ወጣትና የስራ እድል
ታዬ ከበደ
የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቱ በርካታ የስራ እድሎችን አመቻችቷል። ወጣቱ በመንግስት በኩል የተመቻቸለትን የስራ እድል በአግባቡ በመጠቀም ስራ ጠባቂ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ መሆን ይኖርበታል። ለዚህም ስራን በመፍጠር ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ማስፋት አለበት። ወጣትነት የስራ ወቅት በመሆኑ በአዲስ አመት አዳዲስ ስራዎችን በመፍጠርና የስራ ክቡርነትን በመገንዘብ መጪውን ጊዜ እውን ውጤታማ ማድረግ አለበት።
ሁላችንም እንምናውቀው ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም።
ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራችን ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።
ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቶች የሰጠው ትኩረት የህብረቱን ፍላጎት አስቀድሞ የተገነዘበ ነው ማለት ይቻላል። ግና እዚህ ላይ ‘ወጣቶች ሀገራችን የሰጠቻቸውን ትኩረት እንደምን ሊጠቀሙበት ይገባል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። አዎ! ምንም እንኳን የጥያቄው ምላሽ ሊኖር የሚችለው በወጣቱ ትጋት ውስጥ ቢሆንም፤ እኔም ለመነሻ ይሆኑ ዘንድ ጥቂት ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ለማንሳት እሞክራለሁ።
ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት።
ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል። በአጭሩ ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። ስራ ክቡር ነው የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን አገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።
ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተዋል። ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል።
በዚህ ወቅት አገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው። የተመቻቸን ነገር በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ አደጋው የከፋ ይሆናል። ምክንያቱም ያልተመቻቸን ነገር ለመከተል እድል ስለሚከፍት ነው።
ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንደመሆናቸው በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለመስራት ታቅዷል፤ በመጪው አዲስ ዓመት።
የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።
የሀገራችን ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መረጃዎች ያስረዳሉ።
በዚህም በተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቧል።
በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የወደፊት የሀገራችን ተስፋ በሆኑ አምራች ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ በኢንዱስትሪዎችና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የወደፊት የሀገራችን ልማታዊ ባለሃብቶች መፍለቂያ እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃዎች ይገልፃሉ።
ምስጋና ለልማታዊው መንግስት ምቹ ሁኔታ ፈጣሪነት ይግባውና ወጣቱ የነገ ባለተስፋ ሆኗል። ከሰማይ በታች ይህን ተስፋውን የሚያመክን አንዳችም ሃይል የለም። እናም ወጣቱ ይህን ብሩህ ተስፋ በሚገባ መመልከት አለበት። በአንክሮም ማጤን ይገባዋል።
ትናንት የነበረው ተጠቃሚነቱ ነገም ሆነ ከነገ በስቲያ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንጂ የሚቋረጥ አይደለም። የወጣቱ ተጠቃሚነት የሚቋረጠው በፅንፈኞች የጨነገፈ አዕምሮ ውስጥ ብቻ ነው።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥ በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ወጣቱን ከተጠቃሚነት ጎራ ያፈናቀለውና በተገቢው መንገድም ከልማቱ ተጠቃሚ አላደረገውም። ይህ ሁኔታም ወጣቱ ለፅንፈኛ ዲያስፖራዎች የተሳሳተ ተልዕኮ እንዲጋለጥ አድርጎታል።
ይህ የትናንት ታሪክ ነው። ዛሬ ላይ አይሰራም። አሁን ደግሞ አዲስ መድረክ ተፈጥሯል። የወጣቱ ስራ ፈላጊ ድምፅ ይበልጥ ሰሚ፣ ይበልጥ ተደማጭ ሆኖ ገንዘብም ተመድቦለታል። በአዲስ ዓመት በአዲስ ጎዳና ላይ ነገም የተምማል። ይህን ሰፊ የስራ እድል የያዘ ጎዳና ማንም ሊዘጋው አይችልም። በኢትዮጵያችን የከፍታ ማማ ላይ የወጣቱ ተጠቃሚነት ይበልጥ ይጎለብታል። እናም ወጣቱ ለነገ የስራ እድል ተስፋው ዛሬ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት መዘንጋት አይኖርበትም።