Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል የፀረ-ድህነት ዘመቻው አካል ነው!

0 288

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል የፀረ-ድህነት ዘመቻው አካል ነው!

                                   ዳዊት ምትኩ

መንግስት ከ26 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ሲረከብ የድህነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትጠቀስ ሀገር ነበረች። ይህን ችግር ከስር መሰረቱ ለመፍታት መንግስት የፀረ ድህነት ትግል ንቅናቄን በየደረጃው በማቀጣጠል ኢትዮጵያ ዛሬ በተገላቢጦሽ የልማት አገር እንድትሆን ማድረግ ችሏል። አሁንም የሀገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥም በሁሉም መስኮች እየተረባረበ ነው። በተለይም ልማትን ለማረጋገጥ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር በቁርጠኝነት በመታገል ላይ ይገኛል። ይህም ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል የፀረ-ድህነት ዘመቻው አንድ አካል መሆኑን የሚያመላክት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት ገና ከጅምሩ ተራራ የሚያክለውን የአገሪቱን ድህነት ለመዋጋት ሶስት መርሆዎች ቀይሶ ነበር። መንግስትና ህዝብ የተጓዙባቸው መንገዶች በአገሪቱ ለረጅም ጊዜ የተንሰራፋውን ድህነት ለማሸነፍ ፈጣን ባለመሆናቸው፤ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እንዲሁም ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ የዕድገትና ድህነትን የማስወገድ መርህ መዘርጋት አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሔ እንደነበር በማመን ይህን እውን አድርገዋል።

በተለይም በተለያዩ ወቅቶች ሲካናወኑ የነበሩት የፈራረሱና ያረጁ የኢኮኖሚ ማህበራዊ ተቋማትን ለማደስ፣ ኢኮኖሚውን ከኋሊት በማላቀቅ ወደ ፊት ለመመልከትና ትክክለኛ አቅጣጫን እንዲይዝ ለማድረግ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ቀላል አልነበሩም። የመንግስት አስተዳደርንና አገሪቱ የምትመራባቸውን ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያልተማከሉ የማድረግ፣ ኢኮኖሚውን ከዕዝ ወደ ገበያ መር ስርዓት የማምጣት፣ በፖሊሲ መዛባት በጦርነትና በተፈጥሮዊ ክስተቶች ሳቢያ የተሽመደመደው ኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዲቀየር የማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል።

ደርግ እንደ ወደቀ ሰላምና መረጋጋትን ከማምጣትና የመንግስት አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ከማድረግ ባሻገር፤ የመካከለኛ ዘመን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ልማት ለማምጣት ሰፊ ርብርብ መደረጉ አይዘነጋም። በተለይም በፖሊሲ መዛባት፣ በጦርነትና ተፈጥራዊ ክስተቶች ሳቢያ የተሽመደመደውን ኢኮኖሚ እንዲያሰራራ የማድረግ ሲሆን፤ የነበረውን የዕዝ ኢኮኖሚ አሰራሩንና የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ውጤት የሆነውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት የማስተካከል ብሎም የሁለት አስተሳሰብ አደላደልና አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩ ማነቆዎችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የሰው ሃይልና መሰረተ ልማትን በማጎልበት የተፈጥሮ ሃብት አያያዝንና አጠቃቀምን ማሻሻያ ፕሮግራሞች ተካሂደዋል። አራተኛው ደግሞ ለኢኮኖሚ ፖሊሲው ተግባራዊነትና ለልማት ፕሮግራሞች ውጤታማነት የሚረዱ አስተዳደራዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ ተችሏል። በእነዚህም ተግባራዊ ለውጥ ከመምጣቱም በላይ፤ አገራችን ከባዶ ካዝና ተነስታ የተወሰኑ ኢኮኖሚያዊ መሻሻሎችን ማሳየት ችላለች።

ይህ እየተተገበረ በነበረበት ወቅት ግን የዛሬ 15 ዓመት በመጠኑ የተገኘውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ወደ ኋላ የሚቀለብሱ የኪራይ ሰብሳቢነትና የጥገኝነት አስተሳሰቦች በመገንገናቸው ተሃድሶ እንዲካሄድ ተደርጓል። በዚህ ተሃድሶም በርካታ በመንግስት ስልጣን ላይ የነበሩ ግለሰቦች ከኃላፊነታቸው እንዲወገዱና በህግም ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉ አይዘነጋም። በወቅቱ የታየው የኪራይ ሰብሳቢነትና የጥገኝነት ተግባር የአገራችንን የለውጥ ጉዞ በእጅጉ የጎዳ እንዲሁም በተግባሮቹ አራማጆች ላይ የተወሰደው እርምጃ ትክክል መሆኑ የታወቀው በቀጣዩቹ ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ተከታታይ እድገት ነው።

ርግጥም ከመጀመሪያው የተሃድሶ እርምጃ በኋላ የአገራችን እድገት ፈጣንና ተከታታይ ሆኖ ቀጥሏል። በተለይም ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የተሟላ ዝግጅት በመደረጉና ህዝቡም መንግስት የቀረፃቸውን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ወደ ተሻለ እመርታ ለመሸጋገር በቅቷል። እናም ላለፉት 15 ዓመታትም መንግስት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥናት ለማስወገድ በመሞከርና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ክንዋኔዎች መፈፀም ተችሏል። እንዲሁም ያሉትን ውስን ሃብቶች መሰረታዊ ችግሮችን በሚፈቱበት የልማት ስራዎች ላይ በማዋል፣ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት ብሎም የግል ኢንቨስትመንት በማበረታታት ፈጣን ቀጣይነትና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት ለማምጣት ተችሏል።

ባለፉት 15 ዓመታት ዓበይት የኢኮኖሚ ዘርፎች ለሆኑት ግብርና እና ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍም በግብርና እና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ ተችሏል።

በተደረጉት የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለስራው የሰው ሃይል ልማት በመንግስት የተሰጠው ትኩረት የላቀ በመሆኑ የተገኙ ውጤቶችም አበረታች ናቸው። እርግጥ በመንገድ ግንባታ፣ በኤሌትሪክ ሃይልና በቴሌኮሙኒኬሽን እንዲሁም በንጹህ ውኃ አቅርቦት ረገድ የተገኘው መሻሻል አገልግሎቶቹን ለማስፋፋት የጠየቁት ከፍተኛ የፋይናንስና የሙያ ክህሎቶች፤ የተፈራውን ያህል ስራዎቹን ሊያስተጓጉሏቸው አለመቻላቸውን የተገኙት ውጤቶች ምስክሮች ናቸው።

የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር እንዲቀንስና በየደረጃውም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መንግስት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የቻለ ቢሆንም፤ በህዝቡ ተሳትፎ እየተገበረ ያለው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የእድገቱን መሰረት ይበልጥ ያሰፋዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የአገሪቱ የግብርና መር ፖሊሲ ወደ ኢንዱስትሪ መር በሂደት እንዲሸጋገር እየተደረገ ያለው ጥረት አንድ ማሳያ የሆኑት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተስፋ ሰጪዎች ናቸው። ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝልን ነው።

ታዲያ እነዚህ አበረታች ልማትን የማረጋገጥ የፀረ ድህነት ዘመቻዎች የህዝቦችን ከፍተኛ ጥረት የጠየቁ ብቻ ሳይሆን በውጣ ውረድ በታጀቡ ናቸው። እንዲሁ በቀላሉ የተገኙ አይደሉም። እጅግ ከፍተኛ አገራዊ ሃብትንና እውቀትን የጠየቁ ናቸው። እናም ልማቱን የሚያደናቅፉ ተግባራት ሁሉ ሊወገዱ ይገባል። እነዚህን ችግሮች የመቅረፍ ተግባር የፀረ ድህነት ዘመቻው አካል ነው። የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርም በዚህ የፀረ ድህነት ትግል ሊቀረፍ ይገባል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን እያከናወነ ያለው ኪራይ ሰብሳባነትን የመታገል ስራ የፀረ ድህነት አካል ነው ማለት ይቻላል። ድህነትን ለመቅረፍና በሂደትም ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት እንቅፋቶች ማስወገድ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ፊት ለፊት ማውገዝና መታገል ይኖርበታል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy