ኪራይ ሰብሳቢዎችን መመከት የዜጎች ኃላፊነትም ነው!
ታዬ ከበደ
መንግስት ሰሞኑን የህዝብን ሃብት በመዘበሩ ግለሰቦች ላይ ክስ ከፍቷል። እንዲህ ዓይነቱ የተጠናረ ተግባር የመንግስት ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም ዜጎች ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመመከት በሚደረገው ትግል ውስጥ ከመንግስት ጎን በመቆም አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በመንግስት አቅም ብቻ የሚፈፀም ነገር ባለመኖሩ ዜጎች የበኩላቸውን ሚና ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡
የዴክራሲያዊ ስርዓት ዋነኛ ባህሪ ራሱን በራሱ ማረሙና ያሉበትንም ችግሮች ማጥራት የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ስርዓቱ ራሱን በራሱ እንዲያጠራም፤ በውስጡ ያለው ህዝብ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመምረጥ ወዘተ. መብቶቹን ተጠቅሞ በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ሂስ ማድረግ ሲችልና ገዥው ፓርቲም ይህን አድምጦ ማስተካከል ይኖርበታል፡፡
ያም ሆኖ የህዝቡን ልማታዊ አደራ ከግብ ለማድረስ መንግስት ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ ጥረቱን ይበልጥ ለማጠናከርም ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተልሞ ከህዝቡ ጋር ደፋ ቀና ማለት ጀምሯል፡፡
ታዲያ ምንም እንኳን የዚህ ታላቅ ሀገራዊ የዕድገት ዕቅድ ፈፃሚው አካል ህዝቡ ቢሆንም፤ ስራው ከግቡ እንዲደርስ የመሪነት ሚናን የሚጫወተው መንግሥት ውስጡን ለልማቱ እንቅፋት ከሚሆኑ ተግባራት ማጥራት ይኖርበታል፡፡ ይህም በአንድ ወገን ለህዝቡ የገባውን ቃል ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችለው ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የተሰጠውን አደራ በላቀ ቁርጠኝነት እንዲወጣ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርለት ይመስለኛል፡፡ ይህን ካልከወነ ግን በውክልና የተሰጠው ውል መሰረዙ አይቀርም፡፡ እናም ኪራይ ሰብሳቢዎችን የማጥራት እርምጃ መነሻው እነዚህ ህዝባዊ ፍላጎቶች እንዲሁም ስርዓቱን ከአደጋ የመጠበቅ ሃላፊነት መሆናቸውን ለማንኛውም ቅን አሳቢ ዜጋ ግልፅ ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ግንዛቤ የመንግሥት መዋቅሮች ለሙስና የተመቻቹ ባይሆኑም፣ በየትኛውም ዴክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ከነባራዊ ክስተት መሆኑን መረዳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ በመሆኑ፤ ከነባራዊ ክስተት የፀዳና ጉድለቶች አይኖሩትም ተብሎ አይታሰብም፡፡
ምንም እንኳን መንግሥት በየጊዜው በወሰዳቸው በርካታ እርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች ደረጃ በደረጃ ለውጥ እየታየባቸው መሆኑ የማይታበይ ሃቅ ቢሆንም፤ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ቅሪት አስተሳሰቦች ሙሉ ለሙሉ ተቀርፈዋል ማለት አይቻልም፡፡ አስተሳሰቦቹ በጊዜ ሂደት የሚቀየሩ እንጂ በአንድ ጀምበር የሚጠፉ ስላልሆኑም በህብረተሰባችን ውስጥ መንፀባረቃቸውና ገቢራዊ መሆናቸው አይቀርም፡፡
የመንግሥት የግምገማ ባህል ሀገራችንን አሁን ላለችበት የዕድገት ጎዳና ያበቃት ነው፡፡ ይህን ዕውነታ ለማስረዳት ሩቅ መሄድ አያፈልግም፡፡ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የተካሄደውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ መጥቀሱ ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ በወቅቱ በአንድ በኩል ስልጣንን የኢኮኖሚያዊ ሃብትና የብልፅግና መሳሪያ በማድረግ ፀረ-ዴክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚሹ ወገኖች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሃብት ምንጭ እንዳይሆን፣ ዴክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብና እንዲዳብር ብሎም የጥገኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዳያገኝ በሚተጉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግምገማና የመድረክ ትግል መካሄዱን እናስታውሳለን፡፡
በእነዚህ ሁለት ፅንፍ አመለካከቶች ዙሪያ በተካሄዱ ግምገማዊ የሃሳብ ፍጭት፤ ስልጣን የጥቂቶች የሃብት ማካበቻ እንዳይሆን እንዲሁም ዴሞክራሲና ዴክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ብሎም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት እንዳያገኝ የታገለው ወገን ነጥሮ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡
ይህም በመንግሥት ከፍተኛ የአመራር እርከን ላይ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ወደ ትክክለኛ ፀረ-ዴሞክራያዊ ጎራቸው ተቀላቅለው የባጥ የቆጡን እየቀባጠሩ ያሉ ጥገኛ ኃይሎች በተግባር እንዲንገዋለሉ አድርጓቸዋል፡፡
ልማታዊ ዴሞክራሲውም በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም አስችሎታል፡፡ ማንም የዚህ ፅሁፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው፤ የተሃድሶው ግምገማ ባይካሄድ ኖሮ ሀገራችን እንዲህ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ ውስጥ አትገባም ነበር፡፡ ህዝቡም በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ተተብትቦ ከኢኮኖሚው ዕድገት በየደረጃው የሚያገኘው ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል ማለትም ዘበት ይሆን ነበር፡፡
መንግስት የሚያካሂደው ማንኛውም ግምገማምና እርሱን ተከትሎ የሚካሄደው የፀረ-ሙስና የሂደት ትግል፤ በምርጫ ወቅትና ማግስት ለህዝቡ የገባውን የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም እመርታ ቃልን በላቀ ቁርጠኝነት ለመፈፀም ያለመ ነው፡፡
ፅንፈኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ግን የትኛውንም የመንግስት ስራ ከመቃወም ወደ ኋላ አላሉም። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መልካም እመርታዎችን በጭፍን ጥላቻ የማውገዝ ዝማሜ ‘ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ እንሰጣለን’ ከሚሉ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ‘ምናልባትም አጋጣሚውን ካገኘን ሀገርን እንመራለን’ በማለት ስልጣንን በሃይል ለማግኘት ከሚናፍቁ ዕንፈኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች ስራ እየሆነ ነው፡፡
በተለይም ጉዳዩ መንግሥት በልማታዊ እንቅስቃሴውና በህዝቡ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ እንቅፋት ሊፈጥር የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ድርጊት ለማዳከም በሚያደርገው አዎንታዊ ተግባራት ውስጥ አፍራሽ ሚና መጫወቱ አይቀርም፡፡
እንደሚታወቀው ኪራይ ሰብሳቢነት ያለ አግባብ የመንግሥት ስልጣንን በመጠቀም ከባለሥልጣኖች ጋር ተሳስሮ በነፃ ገበያው ውድድር ሊታሰብ ከማይችለው በላይ ሃብት የማጋበስ ስራ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ ወገኖች ይህን ነውረኛ ተግባር የህዝቡን ሃብት ከመዝረፍ ጋር በቀጥታ ያገናኙታል፡፡
እርግጥም የዘረፋ ድርጊትን ከኪራይ ሰብሳቢነት ለይቶ መመልከት አስቸጋሪ በመሆኑ፤ አባባሉ እኔንም ያስማማኛል፡፡ እንዴት ቢሉ፤ አንድ ግለሰብ ሊኖረው የሚችለው የመዝረፍ ዕድል ሌላውም እኩል በሆነ ሁኔታ ሊያገኘው ስለማይችል ነው፡፡
መንግሥት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ይሁን ነገ የሚያካሂዳቸው ማናቸውም የፀረ-ሙስና እርምጃዎች የዚህ መሰረታዊ እውነታ ውጤቶች መሆኑን ለመገንዘብ የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው፤ በማንኛውም የመንግሥት የስራ ኃላፊነት ያሉ ግለሰቦች ህዝብን እንጂ ራሳቸውን ለመጥቀም አይደለም ወንበር ላይ የሚቀመጡት፡፡ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ማጋለጥና ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ ይገባል። ህዝቡም ከመንግስት ጎን በመቆም ተግባሩን ማውገዝ ይኖርበታል፡፡