Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈን መሪ ስንዘክር ከተፀናወተን

0 293

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈን መሪ ስንዘክር ከተፀናወተን

የሃሳብ ድህነት ተፈውሰን ሊሆን ይገባል!!

ስሜነህ

 

የታላቁን መሪ መለስ ዜናዊን ህልፈት አምስተኛ ዓመት የመታሰቢያ ቀን ”የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ” በሚል መሪ ቃል  በመላ አገሪቱ በችግኝ ተከላ፣ በፓናል ውይይትና በመሳሰሉት ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው ።

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት በመፈተሽ ዋነኛ ጠላታችንን በግልጽ ለይተው ያስቀመጡ ጥበበኛ መሪ ስለመሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ነው። መለስ ዋነኛ ጠላታችንን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል በሳይንሳዊ ዘዴ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርጸጾ ወደተግባር እንዲገቡ ያደረገና አፈጻጸማቸውንም በመከታተል ረገድ ለዚህች ሃገር ያበረከታቸው አስተዋጽኦዎች እንዲህ በቀላሉ የሚታዩ እንዳልሆነም አለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ የፖለቲካ ልሂቃኑ መስክረዋል ።

ስለዋና ጠላታችን ድህነት ምንነት በማስገንዘብና በማስረጽ በማክሰሚያ ስልቶች ላይ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የታገለው መለስ ካለፈ አምስት አመታትን አስቆጠረ።  

በታላቁ መሪ በተቀረጹት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች  እና በሰጠው አመራር ምክንያት ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ከድህነት ወለል መውጣት በመቻላቸው ተረጋግጧል። የአገራችን እድገት ቀጣይነትና ዘለቄታ ሊኖረው የሚችለው የሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተግባር ሲረጋጥ ብቻ መሆኑን ከልብ በመቀበል እና ሌሎችንም በማሳመን ለተግባራዊነቱ ሙሉ ህይወቱን የሰጠ የህዝብ ልጅ ስለመሆኑም የአገራችን ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አቀፍ መሪዎችም የተስማሙበት ጉዳይ ነው።

በእርስ በርስ ጦርነት ትታወቅ የነበረችው አገራችን አንዣብቦባት ከነበረ የመበታተን አደጋ ተላቅቃ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት፣ እጅግ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ያለች፣ በእሷ አቅም ፈጽሞ አይቻልም የተባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ የምትገኝ እና በዓለም አቀፍ  መድረኮች ተሰሚነቷ እየጨመረ ያለች አገር መፍጠር የተቻለው በታላቁ መሪ ብልህ አመራር ነው።  

የመለስን ባለራዕይነትና የለውጥ ፈላጊነት የሚያመላክተው  ትልቁ አብነት ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስርት ዓመታት የበለፀጉ ሃገሮችን ጎራ እንድትቀላቀል ያስቀመጠው ራዕይ ነው፡፡ ይህ ራዕይ ኢትዮጵያ ካለችበት የድህነት ሁኔታ በተሟላ ደረጃ የምትላቀቅበትና የዳበረ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለቤት የምትሆንበት ራዕይ መሆኑን እንኳንስ እኛ ዓለም አቀፉ ማህበረሠብ የመሠከረው ሃቅ ነው፡፡ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱም የዚሁ ራዕይ አካል ነው፡፡  

 

የኢኮኖሚው እድገት አመላካች የሆነው የኢንቨስትመንት መስፋፋት ተከታታይነት ባለው መልክ ላለፉት ዓመታት ሳያቋርጥ እያደገ በመምጣቱ ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር የሃገር ውስጥ ምርትና አገልግሎት አቅርቦት እንዲሁም ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች መጠን እንዲጨምር ማስቻሉ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ አገራችን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሚባሉ የአፍሪካ ሃገሮች አንዷ መሆኗም የሚካድ አይደለም፡፡

ይህንኑ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሃገር መሆኗን የሚመሠክሩት ሁሉ በምክንያትነት የሚያነሱት ደግሞ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ፣የሚያበረታታ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ፣የተረጋጋና በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ሃገር መሆኗ እና  በመለስ የፖሊሲ አመንጭነት እና አመራር ሰጪነት  በተስፋፋው የመሠረተ ልማት ግንባታ ነው፡፡

የገበያ ኢኮኖሚ በተሟላ አኳኋን እንዲሰራ ቀልጣፋ መሠረተ ልማት ያስፈልገዋል፡፡ ገበያ ራሱ አንድ ማህበራዊ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የገበያውን ስርዓት ለማቆም የሚያስፈልጉ እጅግ ብዙና የተለያዩ ተቋሞች ከመሰረተ ልማቱ ጋር በማሣለጥ የግል ባለሃብቱን ተወዳዳሪ ይሆን ዘንድ የመለስ አመራር ሰጪነት ትልቅ ስፍራ እንደነበረውም ይታወቃል ፡፡

በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን በጠንካራ የውድድር መንፈስ የሚያቀርቡ ተቋሞችና ድርጅቶችም በመለስ አመራር ሰጪነት ተገንብተዋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በበለፀጉት አገሮች ከሞላ ጎደል ተሟልተው ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም በእነዚህ አገሮች የሚኖረው  የገበያ  እድገት መጠኑና ጥልቀቱ ውሱን ቢሆንም የኛውን ሃገር የግል ባለሃብት ግን እንደቀድሞው ጊዜ ከመወዳደር የሚያግደው አይደለም፡፡ ወይም አሁንም የተገነቡት ተቋማት በዓለም ገበያ የግል ባለሃብቱን በመዘረር የሚያቆሙት እንዳይሆን መሰረቱን ጥሎልናል፡፡

የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ በሃገራችን እድገት ጊዜያዊና ግን ደግሞ የምንፈልገውን ቴክሎጂ ለማምጣትም ሆነ የሥራ እድል በመፍጠር ረገድም ወሳኝ ቢሆንም በዋናነት ግን ዘላቂነት ላለው ልማት ወሳኝ የሚሆነው የሃገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት መሆኑን አስምሮበት ያለፈው መለስ ነው፡፡

ለመለስ ከድህነት በላይ አዋራጅ ነገር እንደሌለ፣ “በድህነት የተቆራመዱና ጠኔ እየገረፋቸው የሚኖሩ፣ የሚለብሱት አጥተው በእርዛት የሚቸገሩና መጠለያ አጥተው ባረጁ ጎጆዎች ተቸፋፍገው የሚያድሩ ዜጎች ሃገር ይዘን እንቅልፍ ተኝተን ልናድር አይገባም” ለሚለው አቋሙ ሌት ተቀን የሚተጋ ስለመሆኑም በህይወት ታሪኩ ላይ በግልጽ ተመልክቷል።

መለስ ገና ከጠዋቱ አገራችን ኢትዮጵያ ብዙሃን ብሔሮችና ሃይማኖቶችን ያቀፈች እንደመሆንዋ ልዩነታችንን አክብረን የተዘነጉ፣ የተናቁ ማንነታቸውንና እኩልነታቸው እውቅና አግኝቶ የአገሪቷ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ነፃና ህያው አካል እንደሆኑ በሰፊው ስለመሥራቱም የትግል አጋሮቹን ጨምሮ የስራ ባልደረቦቹ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።  

በአርሶ አደሩ ጓሮ ስለአርሶ አደሩ ንቃተ ህሊናና የግብአት አጠቃቀም ሲባል የተመደቡትን የልማት ሰራተኞች፤ ስለ አርሶ አደሩ ጤናና ጉልበቱን በማሳው ላይ የማሳለፍ ሰፊ ጊዜ ሲባል በየቀየው የተመደቡትን የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች፣ ስለ አርሶ አደሩ አቅም መጠናከር ሲባል በየወረዳው ያሉ የአነስተኛ ብድር አገልግሎት ተቋማትን እና የህብረት ስራ ማህበራት መቋቋማቸው መለስ የጸነሰው የፖሊሲ ጉዳይ  ነው፡፡

መለስ የቀየሰው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በግብርና ስራ ላይ የተሰማራውን የሰው ሃይል በትምህርትና ስልጠና የላቀ ደረጃ ላይ በማድረስ፣ ይህ የግብርና ሙያው የዳበረ የሰው ሃይል የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ስልቶችን እንዲጠቀም በማድረግ ላይ  ያተኮረ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ የመስኖ ልማትን፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የግብርና ምርቶችን፣ በውስን መሬት የላቀ የግብርና ምርት ለማስገኘት የሚችሉ አማራጮችን ሁሉ አሟጦ የመጠቀም የፖሊሲ አቅጣጫ ስለመሆኑም አርሱን የሚዘክሩ ድርሳናት ያመለክታሉ።

ታላቁ መሪም ራዕያቸው ከድህነት መውጣና ድህነትን ማሸነፍ ነበርና ዘርፉን ከመካከለኛና ከረጅም ጊዜ አንፃር ሃገሪቱ ባላት ውስን ካፒታልና ቴክኖሎጂ በመጀመር ደረጃ በደረጃ የካፒታልና የቴክኖሎጂ አቅምን በማጠናከር በማያቋርጥ ፈጣን የዕድገት ዑደት ውስጥ በመገንባት ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችል ከብዙ ሃገሮች ተሞክሮ እና ከሃገራችንም ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የተረዱት ታላቁ መሪ፤ በ2003 ዓ.ም ዘርፉን በተመለከተ አዲስ ስትራቴጂ በመንደፍ መሠረተ ሠፊ የሆነ ንቅናቄ እንዲፈጠር በማድረግ አሻራቸውን አኑሮ  አልፏል፡፡

መለስ  አፍሪካዊ መሪ… ወዘተ የሚሉ ስያሜዎችን ያተረፉለትን የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑም ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ ምርቶች ዋጋ እንዲሻሻል፣ ወደ አፍሪካ የሚፈሰው ኢንቨስትመንት፣ ብድርና እርዳታ እንዲጨምር፣ አፍሪካውያን በአየር ንብረት መዛባት ለሚደርስባቸው ጉዳት ማካካሻ እንዲያገኙ እንዲሁም የዓለም የንግድ ስርዓት ለአፍሪካ እድገት የሚያመች እንዲሆን ለማድረግ በተገኙት መድረኮች ሁሉ ታግሏል፡፡ ትግሉንም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር በሠጡት ሽፋን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዳሴው ግድብ ሁነኛ ማሳያ ነው።

 

ከዚሁ ጋር  የተያያዘውና የዲፕሎማሲውን መስክ በተመለከተው ጉዳይ  ኢትዮጵያ ዓለም እየተገዛበት ላለው የሠጥቶ መቀበል መርሆ እስከ ጥግ ድረስ የምትሄድና ለጋራ ብልፅግና የምትሠራ ሃገር፤ ዓላማዋም ከድህነት መውጣት መሆኑን ያመላከተና ትርፋማነታችንን ያረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡በዚህና በሰጥቶ መቀበል ላይ በተመሰረተው የመለስ ራዕይ መነሻ በርካታ የውጭ ሃራት መሪዎችና አለም አቀፍ ኩባንያዎች ሃገራችንን መጎብኘታቸውና በርካቶቹም ኢንቨስት ለማድግ ችለዋል።  

ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማምጣትና በኢኮኖሚውም መስክ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላትን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነች ትገኛለች። የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች በማሳካት ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ እየተደረገ ያለው ጥረትም በሁሉ ዘርፍና በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው። በዚህ ረገድ መንግስት የሚጠበቅበትን ፖሊሲዎችና ስትራተጅዎች ነድፎ በተግባር ላይ እንዲውሉ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ሲሆን በተለይም በሶስት ዙሮች ተከፍሎ የሚፈፀም የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተዘጋጅቶ ሁለታኛው በከፊል ተገባዷል።

ይህን የመሰለ ድንቅ ራእይ ያስቀመጠልንን መሪ ስንዘክር ባሳለፍናቸው አመታት ከመለስ ራእይ አኳያ የሰራናቸውን በመፈተሽ ጭምር ሊሆን ይገባል።በየአመቱ ፓናልና የችግኝ ተከላ ማከናወን ግብ አይሆንም። መለስ ጀምሮት የነበረውና በጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው የውጪ ንግድ አፈጻጸማችን ላለፉት ሁለት አመታት ስለምን አሽቆለቆለብን ብሎ መፈተሽ ከመለስ መታሰቢያ ጋር አብሮ ሊታይ ይገባዋል። በመለስ ራእይ በዚሁ ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረ ያለውን የወጪ ንግድ ትራንስፖርት ችግር መቅረፍ እና የሎጀስቲክሱንም ሆነ የአገልግሎት መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋትና ተደራሽነቱን ማረጋገጥ ሲገባ ዛሬም የኋልዮሽ መሆኑ ሊያጠያይቀን ይገባል።  ።

ግዙፍ የማዳበሪያና የሥኳር ፋብሪካዎቻችን በተመለከተ በመለስ ራዕይ መርሆ ልዩ ትኩረት መስጠት የሚገባ እንደሆነ በመጀመሪያው አመት የመታሰቢያ ቀኑ የተወሳ ቢሆንም አለመሳካታቸው ሳያንስ የሙስና ምንጭ ሆነው የመገኘታቸው ምክንያትም ስለመለስ ከላይ የተመለከቱ ትጋቶች ሊፈተሽ ይገባል።  

ይህን  ዕውነተኛ የህዝብ ልጅ ስንዘክር በእርሱ ቁርጠኛ አመራር በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገራችን የተመዘገቡትን ትላልቅ ድሎች ለማስቀጠል፣ ብሎም በእርሱ ዋና መሃንዲስነት የተጀመረውን የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ህዳሴ ከዳር ለማድረስ ያላስቻሉ ማነቆዎችን እያነሱ በመጣልም ጭምር እንጂ ችግኝ ተከላ ለብቻው የሚሆነው ከእርሱ እራእይ በተቃራኒ ላይ ለቆሙ ሃይሎች መደበቂያ ዋሻ ማበጀት ነው 

አገርና ህዝብን መውደድ የሚገለጸው ለአገርና ለህዝብ በሚከፈል መስዋዕትነት እንጅ ሰሞኑን እንዳየነው በጆንያ የተሞላ ብር ላይ ተኝቶ ችግኝ በመትከል ሊሆን አይገባም። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩልነት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ዘላቂ ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና ሲል ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ የከፈለው መስዋዕትነት አሁን ላለው ትውልድ በአርዓያነት ሊወሰድ የሚችለው የራእያቸው ተረካቢ የሆኑ ጓዶቻቸው በእርሳቸው ልክ ሰርተው ሲያሳዩን እንጂ እያወሩ በተግባር የኪራይ ሰብሳቢነት ሰለባ ሲሆኑ አይደለም።ይልቁንም በመለስ መታሰቢያ አስባብ አንዳንዶች ከየፓናሉና ችግኝ ተከላው ላይ የኪራይ ሰብሳቢነት መረባቸውን የጣሉ መሆኑን በመረዳት እና በአንክሮ በመከታተል ሊሆን ይገባል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy