Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝብ ጥያቄዎች በመንግስት እንጂ በፅንፈኞች አይመለሱም!

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብ ጥያቄዎች በመንግስት እንጂ በፅንፈኞች አይመለሱም!

                                              ቶሎሳ ኡርጌሳ

በየትኛውም ሀገር ውስጥ ጊዜያዊ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ነባራዊም ናቸው። የሰው ልጅ በሚያደርጋቸው ማህበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ ግጭት መፈጠሩ ባህሪያዊ ነው። ሆኖም ህግና ስርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ ግጭቶች የሚፈቱበት የየራሳቸው አግባብ አላቸው። ከዚህ አኳያ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውም ጊዜያዊ ችግሮች ህግና ስርዓትን ጠብቀው ምላሽ የሚያገኙ ናቸው።

እናም ሀገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህዝብ የተዋቀረው፣ በህዝብ ያደገውና የጎለበተው እንዲሁም በህዝብ እየተገመገመ ከስህተቶቹ እየተማረ በመጣው ብሎም ተግባሮቹን ሁሉ ከህዝብ ተጠቃሚነት አኳያ በሚያከናውነው በኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው። መቼም ቢሆን ለኢትዮጵያ ጠላቶች በሚላላኩና ባደሩ  ፅንፈኞች ምላሽ ሊያገኝ አይችልም።

በዚህ መሰረትም የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት የመሳሰሉ ችግሮች እንዲሁም ሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነው የቀን ገቢ ግምት ትመና ቅሬታዎች ካሉ መፍትሔ የሚያገኙት መንግስትና ህዝቡ በጋራ በሚያደርጉት ውይይትና መግባባት እንጂ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎችን የሁከት አጀንዳ በሚያራግቡ ፅንፈኞች አለመሆኑን ህብረተሰቡ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል። እናም ሁከትንና ብጥብጥን እዚህ ሀገር ውስጥ ለመፍጠር የሚሹ ሃይሎችን ተራ አሉባልታ ባለመስማት ሁሉንም ችግሮች ከመንግስት ጋር መፍታት እንደሚቻል ግንዛቤ መያዝ ይገባል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁከት ተከስቶ የተጀመረው ልማትና እድገት እንዲቀለበስ ከሀገራችን ጠላቶች መልዕክት ተቀብለው ከሚያቀነቅኑ ሃይሎች ውስጥ አንዱ ራሱን ግንቦት ሰባት በማለት የሚጠራው የሽብር ቡድንና ኢሳት የተሰኘው የአሉባልታ መንዣ ጣቢያው ይጠቀሳሉ።

ግንቦት ሰባት የተሰኘው የሁከት አምላኪዎች ቡድን ምን ያህል ሀገሩን ከመሸጥ የማይመለስ ባንዳ መሆኑን ከትናንት ዳራዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹን ብቻ ነቅሶ መመልከት ይቻላል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቡድኑ በሙባረክና በሙስሊም ወንድማማቾች የስልጣን ዘመን በተላላኪነት ያልቧጠጠው ጉዳይ የለም። የሽብር ቡድኑ መሪ ብርሃኑ ነጋ ከዚህ አኳያ ተጠቃሽ ናቸው። እርግጥ የግለሰቡ የትላንት ዳራ ሲፈተሽ ስብዕናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ሃቆች ስፍር ቁጥር የላቸውም።

ከትላንት እስከ ዛሬ ድረስ የኤርትራ መንግስት ተላላኪና ተወርዋሪ ድንጋይ ከፍ ሲልም ግብፅ ድረስ እንደ ውሃ ቀጂ በመመላለስ ተንቀሳቅሰው አንዳችም ፋይዳ ያላስገኙት አሸባሪው ግለሰብ፤ በሙባረክና በሙስሊም ወንድማማቾች የስልጣን ዘመን ሀገራዊ ክህደታቸውን አሳይተውናል—የህዳሴው ግድብ ላይ አሜኬላ እሾህ ሆነው በመቆም ለባዕዳን ቃል ገብተዋልና።

ኢሳት የተሰኘውና ብሔር እየለየ የሀገራችን ህዝቦች ለማተራመስ የሚከጅለው ጣቢያም ኢትዮጵያ ውስጥ እሳት ለመለኮስ ጥረት ያላደረገበትን ቀን አላስታውስም። ዳሩ ግን በአሉባልታ ነፊነት ከተፈጠረበት ዕለት አንስቶ ከአስመራው አስተዳደርና ከግብፅ ተቋማት ጋር ሆኖ በመዶለት ለመፈፀም ያሰባቸው እኩይ ሴራዎች ሁሉ ከንቱዎች ሆነው ቀርተዋል።

ከግንቦት ሰባት ጋር አንዳንዴ በመጣመር ሌላ ጊዜ ደግሞ በመለያየት የሚሰራው ጃዋር መሃመድ ሌላኛው ሁከት ለመፍጠር የሚሯሯጥ ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ ‘የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ’ እየተባለ በሚጠራው ጣቢያውና በፌስ ቡክ ላይ በሚያሰራጫቸው ሀገርን የሚያምሱ ወሬዎች የዚህ ሀገር ልማት እንዳይሳለጥ የሚሰራ የፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ ነው። ከአንዳንድ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ገንዘብ በገፍ እየተቀበለ ጥቂት ፅንፈኞችን በማሰማራት በየማህበራዊ ሚዲያው አሉባልታን ከመንዛት አልተቆጠበም። አንዳንድ ወገኖችም ሳያውቁ የዚሁ አሉባልታ ሰለባ መሆናቸው የቀሩ አይመስለኝም።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚነትና በቀን ገቢ ግብር ትመናው ላይ እንዲሁም መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ግለሰቦችን በህግ ጥላ ስር ሲያውል ግንቦት ሰባት ከነ ጣቢያው ጃዋርም ከነ ጣቢያው ሲነዙት የነበረው አመለካከት ምን ያህል ተልዕኮ ከአንድ ማዕከል እየተሰጣቸው እንደሚሰሩ አረጋጋጭ ሆኗል።

ሁለቱም ሁከት አምላኪ ሃይሎች የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረውን ህገ መንግስታዊ ሁኔታ በማጣመምና ለኦሮሚያ ህዝብ ጠቃሚ እንዳልሆነ በማስመሰል የአዞ እንባቸውን ሲያነቡ ተስተውሏል። ዳሩ ግን ይህ የአዞ እንባቸው የኦሮሚያ ክልልና ህዝብ ተጠቃሚ ስላልሆኑ ሳይሆን፤ መንግስት የህዝቦችን ጥያቄዎች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ስለመለሰ አጀንዳ ስላሳጣቸው ነው። ይህ አጀንዳ ባለመኖሩ እነርሱ ህዝቡን ለሁከት የሚቀሰቅሱበት ምክንያት ስለሚጠፋባቸው ነው።

የቀን ግብር ትመናን በተመለከተም ሁለቱም ሁከት አምላኪ ፅንፈኛ ሃይሎች “ግብር አትክፈሉ” ከማለት ጀምሮ፤ ሱቃችሁን ዘግታችሁ አድማ ምቱ እስከሚሉ ቅስቀሳዎችን ሲያከናውኑ ነበር። ሀገር ቤት ያልተፈጠረን ነገር ሁሉ ፈጥሮ በማውራት ጭምር በቀን ገቢ ግመታው ስራ ላይ እንቅፋት ለመፍጠር ሞክረዋል። መንግስት ግን እዚህ ሀገር ውስጥ የአጀንዳው ባለቤትና ችግር ፈቺው እርሱ መሆኑን ከህብረተሰቡ ጋር በመተማመንና በመወያየት በግብር ትመናው ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን እየፈታ ነው። ለአብነት ያህልም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የ “ሐ” ግብር ከፋዩች 99 በመቶ ቅሬታ መፈታቱን መጥቀስ ይቻላል።

መንግስት ኪራይ ሰብሳቢዎችን በቁጥጥር ስር ሲያውል የተስተዋለውም ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም ሁከት ናፋቂ ፅንፈኞች ‘ኪራይ ሰብሳቢነት ለምን ይነካብናል?’ በሚል ስሜት ነው መሰለኝ፤ ጉዳዩን አምርረው ተቃውመዋል። በእነርሱ አስተሳሰብ የሚጠሉት ያለ አንዳች መረጃና ማስረጃ ፖለቲከኛ ካልታሰረ በስተቀር የመንግስት ስራ ትክክል አይሆንም።

ዳሩ ግን እዚህ ሀገር የሚከናወነው አጀንዳ ባለቤት መንግስት እንጂ እነርሱ አይደሉም። የዚህን ሀገር ችግር የሚቀርፈው መንግስት እንጂ እነርሱ ባለመሆናቸው፤ መንግስት መረጃና ማስረጃ ያገኘባቸውን ማናቸውንም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ያውላል። ሆኖም በፅንፈኞች አጀንዳ ሊጓዝ አይችልም። በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው የህዝብን ሃብትና ንብረት እስከዘረፉ ድረስ ከተጠያቂነት የሚያመልጥ ሊኖር አይችልም። ይህ ከትናንት እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ የመንግስት አቋም ነው። እናም የፅንፈኞቹ አሉባልታ የማጧጧፍ ጥረት ከቁራ ጩኸትነት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።

በጥቅሉ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት እዚህ ሀገር ውስጥ ጊዜያዊ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ነገር ግን ችግሮቹ ከመንግስት ጋር በመነጋገር የሚፈቱ እንጂ በፅንፈኞች ህገ ወጥ አካሄድ እልባት የሚያገኙ አይደሉም። መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ለህዝብ የገባውን ቃል እንዳላጠፈ ሁሉ፤ ዛሬም ይሁን ነገ ይህን ቃሉን አያጥፍም። እስከዛሬ ያከናወናቸውን እጅግ በርካታ ጉዳዩች ትተን የሰሞኑን የቀን ገቢ ግብር ትመናን ጉዳይ ብቻ በምሳሌነት ብንመለከት እንኳን፤ የቀን ገቢ ግብር ትመናው በግምት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ቅሬታን ከነጋዴው ህብረተሰብ ጋር በመሆን እንፈታለን ባለው መሰረት ለተፈጠረው ችግር እልባት እየሰጠ ነው።

ታዲያ መንግስት ይህን የሚያደርገው ለህዝብ ካለው ከበሬታና ህዝባዊ ባህሪይ በመነጨ እንጂ የትኛውንም ወገን ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የዚህ ሀገር አጀንዳ መሪና ችግር ፈቺ መንግስት ስለሆነ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ የማናቸውም ችግሮች መፍትሔ መንግስት እንጂ ለኢትዮጵያ ጠላቶች የሚላላኩ ፅንፈኞች አለመሆናቸውን በመገንዘብ በአሁኑ ወቅት እያደረገ እንዳለው ሁሉ ወደፊትም ይህንኑ አቅጣጫ መከተል ይኖርበታል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy