Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እኔን እንቅልፍ የሚነሳኝ

0 574

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‹‹እኔን እንቅልፍ የሚነሳኝ…››

                                                                                                                                አሜን ተፈሪ

 

ቢቢሲ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለእርሰዎ እንቅልፍ የሚነሳዎት ችግር ምንድነው?

ጠ/ሚመለስ ዜናዊ፤ እኔን እንቅልፍ የሚነሳኝ አንድ ጉዳይ ይህ የተጀመረው አጓጊ ጉዞ አንድ ሰው በአንድ ቦታ በሚፈጽመው አንድ ስህተት ይደናቀፍ ይሆን የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ከመኝታዬ የሚያነቃኝ ዕረፍት የሚያሳጣኝ ጉዳይ ይህ ነው፡፡

ከፍ ብሎ የሰፈረው ቃል፤ ታላቁ መሪ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ (ምናልባት ከስድስት ወይም ሰባት ዓመታት በፊት) ከቢቢሲው ጋዜጠኛ ከስቴፈን ሳከር ጋር ካደረጉት አንድ ቃለ ምልልስ የተወሰደ ነው፡፡ ይህ ቃል፤ የሐገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በጥልቅ ከመመርመርና ከመረዳት የተሰጠ አስተያየት ነው፡፡ ጠ/ሚ መለስ ‹‹አንድ ሰው በአንድ ቦታ….›› ሲሉ የተናገሩት ቃል ብዙ የሚናገረው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል፤ ሐገራችን ‹‹አንድ ሰው በአንድ ቦታ በሚፈጽመው ስህተት…›› የተነሳ ለአደጋ የምትጋለጥበት ሁኔታ መኖሩን እና በተቋማት ግንባታ ረገድ ብዙ መሥራት የሚገባን መኖሩን የሚያመለክት ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ አጓጊ የህዳሴ ጉዞ ውስጥ መሆናችንን እና ከዚህ ጎዳና ሊያስወጡን የሚችሉ ጉዳዮች መኖራችንን ተገንዝበን በማስተዋል መጓዝ የሚገባን መሆኑን የሚያሳስብ ቃል ሆኖ ይታየኛል፡፡ የጠ/ሚ መለስ ቃል በሁለቱም ጎዳና ወሳኝ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በአጭሩ ይህ የአቶ መለስ ቃል፤ ባለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር የሚታየው ህብረተሰብ ‹‹የሽግግር ህብረተሰብ›› መሆኑን የሚያስረዳ አስተያየት ነው፡፡

የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን፤ ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› (2003) ሲሉ በጻፉት መጽሐፋቸው የሽግግር ህብረተሰብ ባህርያትን በሰፊው ይተነትናሉ፡፡ አቶ በረከት የሽግግር ህብረተሰብ ሁለት ወደረኛ የሆኑ ገጽታዎች ጎልተው የሚታዩበት ህብረተሰብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህን ሁኔታ ለማስረዳት ሲነሱ፤ ከስመ ጥሩው እንግሊዛዊ ደራሲ ቻርልስ ዲከንስ መጽሐፍ በተወሰደ ጥቅስ ይንደረደራሉ፡፡ ቻርልስ ዲከንስ ‹‹የሁለት ከተሞች ወግ›› በተሰኘ የልብወለድ ድርሰቱ፤ ‹‹የተስፋ ጊዜ ነው፡፡ የተስፋ ማጣትም ጊዜ ነው፡፡ የዕረፍት ጊዜ ነው፡፡ ዕረፍት የማጣት ጊዜም ነው፡፡ የማግኘት ጊዜ ነው፡፡ የማጣትም ጊዜ ነው፡፡…..›› እያለ የሚያቀርበውን ገለጻ መነሻ አድርገው፤ የሽግግር ህብረተሰብ መንታ ገጽታዎች ጎልተው የሚታዩበት ህብረተሰብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ አንጻር የአሁኑ የሐገራችንን ህብረተሰብ ሁለት መንታ ገጽታዎችን የሚያንጸባርቅ ህብረተሰብ ነው፡፡ ይህ ዘመን ‹‹ተስፋ የማድረግ ዘመን ነው፡፡ የተስፋ ማጣት ዘመንም ነው፡፡  የብርሃን ጊዜ ነው፡፡ የጨለማም ጊዜ ነው፡፡ የማግኘት ጊዜ ነው፡፡ የማጣትም ጊዜ ነው፡፡›› እንዲህ ያሉ ሁለት ተነጻጻሪ እና ተጻራሪ ሁኔታዎች በአንድ ቦታ እና በአንድ ጊዜ ተነባብረው እና በአንድ ጊዜ እና ሥፍራ አድረው የሚታዩበት ጊዜ ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ ገለጻቸው የአሁኗን ኢትዮጵያ ሁኔታ በትክክል የሚያንጸባርቅ አስተያየት ነው፡፡ የአሁኗን ኢትዮጵያ በተስፋዋ ብቻ መግለጽ ስህተት ይሆናል፡፡ ትክክለኛው የሚሆነው፤ አወንታዊ ገጽታውን ከአሉታዊው ገጽታ ጋር አስተባብሮ ለማየት መሞከር ነው፡፡ በተጨባጭ የሽግግር ህብረተሰብ መሆናችን የሚያሳየው እንዲህ ያለ ትንታኔ ነው፡፡

ይህን እውነታ የሚኖርበትን ዐውድ በትኩረት ለመከታተል የሚሞክር ሰው ሁሉ በግል ህይወቱ እና በዕለት-ተዕለት ገጠመኞቹ ነጸብራቅ ሊያስተውለውና በቀላሉ ሊረዳው የሚችለው ነው፡፡ በአሁኑ ሁኔታ በተስፋ ተሞልተን ከምንናገርበት ሥፍራ ሳንነሳ፤ ተስፋችንን የሚነጥቅ ሁኔታ ለማየት እንገደዳለን፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያን ሁኔታ በተለያዩ የህብረተሰብ ህይወት ዘርፎች ለመቃኘት ስንሞክር፤ በተስፋ የሚሞሉን በርካታ ስኬቶችን በሰፊው እናገኛለን፡፡ በዚህም በተስፋ ተሞልተን የምንገኝበትን ሁኔታ ለመጥቀስ እንችላለን፡፡ በዚሁ አኳያ በተለያዩ ዘርፎች የሚታዩ ተግዳሮቶችን ተመልክተን ግራ እንጋባለን፡፡ ተስፋችን ሊነጥቁ የሚሞክሩ በዙሪያችን የሚያደቡ በርካታ ተኩላዎችን ልናስተውል እንችላለን፡፡

ታዲያ አንዳንዴ ይህ ዥዋዥዌ የተጨባጭ ሁኔታ ንባብ ችግር መስሎ ሊሰማን ይችላል፡፡ የህብረተሰብ ህይወት ንባብ የአቅም ውስንነት ችግር ሆኖ ሊታየንም ይችላል፡፡ ከማይፈታ እንቆቅልሽ ጋር የተጋፈጥን መስሎን ልንደናገር እንችላለን፡፡ ሆኖም፤ ችግሩ ከተጨባጭ ሁኔታ ንባብ ወይም ከህብረተሰባዊ ህይወት አተረጓጎም ብቃት ማጣት ችግር ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ችግሩ ከዚህ ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ራሱ የተጨባጭ ሁኔታው መልክ እንዲህ ግራ አጋቢ ነው፡፡ ግራ መጋባታችን ከንባብ አቅም ችግር ጋር የተያያዘ ሳይሆን፤ ከራሱ ከህብረተሰባዊ ህይወቱ ተጨባጭ እውነታ የሚፈልቅ ግራ አጋቢ ሁኔታ ነው፡፡

በመሆኑም፤ የህብረተሰባችን ህይወት ገጽታ ግራ አጋቢ ሆኖ ከታየን፤ ተጨባጭ ሁኔታውን በትክክል ተረድተነዋል ማለት ነው፡፡ የምንገኝበት የህብረተሰባችን ተጨባጭ ሁኔታ ሁለቱንም ተቃራኒ እውነታዎች የያዘና እነዚህን ሁለት ተጻጻሪ ገጽታዎች በአንድ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ንባባችን ትክክል ነው፡፡ ይህም የሽግግር ህብረተሰብ ጠባይ ነው፡፡ ትንታኔአችን ትክክል ነው፡፡

የሐገራችን እምቅ አወንታዊ ኃይል እና እምቅ አሉታዊ ኃይሉ የገመድ ጉተታ ትግል ውስጥ ናቸው፡፡ ሁለቱ ኃይሎች የገመድ ጉተታ ትግል የሚያደርጉበት ሜዳ ነው፡፡ ትግላቸውን ዳር ቆሞ ለሚመለከት ሰው፤ በምን ግዴ ስሜት ሁኔታውን ለሚከታተል ሰው፤ በልብ ሰቃይ ገጽታው ተስቦ በአንክሮ ሊመለከተው የሚችለው የሽግግር ህብረተሰብ ህይወት ነው፡፡ ሁኔታው ኢትዮጵያ በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ የምትገኝ ሐገር መሆኗ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ ትክክለኛ ጎዳና ሊያስወጧት የሚችሉ በርካታ ተኩላዎች ውርውር ሲሉ የሚታዩበት የልማት ጎዳና መሆኑም እሙን ነው፡፡  

በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ከሚገኙ አብዮታዊ ዴሞክራቶች የሚጠበቀው፤ አወንታዊ እምቅ ኃይሉን ለማጠናከርና አሉታዊ እምቅ ኃይሉን ለመድፈቅ በሚካሄደው ትግል አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የሚያስችል በሳል አመራር መስጠት እና በጽናት ትግል ማካሄድ ነው፡፡ ትግሉ የሚጠይቀው ማስተዋል እና ጽናትን ነው፡፡ በማይነዋወጽ የዓላማ ጽናት መቆምን ግድ ከሚል የትግል ምዕራፍ ውስጥ መሆናቸውን ተረድተው በትግሉ ሜዳ በማስተዋል እና በንቃት መሰለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የሽግግር ህብረተሰባችን አወንታዊ እምቅ ኃይል ተጠናክሮ፤ አወታዊው ኃይል የበላይ ሆኖ እንዲወጣ በጽናት መታገል የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው፡፡

ይህን ትግል ከመኖር ማስቀረት አይቻልም፡፡ የግድ መታለፍ የሚገባው የትግል ምዕራፍ ነው፡፡ በጽናት ወደፊት መራመድን የሚጠይቅ የትግል ምዕራፍ ነው፡፡ ሁለት ልብ በመሆን የሚሰለፉበት ምዕራፍ አይደለም፡፡ ሁለት ልብ መሆን ለአሉታዊ እምቅ ኃይሉ ዕድል መስጠት እና ክህደት ነው፡፡ ትግሉ የጎራ መደበላለቅ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምናካሂደው ትግል በመሆኑ ውስብስብ እና አስቸጋሪ ባህርያት ያሉት መድረክ ነው፡፡ የሽግግር ህብረተሰብ ከሚገጥመው ፈተና ጋር መጋፈጣችንን በመረዳት የሚካሄድ ትግል ነው፡፡ እናም ይህ የተሳከረ ሁኔታ እየጠራ አወንታዊ እምቅ ኃይሉ የበላይነት የሚይዝበት ዕድል እንዲጠናከር ለማድረግ ተግተን መሥራት ይኖርብናል፡፡

የሽግግር ህብረተሰብ ባህርይ በመሆኑ፤ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ እንደተናገሩት፤ ‹‹አንድ ሰው በአንድ ቦታ በሚፈጽመው ስህተት የተጀመረው አጓጊ የህዳሴ ጉዞ ይደናቀፍ ይሆን?›› የሚል ከእንቅልፍ የሚያባንን ችግር መጋፈጣችን አይቀርም፡፡ የተስፋው ትዕይንት ወይም የህዳሴው ትርዒት፤ በረሃብ ወቅት እንደተገኘ ‹‹የአክርሚኝ እህል›› የሚያሳሳ ነው፡፡ በመሆኑም የተገነባው ፌዴራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይናጋ፤ አሁን የሚታየው አጓጊ የኢኮኖሚ ልማት ግስጋሴ እንዳይቀዛቀዝ፤ እንዲሁም ለሁለት አስርት ያጣጣምነው የሰላም አየር እንዳይደፈርስ በንቃት ዘብ በመቆም፤ የህዳሴው ጉዞ ‹‹አንድ ሰው በአንድ ቦታ በሚፈጽመው ስህተት›› ሊደናቀፍ ከማይችልበት ደረጃ ለማድረስ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህን ተረድተን አወንታዊ እምቅ ኃይሉ ሚዛን እንዲደፋ ለማድረግ እንቅልፍ ሳያምረን መሥራት እና ታላቁ መሪያችን የነፍስ ዕረፍት እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርብናል፡፡                         

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy