ቀጥላ ሁለተኛዋ ግዙፍ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያላት አገር እየተባለች መወደስ ይዛለች። ይህን ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ወደ እውነታነት ለመቀየርና አገልግሎት ላይ ለማዋል በብርቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች።

 

ኢትዮጵያ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶቿ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ላይ ትገኛለች።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጅማሮ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ አለው፡፡ ዘርፉ ስድስት አሥርት ዓመታት አስቆጥሯል። በዚህ እድሜው ዘመናዊ ሊባል የሚችል የአገልግሎት ተቋም ደረጃ ላይ መድረስ ነበረበት። ግን አልሆነም። ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ከዘርፉ የሚገባውን ያህል ጥቅም ማግኘት አዳጋች ነበር።  አብዛኞቹ የአገሪቱ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ውስን ነበር። ኅብረተሰቡም ከዘርፉ በሚገኘው ጥቅም ህይወቱን እንዳይለውጥ ተገድዶ ቆይቷል።  

 

ይሁንና ዘርፉ ይነስም ይብዛም አገሪቱ አሁን ላለችበት የዕድገት ደረጃ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አይካድም። ከአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አጀማመር የጊዜ ርቀት አንፃር ወቅቱ የሚጠይቀውን የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሳይገነባ ቆይቷል፡፡

 

አገሪቱ ባለፈችባቸው በተለያዩ መንግሥታት በተለያዩ መዋቅሮች ማለፉና ከዘርፉ የሚገኘውን ትርፍ ብቻ ታሳቢ ያደረገ አሠራር እንዲሁም የአገልግሎቱን ጥራት ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች አለመኖራቸው አሁን ላለበት የአገልግሎቱ ችግሮች መባባስ ምክንያት ሆኗል።  

እንደሚታወቀው የአገሪቱ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገትና የህዝብ ቁጥር መጨመር እንዲሁም ዕድገቱ የፈጠረው የዜጎች የዘመናዊ ኑሮ መሻት የኤሌክትሪክ ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ አንሮታል። የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርናም ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ማደግ የራሱን ድርሻ በማበርከት ቦታውን ለማኑፋክቸሪንግና ለኢንዱስትሪ በመልቀቅ ላይ መገኘቱ ደግሞ ለኃይል ፍላጎት ማሻቀብ ሌላው ምክንያት እየሆነ መጥቷል።

 

እንደ ኮንስትራክሽን ያሉ የምጣኔ ሀብት ዘርፎችም የሚጠበቅባቸውን የኢነርጂ አቅርቦት ለማሟላት ከመቼውም ጊዜ በላይ የኃይል ዘርፉን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ አቅም መገንባት እንዲሁም የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ማስፋፋትና አቅማቸውን ማሳደግ ይገባቸዋል፡፡

 

የኢፌዴሪ መንግሥት ለምጣኔ ሀብቱ አንቀሳቃሽ ሞተር ለሆነው የኢነርጂ ልማት ባለፉት ዓመታት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በማልማት ላይ ይገኛል። ባለፉት 26 ዓመታት ብቻ ወደ ስምንት የሚጠጉ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ሰርቷል። የግል ባላሀብቶችም በዘርፉ እንዲሳተፉ እያበረታታ ይገኛል፡፡

 

ከዚሁ በተጓዳኝ ታላላቅ የሚባሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን በመገንባት አስተማማኝና ዘላቂ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን እውን ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ እየጣረ ነው። ለዚህም በዋቢነት የሚጠቀሱት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ የጊቤ ሦስት፣ የገናሌ ዳዋ ሦስትና የአዳማ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

 

ከዚህም ሌላ መንግሥት ዘርፉ ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት የተለያዩ ዕቅዶችን ነድፎ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ከአገሪቱ ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማርካትና ተደራሽነቱንም ለማስፋት እንዲሁም ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር እንዲኖር ለማስቻል የኃይል ዘርፉ እንደ አዲስ እንዲደራጅ ብሎም እንዲዘምን አድርጓል።

 

ይኸውም የቀድሞውንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በመባል የሚታወቀውን ተቋም ለሁለት በመክፈል የየራሳቸው ህልውና ባላቸው ሁለት የሥራ ዘርፎች እንዲዋቀር በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚል ሥያሜ እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡

 

የተሟላ የኃይል አቅርቦት ለምጣኔ ሀብት ተጨማሪ እሴት በመፍጠር አገሪቱ የተያያዘችውን ድህነትን የመቀነስ ስትራቴጂ በማገዝ የሚኖረው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ይህንንም የኃይል ዘርፍ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

 

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በኢነርጂ የተትረፈረፈ ኃይል የማምረት አቅም ያላቸው አገሮች የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭን ወደ ጎረቤት አገሮች በመላክ ዓይነተኛ የገቢ ምንጭ ማድረግ ግባቸው ነው፡፡ ከራስ ፍጆታ የሚተርፍን የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገራት በመሸጥ ከሚገኘው ሽያጭ አገራዊ አቅምን መገንባት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮችን መፍታት፣ ከአገሮችም ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ መልካም ጉርብትና ለመመሥረት ያስችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከሽያጩ በሚገኘው ገቢ ለቀጣይ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች ወጪም ጭምር የሚያግዝና አገሪቱን የምሥራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለማድረግ የታያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ ከፍተኛ ጉልበት ይኖረዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ብቻ ለሱዳን 100 ሜጋ ዋት፣ ለጂቡቲ 60 ሜጋ ዋት እንዲሁም ለኬንያ 10 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርባለች። ከዚህም 70 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች። የኃይል ሽያጩንም ለማሳደግ ከተለያዩ አገሮች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርማለች። ይህም የአገሪቱን ስትራጂክ አጋርነት የሚጨምርና በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ የጂኦ ፖለቲካ ወሣኝ ሆኖ ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት በማገዝና የጎረቤት አገሮች ምጣኔ ሀብት ጭምር እንዲያድግ የላቀ ድርሻ ይጫወታል፡፡

 

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጎን ለጎን የታቀደው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ጋር ተዳምሮ አገሪቱ አሁንና ወደፊት የሚያስፈልጋትን የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው ከወዲሁ የምጣኔ ሀብት አቅምን ማሳደግ ይገባል፡፡ ይህንኑ ከግምት በማስገባት ወደፊት የሚያስፈልገውን የኢነርጂ ፍላጎትና አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ሥራም በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን ታዳሽ ኃይል ለአገር ውስጥ ፍጆታ በማዋል እንዲሁም የተረፈውን ደግሞ ወደ ውጭ በመላክ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ባሻገር 50 ሚሊዮን ቶን ለአየር ንብረት ዋነኛ መንስዔ የሆኑ ሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ የሚያስችላት በመሆኑ የኃይል ዘርፉ ግንባታ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ብልፅግና መሠረት በመሆኑ አጠናክሮ መሄዱ ለነገ የማይባል ሥራ ይሆናል፡፡

 

በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ካርበን በመቀነስ ኢትዮጵያ ለዓለማችን ደህንነት ሥጋት በመሆን ላይ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የአገራትን ትብብር በሚጠይቀው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ወሣኝ ወቅት ላይ ዋና ተዋናይ መሆን ከሚፈጥረው አገራዊ ገፅታ ባሻገር ከካርበን ንግዱ ኢትዮጵያ የሚበረከትላት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ለአገሪቱ ዕድገት የሚያበረክተው ድርሻም እንዲሁ ከፍተኛ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy