Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዘመን ተሻጋሪ አመለካከትና ተግባር

0 736

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዘመን ተሻጋሪ አመለካከትና ተግባር

                                                   ቶሎሳ ኡርጌሳ

እነሆ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ካለፉ አምስት ዓመት ሆናቸው። እርሳቸው ዛሬ በህይወት ባይኖሩም፤ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ፣ በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያራምዷቸው ዘመናትን የሚሻገሩ አስተሳሰቦችና ተግባሮቻቸው ሁሌም ሲዘከሩ የሚኖሩ ናቸው። ዛሬም በዚህ ፅሑፍ ላይ አቶ መለስ ከእነዚያ ዘመን አይሽሬ እሳቤዎቻቸውና አፈፃፀማቸው ጋር በወፍ በረር ልቃኛቸው ወደድኩ።

ጊዜ ትናንትን በነበርነት ትቶ ባለ ራዕዩ መሪያችንን ካሳጣን አምስት ዓመታትን ደፈነ። ታዲያ ይህ ከልካይ የሌለው ተፈጥሮአዊ ዑደት እንዳሻው ቢከንፍም፤ አቶ መለስ ለሀገራችን ትተውት የሄዱት ትውልድ ተሻጋሪ የገዘፈ ራዕይ ዛሬም እንደ መሪ የባቡር ፉርጎ ከእኛው ጋር አብሮን ተቀጣጥሎና እኛኑ አስከትሎ በልማት ጎዳና ላይ ሽምጥ መጋለቡን አልተወም— የድህነትን ተራራ እየናደና የብልፅግናን በር ወለል አድርጎ ለመክፈት እየታገለ።

ታዲያ የብልሁና የአስተዋዩ መሪያችን ራዕዩች ከእኛ አልፈው የአፍሪካ ሞዴል በመሆናቸው፤ ተመፅዋችነትን እየተፀየፍን የብልፅግናው ማማ ላይ የማንወጣበት ምንም ምክንያት ያለ አይመስለኝም—እየተመራን የመጣንባቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም የዕድገት መሰላል ላይ ይዘውን ወጥተዋልና። ነገም እንዲሁ መሆኑ አይቀሬ ነው። ነገሩ “የነብርን ጭራ አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም” እንዲሉት ነውና።

እርግጥ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ክስተት ከሆነው ሞት አያመልጥም። ትልቁ ቁም ነገር በህይወት ዘመኑ ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት የሰራው ታሪኩ ነው። በአንድ ወቅት ቤንጃሚን ፍራንክሊን “ከሞትክ በኋላ ስምህ ደጋግሞ እንዲነሳ ከፈለግህ፤ የሚነበብ መፅሐፍ ፃፍ አሊያም የማይረሳ ታሪክ ስራ” ብሎ ነበር።

ታዲያ በእኔ ትንሿ እሳቤ አቶ መለስን ከዚህ አኳያ ስመለከታቸው፤ ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካና ለዓለም የፃፏቸው የታተሙና ያልታተሙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ለሀገራችን፣ ለምስራቅ አፍሪካ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ያበረከቱት ታሪካዊ ስራዎች የዘመን ክስተትነታቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው። አዎ! የህይወት ዘመናቸውን በመሉ ለህዝብ የኖሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለእኛና ለመጪው ትውልድ ትተውልን የሄዱት ታላላቅ አስተምህሮቶችና ስራዎቻቸው የሀገራችንን አስከፊ የድህነት ታሪክ በመለወጥ ላይ ያሉና ወደፊትም የሚለውጡ ናቸው።

ሀገራችንም ሆኑ ዜጓቿ መቼም የሚረሷቸው አይደሉም። አዎ! ሁሌም ከህሊናችን ጓዳ ውስጥ አይጠፉም—የነገ ሰው መሆን እንዴት እንደሚቻል ያስተማሩን በመሆናቸውም፤ “ነገነታችንን” ስናሰብ ሁሌም እናስባቸዋለን፤ እናስታውሳቸዋለን። ምንም እንኳን እኔ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ምንም እንኳን በዚህች አጭር መጣጥፌ ስለ ታላቁ መሪ ፈርጀ ብዙ ውለታዎች የመፃፍ አቅሙ ባይኖረኝም፤ ለእኛና ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ካበረከቷቸው በርካታ ገፀ በረከቶችንና ተግባሮቻቸውን በጥቂቱም ቢሆን እንዲህ ማስታወስ ይገባል።

እንደሚታወቀው የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የነበሩት እኚህ ታላቅ መሪ በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን እያፈለቁ ለሀገራችንና ለዓለም ሲያበረክቱ ነበር፡፡ በዚህም የመላው አፍሪካ ድምፅ በመሆን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ወደ ማግኘትም የተሸጋገሩ ነበሩ፡፡ ታላቁ መሪ አፍሪካውያን በመሠረታዊ የጋራ ጥቅም ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲወስዱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአህጉሪቱ ቃል አቀባይ ሆነው ውጤት ማስገኘት የቻሉ ጀግና ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡

በተለይም በየዓመቱ በአማካይ በሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይጨምራል ተብሎ በሚጠበቀው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ “አፍሪካ ዋነኛዋ ተጎጂ ናት” በማለት የምዕራቡ ዓለም በኢንዱስትሪ ሳቢያ ለፈጠረው የካርቦን ልቀት ለአህጉሪቱ ካሣ እንዲከፍል በመጠየቅ ከአፍሪካ ህዝቦች ባሻገር፤ ከራሳቸው ካደጉት ሀገራት ጭምር አንቱታን ለማትረፍ የበቁ የሀገራችን ዕንቁ ሰው ነበሩ፡፡

ይህን እምቅ አቅማቸውንና ክህሎታቸውን የተገነዘበው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም የበለፀጉት ሀገራት በቡድን ስምንት እና በቡድን ስምንትና 20 ስብሰባዎች ላይ ከሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጋበዙ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እናም ቀደም ሲል በረሃብና በጦርነት የምትታወቀውን ሀገራችንን ስም በአዲስ የዲፕሎማሲ መንገድ አራማጅነት እንዲቀየር ለማድረግ የቻሉ የሀገራችንና የአፍሪካ ባለውለታ ናቸው፡፡

አቶ መለስ ወትሮም ግጭትና አለመረጋጋት በማይለየው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ካበረከቱት ወደር የሌለው ተግባራቸውም ይታወሳሉ፡፡ ታላቁ መሪ የኤርትራ መንግሥት ሀገራችንንና ምስራቅ አፍሪካን የጦርነት አውድማ ለማድረግ የቀመረውን የሽብር ስትራቴጂ በቅርበት በመከታተልና ብቃትና ብስለት ባለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እየተመሩ የአስመራው አስተዳደር ለመፍጠር የሞከረውን ቀጣናዊ ቀውስ ለማርገብ በቁርጠኝነት የሰሩ አፍሪካዊ አባት ናቸው፡፡

ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ሰብዓዊ ጥፋት ያስከተሉ ጦርነቶች የተካሄዱበትን ይህን ቀጣና ማረጋጋት ቀላል ባይሆንም፤ ታላቁ መሪያችን ግን ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆኑ አካሄዶችን በሳል በሆነና ብቃት ባለው አካሄድ እየተመሩ ያጋጥሙ የነበሩ ፈተናዎችን በድል ተወጥተዋል፡፡

አቶ መለስ አሸባሪነትና አክራሪነት በቀጣናው እንዳያቆጠቁጥና ምስራቅ አፍሪካ ከፅንፈኞች ስጋት ነፃ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ መሪ ናቸው፡፡ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት መንግሥት አልባ በነበረችው ሶማሊያ የመሸገው “እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” በወቅቱ በሀገራችን ላይ ደቅኖት የነበረውን ግልፅና ድርስ አደጋ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ሰማይ ላይ እንዲያንዣብብ ያደረገውን የጦርነት ደመና ብስለት በተሞላው ዘዴ ማስወገድ የቻሉ መሪ ናቸው።

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በሱዳን- ዳርፉር የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ የሱዳን መንግሥትና የደቡብ ሱዳን ነፃነት ንቅናቄ መካከል “ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት” እየተባለ የሚጠራውን ሰነድ እንዲፈራረሙ ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርገዋል። እንዲሁም ለሰላም ካላቸው ፅኑ ፍላጎት በመነሳት በዳርፉር የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ጥላ ስር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሰላም አስከባሪነት እንዲሰማራ በማድረግ በዚያች ሀገር መረጋጋት እንዲፈጠር ጥረዋል። እናም በእነዚህ ቀጣናዊ ተግባሮቻቸው በአፍሪካ ህዝቦች ዘንድ ታላቅ አክብሮትን ማግኘት የቻሉ አርቆ አስተዋይ መሪ ናቸው።

ከታላቁ መሪያችን የዲፕሎማሲ ተግባራት ውስጥ የማይረሳው ሌላኛው ታላቅ ክንዋኔ የሰላም ዲፕሎማሲ አንዱ ነው። አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት የመሪነት ዘመናቸው ሀገራችን ለአፍሪካ ሰላም መከበር በቁርጠኝነት እንድትንቀሳቀስ ያስቻሉ ናቸው፡፡

ታላቁ መሪ ለ21 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመሩ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በላይቤሪያና በሱዳን ዳርፉርና በአብዬ ግዛቶች መከላከያ ሠራዊታችንን በማሰማራት ለአፍሪካውያን ሰላም መረጋገጥ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ የተጉ የአፍሪካዊያን ተቆርቋሪ ነበሩ፡፡ በእርሳቸው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነት የተሰማራው ሰራዊታችንም የተሰጠውን ግዳጅ በብቃትና በፍጹም ወታደራዊ ዲስፕሊን በመታገዝ የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

እርግጥ እኚህ ባለራዕይ፣ የአፍሪካ ኩራትና ዲፕሎማት እንዲሁም ዓለምን ያስደመሙ በሳልና አርቆ አስተዋይ መሪ ዛሬ በህይወት የሉም። አምስተኛ ዓመት ሙት ዓመታቸው እየተዘከረ ነው። ይሁንና የሀገራችንን ስም በዓለም አደባባይ የማደስ፣ የአፍሪካን ዘላቂ ጥቅሞች የማስጠበቅ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ገንቢ ሃሳቦችን የማቅረብ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ስራዎቻቸው ግን ዛሬም ከእኛ ጋር ናቸው፡፡

አዎ! አቶ መለስ እውነትን፣ ትዕግስትን፣ አስተዋይነትን፣ ፅናትን፣ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ተዝቆ ከማያልቀው ዕውቀታቸው ሳይሰስቱ አስተምረውናል። ሰው የመሆን ፊደልን አስቆጥረውናል። የውርደታችንን ካባ ገፍፈው ቀና ብለን እንድንሄድ አድርገውናል። ሌላ…ሌላም።…ምኑ ተዘርዝሮ ያልቃል።

ሁሌም እናመሰግናቸዋለን። እንወዳቸዋለን። ሁሌም በልባችን ማህደር ውስጥ ከትመናቸው እንዘክራቸዋለን። እርግጥ አርቆ አሳቢው መሪ በሞት ከተለዩን አምስት ዓመት ቢሆንም፤ እርሳቸው ያቀበሉንን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ አጭር ሩጫ ዱላ ተቀብለን ራዕያቸውን ዕውን ለማድረግ በእልህና በወኔ ውስጥ መሆን ይኖርብናል።

እናም እኛ የአዲሱ ትውልድ አካላት የአቶ መለስ የመንፈስ ልጅ ሆነን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትልሞቻቸውን በእልህ ሰንቀን የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርብናል። በዘመን ተሻጋሪ አስተሳሰባቸውንና ተግባሮቻቸውን እየደመቅንና እየፈካን የሀገራችንን ህዳሴ እውን ማድረግ ይጠበቅብናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy