Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኪራይ ሰብሳቢነትን ጠራርጎ ማስወገድ ቀጣዩ ሥራችን…

0 304

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኪራይ ሰብሳቢነትን ጠራርጎ ማስወገድ ቀጣዩ ሥራችን…

 

አባ መላኩ

 

የተበላሹ አሠራሮችን የመለየትና በተበላሹ አሠራሮች ውስጥ ገብተው የግል ተጠቃሚነታቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶች፣ ደላላዎችና ኃላፊዎችን በመከታተል፣ በመመርመርና በማጥናት ለሕግ ቀርበው ተገቢውን ርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ በቢሊዮን የሚቆጠር የአገርና የህዝብ ሐብት ከብክነት የዳነበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን ለመዋጋት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ዳር ለማድረስ ትግሉን  ህዝቡ በባለቤትነት ሊመራው ይገባል። እስካሁን ያለው ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሮ መጪው ትውልድ በሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት ታንጾ  ሙስናን የማይሸከም ለማድረግ ሁሉም መሠረቶች ሊፈጠሩና ሊጠናከሩ የግድ ይላል።


ኪራይ ሰብሳቢነትን በግላጭ የሚዋጋ፣ ራሱም ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳና ሙሰኝነትን የሚፀየፍ ኅብረተሰብ መፍጠር የልማቱ መቀጠልና አለመቀጠል አንድ ወሣኝ አካል ነው። ይህንን መሠረት ለመፍጠር መንግሥት አመቺ ሁኔታ አዘጋጅቷል። ይህንን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም ሁሉም በአንድነት  የተጠናከረ ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል።

 

ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለሙስና ትግሉ ስኬት ኅብረተሰቡ መገለጫዎቹን ለይቶ ማወቅና በዚያ ልክ መተግበር ይጠበቅበታል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ የአገርና የህዝብ ጠንቅ ለመቆጠብና ሌሎችንም ለመከላከል መሠረታዊ ባህሪያቱንና የተለያዩ ገጽታዎቹን ጠንቅቆ ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ መንግሥት በትምህርት ቤቶች የሥነ ምግባርና የሥነ ዜጋ ትምህርቶች እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል፡፡


የሙስና መሠረታዊያን  መገለጫዎች ከሚባሉት  አንዱ በየደረጃው ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ሊያገለግሉት ኃላፊነት ከተሰጣቸው ህዝብ ጉዳይ  ለማስፈፀም የሚቀበሉት ጉቦ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሙስና በአንድ አገር የፍትህ መጓደል ላይ ያለውን አደጋ ያሳያል። ይህም ሁኔታ ዜጎች ነጻ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ሲገባቸው ያለአግባብ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረጉበትን ሁኔታ ይፈጥራል።


ሌላው አስከፊ ገጽታ ደግሞ በኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች የሚፈፀመው ነው። እነዚህ ባለሃብቶች በሕገ ወጥ  መንገድ ከሃብት ላይ ሃብትን ለማካበት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው።  እነዚህ ወገኖች ለሚያደርጉት መጠነ ሰፊ ሕግን ያልተከተለ የገንዘብ እንቅስቃሴ ሕጋዊ  ከለላን ለማግኘት ከመንግሥት ሹመኞች ጋር የሚዋዋሉት ጉዳይ ነው። ይኼኛው የኪራይ ሰብሳቢነት ገጽታ ወይም  የሙስና መረብ የህዝብ ኃላፊነት የያዙ ግለሰቦችን በገንዘብ ኃይል በማማለል በአገሪቱ ውስጥ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን በማስፋፋት ከሃብት ላይ ሃብትን የማደለብ ተግባር  ነው፡፡

 

እንዲህ ዓይነቱ ወንጀል ከፍተኛ የፍትሕ መጓደልን ያስከትላል። በዚህ የሙስና ዘርፍ በርካታ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ደላላዎች  በሕገ ወጥ መንገድ ከጉቦ ሰጪዎች ቋሚ የሆነ ኮሚሽን ወይም ክፍያ በመቀበል አሠራርን የሚጥሱበት መንገድ ነው፡፡ ይህ በአገሪቱ ፍትሃዊ የሆነ ነጻ የገበያ ውድድር እንዳይኖር በማድረግና በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶችን በማቀጨጭ በአገሪቱ የዕድገት ጎዳና ላይ ቀላል የማይባል ጫና ያሳድራል።


ሦስተኛው የሙስና ገጽታ ደግሞ  በተቋም መልክ የሚካሂድና ሕጋዊ ከለላ ያለው የምዝበራ ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሙስና ተሳታፊ የሆኑ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች  የአገር ንብረት የሚዘርፉበት ሕጋዊ የሚመስል ሰነድ እየተዘጋጀ የሚወራረድበት መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የሙስና ተግባር በርካታ ሰዎችን በዝርፊያው ውስጥ የማስገባት ባህሪ አለው። አንዳቸው ሌላኛውን ከለላ በመሆን የሚጠቃቀሙበት መንገድም ነው፡፡

 

ኅብረተሰቡ በንቃት ሊከታተለው የሚገባው ሌላው የሙስና ገጽታ ደግሞ በንግድ ሥራ ተሰማርተው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ የንግድ ድርጅቶች የመንግሥትን ግብር በተገቢው መንገድ ባለመክፈል የሚፈፀም ተግባር ነው።

 

እነዚህን የንግድ ድርጅቶች ልዩ የሚያደርጋቸው በአገሪቱ በተፈጠረው መልካም የነጻ ገበያ ገብተው በከፍተኛ ደረጃ አትራፊና ተጠቃሚ እየሆኑ ለህዝብ መሠረተ ልማት ግንባታ የሚውለውን የመንግሥት ድርሻ ከሙሰኛ ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር የሚሰሩት የማጭበርበር ተግባር ነው። በዚህም ሕገ ወጥ  ነጋዴዎች ልማታዊ ባለሃብቶችን  ከገበያ የማፈናቀል ተግባራትን ይፈፅማሉ፡፡

 

ከጥቅመኛ ሠራተኞች ጋር በመመሳጠርም ወደ ገበያ መግቢያና ንግድ ማስፋፊያ ካፒታል ተገቢነት በሌለው መንገድ ማግኘት፣ የውጭ ምንዛሪን በሚፈልጉት መጠን ለማግኘት የሚያስችላቸውን የግንኙነት መረብ በመዘርጋት ተፎካካሪዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ መንቀሳቀስም ሌላው የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ነው።


በርካታ ልማታዊ ባለሃብቶች ለውጭ ምንዛሪ እጦት ሲዳረጉ ኪራይ ሰብሳቢዎች በዘረጉት መረብ መሠረት ተጠቃሚ በመሆን በአገሪቱ ፍትሃዊ አስተዳደር እንዳይነግስ ከፍተኛ መሰናክል ሆነው የአገሪቱን ዕድገት በተፈለገው መልክ እንዳይሄድ ወደ ኋላ የሚጎትት ተግባር በመፈፀምና እነሱ ባላቸው ሰፊ ዕድል በመጠቀም ለሥራው ብቃት ሳይኖራቸው ገበያውን ለመቆጣጠር ይሰራሉ። 

 

ልማታዊ ባለሃብት የበላይነቱን እየያዘ ካልሄደ አገሪቱ እያሰበች ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገትም ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው። ልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ ለዚህች አገርና ህዝብ የህልውና ጉዳይ ነው። ፈጣን ልማት ካልተረጋገጠና ፍትህና ዴሞክራሲ በተገቢው ደረጃ ካልሰፈነ የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከማንም የተሰወረ አይደለም። ለዚህም ነው  መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት የአገሪቱ ከፍተኛ አደጋዎች በመሆናቸው መገታት እንዳለባቸው በተለያየ መልክ ጥረት እያደረገ የሚገኘው።

መንግሥት እየወሰዳቸው ካሉ ዐበይት ርምጃዎች መካከል አንዱ ልማታዊ ባለሃብቶችን መደገፍ ነው። በነፃ ገበያ ደንብ መሠረት ለመሽቀዳደም በማለም ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱትን ኢንቨስተሮች በኪራይ ሰብሳቢ ኢንቬስተሮች ድርጊት ተስፋ እንዳይቆርጡና  ከውድድሩ ውጭ እንዳይሆኑ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

 

የንግድ ተሰጥኦ ያላቸውን ሥራ ፈጣሪዎች አዲስ ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚያደርግ፣ የነፃ ፉክክርን መንፈስ የሚያጠናክር፣ በአዲስ ግኝት ላይ የተመሠረተን የንግድ እሴት የሚጨምር፣ ጥሮ ተጣጥሮ የሚመጣ የንግድ ትርፋማነት  እንዲዳብር የማድረግ አቅጣጫን ይከተላል፡፡ ከዚያ ጎን ለጎን   የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትና ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚፀየፍ ትውልድ ለማፍራት በትምህርት ተቋማትና በመገናኛ ብዙሃን በኩል በርካታ አስተምህሮዎች እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ይገኛል።

 

ማንኛውም ዜጋ በአገሩ ያለምንም አድልዎ በነጻነት ሰርቶ ሃብት የሚያገኝበት አሠራርም ተዘርግቷል።  ጥሮ ግሮ ሃብትን ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ከባለሥልጣናት ጋር ተመሳጥሮ በማጭበርበር ለመጠቀም በሚሞክር ማንኛውም ወገን ላይ ደግሞ ተገቢውን ክትትልና ምርመራ በማድረግ ለሕግ የማቅረቡን ተግባር ከኅብረተሰቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል።


መንግሥት ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነት የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብም  ለትግሉ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። በቅርቡ መንግሥት በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ደላላዎች ላይ እየወሰደ ያለውን ቆራጥ ርምጃ ተከትሎ በህዝብ ስሜት ውስጥ ያደረው ተስፋ የጥቆማ መጠኑ ማደጉን ከሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

 

ርምጃውን ተከትሎ እየመጣ ያለው የሕዝብ መነቃቃት የሚያሳየው በመንግሥት በኩል ያለው ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ በሕዝቡ በኩልም ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ቁርጠኝነት መኖሩን ነው። አሁን የሚያስፈልገው ነገር በሁለቱ መካከል ያለውን ቁርኝት ማጥበቅና ማጠናከር ብቻ  ይሆናል። በዚህም ምክንያት ኪራይ ሰብሳቢነትን ጠራርጎ ማስወገድ ቀጣይ ሥራችን እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy