Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹ከመንግሥት ባለሥልጣን ጋር የተጠጋ አይነካም የሚለው ነገር ከዚህ በኋላ አይሠራም››

0 602

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

የሙስና ወንጀል ተግባራት ጋር ተያይዞ መንግሥት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ የዘገየ አለመሆኑንና የባለሥልጣን ከለላ ያላቸው አይነኩም የሚለውን አመለካከት እንደማይቀበሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡ መንግሥት ከአሁን በኋላ በአገሪቱ አለመረጋጋትን የሚያስከትሉ ክስተቶችን እንደማይታገስም አስጠንቅቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንኑ የገለጹት ቅዳሜ ነሐሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው በሦስተኛው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ በተለይ ከሙስና ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ እንደሚገፋበት አመልክተዋል፡፡ ከእሳቸው ማብራሪያ ቀደም ብሎ ግን በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ የቀረበው ሪፖርት፣ የመንግሥት ዕርምጃ የዘገየ ነው የሚል አመለካከትን ያንፀባረቀ ነበር፡፡

በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ሙስናንና እያስከተለ ያለውን አደጋ በአፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚያፈልግ የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ሙስና በአገር ዕድገትና ልማት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ዋነኛ የሥነ ምግባር ችግር መገለጫ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ሙስናን በመከላከል ረገድ በመንግሥት የተከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች ቢኖሩም፣ ችግሩን በሚፈለገው መጠን ለመቀነስ ባለመቻሉ ሳቢያ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት ለምዝበራና ለብክነት በማጋለጥ አሳሳቢነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ሲያስፈልግ ዘግይቶ ሙሰኞችን የሚይዝበት ሳይፈልግ የሚተውበት የሚመስል አሠራር በመተው የግሉን ዘርፍ፣ የፓርላማ አባላትን፣ ሲቪክ ማኅበራትንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ወጥነት ያለው አደረጃጀት በመፍጠር ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት አሠራር መፈጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በመንግሥት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አጥፊዎችን በሕግ ከመቅጣት ባለፈ ለሌሎች አስተማሪ ሊሆን የሚገባው በመሆኑ፣ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችን ውጤት ለሕዝብ በይፋ እንዲገለጽ ማድረግ እንደሚገባ፣ ዘግይቶ የሚሰጥ ውሳኔ ጊዜ በመግዛት የፍርድ መዛባትን ስለሚያስከትል እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን ብቻ የሚያይ ልዩ ችሎት እንዲቋቋም አቶ ሰለሞን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ሰለሞን በዘመቻ መልክ የሚካሄዱ የፀረ ሙስና ሥራዎች የአንድ ወቅት ከመሆናቸው ባለፈ፣ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰነው ቅጣት በሕዝብና በመንግሥት ጥቅም ላይ ካደረሱት ጉዳት አንፃር ሲመዘን ተመጣጣኝ ባለመሆኑና ሌሎች አጥፊዎችን ከማስተማር ይልቅ የሚያበረታታ በመሆኑ፣ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም ብሎ ምክር ቤታቸው እንደሚያምንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተለይ በቅርቡ በመንግሥት የተወሰደውን ዕርምጃ የተመለከትን እንደሆነ ከዚች ደሃ አገር በቢሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት ያላግባብ ሲመዘበርና ሲባክን የበይ ተመልካች በሆነው ሕዝብም ሆነ መንግሥት በኩል፣ ይህ ሁሉ ሲሆን የት ነበርን የሚያስብል አግራሞትና ትዝብት የሚፈጥር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ሐሳብ ጋር የማይስማሙ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ ‹‹አሁን በኋላ መንግሥት እንደ ድሮው ዓይነት አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እንኳን ከመንግሥት ባለሥልጣን የተጠጋ አሁን የመንግሥት ባለሥልጣናት መያዣ መጨበጫ አጥተዋል፤›› በማለት የሰሞኑን ክስተት አንፀባርቀዋል፡፡ አንዱ ተቆርጦ ሌላው እንደማይቀር ተናግረው፣ ስለዚህ አሁን እከሌ የሚባል ባለሥልጣን አለኝና እሱን ተገን አድርጌ እንደፈለግኩ እኖራለሁ የሚል ሰው ካለ እጁን መሰብሰብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ከሙስናና ከሕገወጥ ተግባራት ጋር በተያያዘ እየተወሰደ ያለውን ዕርምጃ በተመለከተም፣ ቀጣዩ የመንግሥት ዕርምጃ በንግዱ ዘርፍ ላይ የሚያነጣጥር መሆኑን ለማስገንዘብ ‹‹የሚቀጥለው ጥናታችን ወደ ንግዱ እየገባ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ንግግራቸው በትክክል የሚፈጸምና የአገር ጉዳይ በመሆኑ የሚተገበር መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይቺ አገር ሰላማዊ ካልሆነች የማናችንም መኖር ዋስትና የለውም፡፡ ከዚህ በፊት አንዳንድ የሚወሩ ነገሮች ነበሩ፡፡ እከሌ የሚባል ባለሥልጣን ዘንድ የተጠጋ ስለሆነ አይነካም፡፡ እስቲ እንደማይነካ እናያለን፡፡ እውነቴን ነው የማይነካ ሰው የለም፡፡ ምክንያቱም ከግለሰቦች አገር ይበልጣል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ሲደረግ ግን ሕግና ሥርዓትን ተከትለን ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ትልቁ ምሰሶ የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ሕጎች በሚፈቅዱት መሠረት ብቻ ዕርምጃ እንደሚወሰድና eza

News 1ዕርምጀጃዕር ማንም ቢሆን ራሱን የመከላከል መብት እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ምንጭ የሆኑ አምስት ጉዳዮች መኖራቸውን መንግሥት ሲናገር እንደቆየ ያመለከቱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው መሬት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከመሬት ሊዝ ጋር የሚገናኝ ችግር አለ፡፡ ይኼ ችግር የሚያጋጥመን በትልልቅ ከተሞች ነው፡፡ ለምሳሌ የሪል ስቴት አልሚዎችን ማየት ይቻላል፡፡ የሪል ስቴት አልሚዎችን ነገሩ ወደ እስር ቤት የሚያስገባም ቢሆንም ግድ የለም እንታገሳቸውና የወሰድከውን ትርፍ መሬት መልስ ከመለስክ በኋላ የቦታውን ትክክለኛ ሊዝ ክፈል ብለን ከባለሀብቶቹ ጋር ተደራድረን እስር ቤቱን ላለማጣበብ ሙከራ አድርገናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

አሁን መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ የዘገየ ነው የሚለው አቋም መንግሥትን በማንቋሸሽ ዕርምጃውን ለማስቀረት የሚደረግ ፕሮፓጋንዳ ነው ብለውታል፡፡ ‹‹ይህንን አመለካከት በግሌ የምቀበለው አይደለም፡፡ እቺ እሳት እየተቀጣጠለች ወዴት ትደርሳለች ብሎ ያሰበ ሁሉ እያንቋሸሸ ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም እሳቱ መድረሱ፣ መንግሥትም ጠንክሮ መቀጠሉ እንደማይቀር አመልክተዋል፡፡

የሙስና ዕርምጃው የላይኛውን የሥልጣን አካል አልነካም እየተባለ የሚነገረውም ለማንቋሸሽና ለማኮላሸት የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፕሮፖጋንዳው ምንጭ በአግባቡ ካልጠራ በስተቀር ሒደቱን ለማኮላሸት የሚደረግ ሽረባ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ በዚህ ላይ አንድም ጥቆማ ያለመስጠቱን እንደ ምሳሌ አቅርበዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱም ሆነ የዘርፍ ማኅበራቱ አንድ ጥቆማ ያለማምጣታቸውን የጠቆሙት አቶ ኃይለ ማርያም፣ እስካሁን የደረሱ ጥቆማዎች ከሕዝብ የመጡ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

‹‹የንግድ ኅብረተሰቡ አንድም ጥቆማ ሳያደርግ ጉዳዩን መንግሥት ላይ ደፍድፋችሁ የፀረ ሙስና ትግል በዚህ ይሄዳል ብላችሁ ካሰባችሁ አያስኬዳችሁም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከማንም በላይ ሌባ የምታውቁት እናንተ ናችሁ፡፡ ምንም የሌለው ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙ ሕንፃዎች ባለቤት ሲሆን የምታውቁት እናንተ ናችሁ፡፡ አብራችሁ የምትበሉ የምትጠጡ፣ በሠርጉም በድግሱም አብራችሁ የምትቆዩት እናንተ ስለሆናችሁ፣ እናንተ እኛን አከናንባችሁ መንግሥት ዘግይቶ እንዲህ አደረገ ማለት አትችሉም፤›› በማለት የንግድ ኅብረተሰቡ ሙሰኞችን በመጠቆም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፀረ ሙስና ንቅናቄ ተብሎ በሚደረግ መድረክና ስብሰባ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች መኖራቸውን በማስታወስ፣ አሁን ምንም እንደማያውቁ አድርገው ያቀረቡት  እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የፀረ ሙስና ትግል ኅብረተሰባዊ ካልሆነ፣ የሕዝብ ንቅናቄ ያልተፈጠረበት ትግል ካልሆነ ውጤቱ የተኮላሸ ይሆናል፡፡ የምንጋፈጠው ኃይል ቀላል  አይደለም፡፡ የራሱ መስመርና ኃይል ካለው ጋር ነው የምንጋፈጠው፡፡ በዚህ ትግል የንግዱ ኅብረተሰብ በሙሉ ቀልብ ተሳታፊ ከሆነ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ይህንን በጋራ ሆነን አጠናክረን ከቀጠልን ፍትሐዊ የንግድ ኢንቨስትመንት ይኖራል፤›› ሲሉም ከመወቃቀስ ይልቅ በትብብር ለመሥራት ጥሪ አድርገዋል፡፡

በቅዳሜው ስብሰባ ላይ ከሙስና ጋር በተያያዘ የሕዝብ ሀብት እየተመዘበረ ለመሆኑ ለቀረበው አስተያየት ጉዳዩን ከቡና የኮንትሮባንድ ንግድ ጋር አያይዘው መልስ ሰጥተውበታል፡፡ ቡና በሕገወጥ መንገድ እንደሚወጣ በመናገር፣ ይህንን የሚያደርጉት በሕጋዊ መንገድ ቡና እያቀረቡ ያሉ ነጋዴዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በኮንትሮባንድ  ቡና ከአገር የሚያስወጡት አንድ እግራቸውን በማዕከላዊ ገበያ ያደረጉ፣ ሌላውን እግራቸውን ደግሞ ሱዳን ያስቀመጡ ሰዎች ናቸው፤›› በማለት ሕገወጥ ንግዱ ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው የሚከናወን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በሁለት እግሮች ይንቀሳቀሳሉ ያሉዋቸውን፣ ‹‹እግራችሁ ሰብሰብ ይበል!›› በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

እንዲህ ያለው ጉዳይ መስተካከል እንዳለበት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ለዚህም አንድ ጠንካራ ፀረ ኮንትሮባንድ ቡድን አቋቁሜያለሁ፡፡ አከርካሪ ሰብረንም ቢሆን እናስተካክላለን፤›› በማለት በመንግሥት ሊወሰድ የታሰበውን ዕርምጃ ጠቆም አድርገዋል፡፡ ቀጣዩ ዕርምጃ በንግድ ላይ ነው የተባለውም ለዚህ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹እነዚያ አጭበርባሪ ኮንትራክተሮች ንብረታቸው ታግዷል፡፡ ስንትና ስንት ዓመት የለፉበትን ንብረት በሌብነት ምክንያት እያጡት ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ተዘረፈ የተባለውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለማስመለስ የሚያስችል በቂ ንብረት አለ ብለዋል፡፡ ‹‹የተዘረፈ የሕዝብ ንብረት ተዘርፎ አይቀርም፤›› የሚል ምላሽም ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሥጋት እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ማብራሪያ ጎን ለጎንም ሰሞኑን ከሙስና ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው ስለታሰሩ ግለሰቦችና ስለታገዱ ኩባንያዎች ታዘብን ያሉትን እንዲህ ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ንብረታቸው የታገደባቸው ኩባንያዎች ስም ሲጠራ ብዙ ሰው ቦሌ ነበር፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲባል ወዲያው ራሱን የጠረጠረም ነበር፡፡ እኛ ያልደረስንበትም የደረስንበትም ነበር፡፡ የዱባይ አውሮፕላን ተጨናንቆ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ እዚያ ከመድረስ በፊት መጠንቀቅ እንደሚያሻ ያመለከቱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ያንን ሁሉ ለፍተው ያገኙትን ንብረት ጥለው ከመኮብል በፊት አርፎ መቀመጥ ይሻላል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ እነዚህ ሰዎች እዚያ (ዱባይ) ገንዘብና ንብረት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ዋናው ንብረት እዚህ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የቡናውንም ቢሆን መልክ እናስይዛለን፡፡ ይኼ ካልሆነ አገራችን ችግር ውስጥ መውደቋ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በዚህ ትግል ውስጥ በጋራ እንሳተፍ፡፡ ከቡና ጋር ተያይዞ አለ የሚባለውን ችግር ብናይ ጥሩ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ አቶ ኃይለ ማርያም አፅኖት ሰጥተው ካስገነዘቡዋቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ በባህር ዳር አካባቢ ከንግዱ ኅብረተሰብ አባላት መታሰር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ‹‹በባህር ዳር አካባቢ ከመረጋጋት ጋር ተያይዞ መንገራገጭ ቢኖርም ይህንን እናስቆመዋለን፤›› ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ታስረዋል የተባሉ ሰዎች ንፁኃን ናቸው የሚለውን አስተያየት አቶ ኃይለ ማርያም እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የታሰሩት ሰዎች ተጠንተው የታሰሩ ናቸው፡፡ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ቀድሞም የነበሩ ሰዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሰውዬው ስሙ ማንም ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛውም ዓይነት ክብር ሊኖረው ይችላል፡፡ ወጣት፣ ታክሲ፣ ባጃጅ እየቀሰቀሰ፣ ገንዘብ እየሰጠ፣ ዝጉ እያለና እያሰማራ ሕፃናቱን ከፊት እንድናገኝ አናደርገውም፤›› በማለት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አሁን ግን ሥሩን ፈትሸን እንነቅላለን፡፡ እስካሁንም ከወጣቶቻችን ጋር የተጋጨነው ይበቃናል፤›› በማለት ሲናገሩ ተሳታፊዎች የሞቀ ጭብጨባ ችረዋቸዋል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የተለያዩ ሐሳቦች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከንግድ ማኅበረሰቡ ለተጠየቁ ጥያቄዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጡ የነበሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ በቅዳሜው ስብሰባ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy