ወጣቶችና ተዘዋዋሪ ፈንዱ
ዳዊት ምትኩ
መንግስት በፌዴራል ደረጃ ለወጣቶች የመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቧል፤ 10 ቢሊዮን ብር። ከዚህ በተጨማሪም ክልሎች ከበጀታቸው በመቀነስ ወጣቱ የስራ ፈጣሪ እንዲሆን ጥረት እያደረጉ ነው። በዚህም በአሁኑ ወቅት ወጣቶች በተዘዋዋሪ ፈንዱም ይሁን በክልሎች በተመደበው በጀት የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ይህም ወጣቶች ተጠቃሚ በማድረግ ወደ ስራ ገብተዋል። ይሁንና ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንዱን ወጣቶቹ በአግባቡ እንዳይጠቀሙ የተለያዩ የአመፅ ጥሪዎችን እያስተላለፉ ነው። ወጣቱ ግን የመንግስት ስራዎችን ብቻ መመልከት ያለበት ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት መንግስት በየክልሉ ለሚገኙ የሀገራችን ወጣቶች ከስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው። እርግጥም የሀገራችን ወጣት በውጭ የሚኖሩት ሁከት አቀጣጣይ ኃይሎች ከሞትና ከጥፋት ተግባር በስተቀር የፈየዱለት አንዳችም ነገር የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የተጠቃሚነትና የመበልፀግ አጀንዳን የሚመራው መንግስት እንጂ እነዚህ ሃይሎች ባለመሆናቸው ወጣቱ ይህን ሃቅ መገንዘብ አለበት።
እርግጥ የሀገራችን ወጣት አመዛዛኝ፣ አስተዋይ፣ ፍትሃዊና በስሜት አይጓዝም። በተሳሳተ መንገድ አሊያም የችግሩን መንስኤ በውል ካለመገንዘብ ካልሆነ በስተቀር በሁከት ፈጣሪዎች የጥፋት ጎራ ይሰለፋል ማለት አይቻልም። እናም ወጣቱ የውስጥና የውጭ የአመፅና የጥላቻ ጥሪዎችን በሁለት ምክንያቶች ማምከን ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም መንግስት የሚከተለው ልማታዊ አቅጣጫ ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግሮች የመፍታት አቅም ያለው መሆኑን ስለሚያውቅና መንግስት ሁሌም ቢሆን የገነባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው።
እንደሚታወቀው ወጣቱ ባለፉት 15 የፈጣን ዕድገት ዓመታት ውስጥ የመንግስት ልማታዊ አቅጣጫን በሚገባ ተገንዝቧል። ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግስት እየፈታው ነው። እንደ ኦሮሚያ ባሉ ክልሎች ውስጥ ማልማት ካልቻሉ ባለሃብቶች ቦታ በመቀማት ጭምር ወጣቱን ወደ ስራ የማስገባት ተግባር እያከናወነ ነው። ይህ ሁኔታም መንግስት ምን ያህል ለወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ትኩረት የመስጠት ተግባሮች እውን እየሆኑ ነው።
እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ላለፉት 26 ዓመታት በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል።
ከ26 ዓመት በፊት በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው።
ለምሳሌ ያህልም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። እናም ወጣቱ በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል።
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ከድህነት ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ወጣት፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ሁለንተናዊ የጥቅም ተጋሪነቱ የኋሊት ተጎትቶ እንዲሸረሸርበት አይፈልግም።
ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት የትናንት እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ሁከትን በማዳመጥ አይደለም።
በመሆኑም እነርሱ ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውንና ህይወቱን ለመቀየር እየተጋ ያለውን ወጣት በእሳት ለመማገድ የሚሹ የሁከት ኃይሎችን ጥሪዎች ማምከን ይኖርበታል።
ወጣቱ ከሁከቱ ወዲህ ስለ እነዚህ ኃይሎች ባዶና የአሉባልታ አጀንዳ አራማጅነት እንዲሁም ስለ መንግሥት ትክክለኛነት የልማት አቅጣጫዎች የተገነዘበ ይመስለኛል። መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት በዳግም ተሃድሶው ይበልጥ ለማረጋገጥ ወደ ስራ ገብቷል።
ያም ሆኖ ግን ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባቸውን የተስፋ ቃላት ተፈፃሚ አድርጓቸዋል።
አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም። ዛሬም ሰላምን ከወጣቱ ጋር ሆኖ በማረጋገጥ አብዛኛውን ወጣት ወደ ስራ ለማስገባት አቅም በፈቀደ መጠን በፌዴራልና በክልል ደረጃ ፈንድ መድቦ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህ እውነታ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
እርግጥ ባለፉት ጊዜያት ገዥው ፓርቲና መንግሥት የለውጥ አደራጅና ቀያሽ መሆናቸውን ወጣቱ በሚገባ ስለሚያውቅ፤ ማናቸውም ተግዳሮቶች ህዝብ በመረጠው መንግስት እንጂ በሁከት አቀንቃኞች ይፈታል ብሎ ያስባል ማለት አይቻልም።
ምንም እንኳን የሁከት ኃይሎቹ በተቀናጀ ሁኔታ የህዝቡን ብሶቶችና የራሳቸውን አሉባልታዎች በማያያዝ ለማራገብ ቢሞክሩም እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑና የሚምታቱ ፀረ-ልማት ሃሳቦችን እያቀረቡ ለማሳሳት ቢሞክሩም ወጣቱ ጆሮውን መስጠት አይኖርበትም። ዓላማቸው የወጣቱን ሰላም፣ ነፃነትና ተጠቃሚነትን መንጠቅ በመሆኑ ተጠቃሚነቱን ለማስጠበቅ የእነዚህን ሃይሎች ተራ ወሬ ማዳመጥ የለበትም።
የማናቸውም ችግሮች መፍትሔ የሚመነጨው በሀገሪቱ ህዝብ እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ብሎም የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ኃይሎች ባለመሆኑ ሃቁን መገንዘብ ይኖርበታል። እናም መንግሥት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቱ ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመገንዘብ ከእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ ራሱን ማራቅ አለበት።
በአጠቃላይ ወጣቱ ዛሬ በፌዴራል ደረጃ በተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ ሆኗል። እንዲሁም ክልሎች ከመደቡት በጀት መጠቀም ችሏል። ይህ ተጠቃሚነቱም በሚቀጥሉት ዓመታት እጅግ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንግስት ቃል ገብቷል። ስለሆነም ተዘዋዋሪ ፈንዱንም ይሁን የክልሎችን በጀት በአግባቡ በመጠቀም ራሱንና ቤተሰቡን ብሎም ሀገሩን የመለወጥ ተግባር ከወጣቱ የሚጠበቅ ይሆናል።