Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህገ መንግስቱ “አንጓዎች”                                             

0 834

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህገ መንግስቱ “አንጓዎች”

                                                ደስታ ኃይሉ

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተመሰረተበትን የማዕዘን ድንጋዩች ወይም “አንጓዎች” የሰነዱ ወሳኝ ጉዳዩች ናቸው። በእነዚህ የማዕዘን ድንጋዩች በህዝቦች የጋራ መፈቃቀድ ላይ ተመስርተው የፀኑ ናቸው። “አንጓዎቹ” በአገራችን ሰላምን እያሰፈኑ ያሉ፣ ቀጣይነት ያለውን ልማት በማረጋገጥ ላይ የሚገኙና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን እያደረጉ ያሉ ናቸው።

የህገ መንግስቱ “አንጓዎች” ተብለው በመሰረታዊነት ከሚጠቀሱት ውስጥ፤ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች የተከበሩበት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ስርዓት፣ ራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የነፃ ገበያ መርህና በዚሁ ማዕቀፍ የመሬት አስተዳደር  በመንግስትና በህዝብ ስር እንዲሆን ማድረግ የሚሉት ዋነኛዎቹ ናቸው።

እነዚህን የህገ-መንግስቱን የማዕዘን ድንጋዩች መቃወም አሊያም ከህገ-መንግስቱ ውስጥ እንዲወጡ ማለም ማለት፤ እንደ አፄው ስርዓት ወቅት “ስዩመ-እግዚሐብሔር” እየተባለ መንግስትና ሃይማኖት አንድ እንዲሆኑ መመኘት፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን የሚጨፈልቁት ያለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ፀረዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ተመልሰው እንዲመጡ መሻት፣ የሌሎች ፍላጎቶችን ለማሟላት ሲባል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶችን እንዲታፈኑ መፍቀድ አሊያም ያለፈውን የሶሻሊስት ስርዓትን በመናፈቅ የነፃ ገበያ ስርዓት መርህ እንዳይኖር መፈለግ እንዲሁም የአርሶ አደሩን መሬት በመሸጥና በመለወጥ ጭሰኛ ሆኖ እንዲቀር መፈለግ ማለት ነው።

ሆኖም እነዚህን ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ፀረ-ልማታዊ አስተሳሰቦችን ጫንቃው ላይ ጭኖ ለመሸከም የሚፈቅድ ማህበረሰብ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር አይመስለኝም። ሊኖርም አይችልም።

የአገራችን ህዝቦች እነዚህን ፀረ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ልማታዊ እሳቤዎችን አምርሮ የሚጠላቸውና ከጫንቃው ላይም እንዲወገዱ በፅናት የታገላቸው ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ያለፉ ስርዓቶች ተግባራትን ማለም ህገ-መንግስቱን ዕውን ለማድረግ ውድ ህይወቱን ከከፈለው የሀገራችን ህዝብ ጋር አይንና ናጫ መሆን ይመስለኛል።

 

እነዚህን የህገ መንግስቱን “አንጓዎች” የትኛውም ወገን እንዳሻው ሊቀይራቸው አይችልም። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንድ ህገ-መንግስታዊ ሃሳብ እንዴት ተደርጎ እንደሚሻሻል በግልፅ የሚከተላቸው አሰራሮች አሉ።

ይሁን እንጂ የህገ መንግስቱን “አንጓዎች” ማሻሻል ማለት ህገ መንግስቱ የቆመበትን የማዕዘን ድንጋይ የሚቀይርና ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን መሰረት የሚያሳጣ በመሆኑ እነርሱን ማሻሻል ህገ-መንግስቱን ቀዳድዶ የመተው ያህል ይመስለኛል። እናም እነዚህን “አንጓዎች” ማሻሻል የሚቻል አይመስለኝም።

ስለ ህገ-መንግስቱ መሻሻል ጉዳይ ሲነሳ፤ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 104 እና 105 ላይ የተገለፁትን ፍሬ ነገሮችን መመልከት ይገባል። በህገ-መንግስት አንቀፅ 104 ላይ የሚገኘውና “የህገ-መንግስት ማሻሻያ ሃሳብን ስለማመንጨት” በሚለው ርዕስ ስር፤ የማሻሻያ ሃሳቡን የህዝብና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲደግፉት እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሶስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የደገፉት ከሆነ፤ የማሻሻያ ሃሳቡ ለመላው ህዝብና የህገ- መንግስቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች እንደሚቀርብ ይገልፃል።

ከዚህ ጎን ለጎንም “ህገ-መንግስቱን ስለማሻሻል” በሚያወሳው አንቀፅ 105 ስር፤ ህገ- መንግስቱን የማሻሻል ጉዳይ ንዑስ አንቀፅ አንድ እስከ ንዑስ አንቀፅ ሁለት ድረስ ባሉት የድንጋጌ ማዕቀፎች ውስጥ ብቻ እንደሚከናወን ተብራርቷል። በዚህ መሰረትም በአንቀፅ 105 (1) ላይ፤ በህገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች በሙሉ፣ ይህ አንቀፅና አንቀፅ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት፤ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት፣ የፌዴራሉ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የቀረበውን ማሻሻያ በሁለት ሶስተኛ ሲፀድቀውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲፀድቀው ብቻ እንደሚሆን ተደንግጓል።

በአንቀፅ ሁለት ላይም፤ ከላይ የጠቀስኩት የአንቀፁ ንዑስ አንቀፅ አንድ ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የህገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት፦ (ሀ) የህዝብ ተወካዩችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባቸው የቀረበውን ማሻሻያ በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ሲያጸድቁት እና (ለ) ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሶስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት ብቻ እንደሆነ በግልፅ ተደንግጓል። እነዚህ ህገ-መንግስቱን ስለማሻሻል የሚያወሱት አንቀፆች የህገ-መንግስቱ ዴሞክራሲያዊነት ትክክለኛ መገለጫዎች ይመስሉኛል።

ሁላችንም እንደምናውቀው እንደ ኢትዮጵያ ህዝቦች የፀረ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶችን አስከፊነት የሚያውቅ የለም—ከራሳቸው ተጨባጭ ልምድ በሚገባ ይገነዘቡታልና። እናም የህገ-መንግስቱ “ምሶሶዎች” በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ መኖርን በምንም መንገድ ሊፈቅዱት አይችሉም።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ባለፉት 23 ህገ መንግስታዊ ዓመታት የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን በሚገባ ማጣጣማቸው፣ የጀመሩት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያድግላቸውና እንዲመነደግላቸው ይሻሉ እንጂ፤ ዳግም ተመልሰው በኢ-ሰብዓዊና አምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ መዳከርን አይመኙም፤ ሊያስቡትም የሚፈልጉ አይመስለኝም። እናም በርካታ መስዕዋትነት የከፈሉበትንና የቃል ኪዳን ሰነዳቸው የሆነውን ህገ-መንግስት እንደ ዓይናቸው ብሌን ይንከባከቡታል።

ህገ መንግስቱ በራሳቸው የደም ጠብታ የፃፉት የጋራ ሰምምነት ሰነዳቸው በመሆኑም፤ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ባልተገባ ሁኔታ ሊቆርሱት እንዲመኙ ዕድል የሚሰጧቸው አይመስለኝም።

ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ላለፉት 23 ህገ-መንግስታዊ ዓመታት የተጎናፀፉትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳጧቸው መሆኑን ስለሚያውቁም፤ ለሰነቁት ራዕይና የህዳሴ ጉዞ ደንቃራ እንዲሆኑባቸው ይፈቅዳሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ ግን ህገ-መንግስቱን የሚቃወሙ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ማወቅ ያለባቸው ሃቅ ያለ ይመስለኛል፤ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነዳቸውን እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚጠብቁት እንጂ፤ “አንጓዎቹ” ተነቅለው የሌላ ሀገር ህገ-መንግስት እንዲሆን እንደ ባይተዋር በትዝብት የሚያዩት አይደለም፤ በደማቸው የዋጁትና የዘመናት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎቻቸውን መመለስ የቻለ ብቸኛ አገራዊ ሰነድ ስለሆነ ነው። እናም እነዚህን የህገ መንግስቱን “አንጓዎች” ማክበርና ማስከበር የሁሉም ዜጎች ግዴታ ነው። ምክንያቱም የህገ መንግስቱ መስራቾችና ባለቤቶች ዜጎች ስለሆኑ ነው። ስለሆነም የህገ መንገስቱን “አንጓዎች” በማክበርና ግንዛቤ ለሌላቸው ግለሰቦችም ተገቢውን ማብራሪያ መስጠትም ይገባል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy