Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህጋዊ ነጋዴዎችን ጥያቄ የመለሰው የግብር አሰራር

0 425

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህጋዊ ነጋዴዎችን ጥያቄ የመለሰው የግብር አሰራር

ዳዊት ምትኩ

አዲሱ የግብር አሰራር ከዚህ ቀደም በህገ ወጥ መንገድ ግብር ሳይከፍሉ ይነግዱ በነበሩ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ ግብር ከፋዩቹ ለመንግስት ሲያቀርቡ የነበሩትን ጥያቄ የመለሰ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም የታችኛው ነጋዴ ክፍል በግብር ስርዓቱ ውስጥ ሳይታቀፍ ህጋዊ ነጋዴዎችን የሚገዳደር ንግድ ያካሂድ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። በዚህ ሁኔታም ህጋዊ ነጋዴው ተጎጂ ሆኖ ቆይቷል። አሁን ግን ግብር የማይከፍሉ የነበሩት ነጋዴዎች ወደ ህጋዊው አሰራር ስለገቡ የህጋዊ ነጋዴዎችን ጥያቄ መመለስ ተችሏል።

ይህ የግብር አዋጅ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ነጋዴው ማህበረሰብ በተለይም ቀደም ሲል በግብር ማዕቀፉ ውስጥ ሳይታቀፉ የቀሩትን ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ አሰራር የመለሰ ነው። ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ያገኘሁት መረጃ እንደሚገልፀው፤ በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀፅ 3 መሰረት የግብር ከፋዮች ደረጃ ቀድሞ ከነበረው ተሻሽሏል።

በዚህ መሰረትም ደረጃ “ሀ” በመባል የሚታወቁት ግብር ከፋዮች  ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው አንድ ሚሊዮን እና ከዚያ በላይ ብር ከፋይ የሆኑትን የሚያጠቃልል ነው። ደረጃ “ለ” የሚባሉት ደግሞ ድርጅቶችን ሳይጨምር ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው ከአምስት መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ግብር ከፋይ ናቸው። እንዲሁም ደረጃ “ሐ” የተሰኙት ግብር ከፋዮች ደግሞ ድርጅቶችን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከብር አኝስት መቶ ሺህ በታች የሆኑ ግብር ከፋዮችን የሚያጠቃልል ነው።

ግብር ከፋዮች ላይ የሚታየውን የግብር አሰባሰብ ስርዓት ለውጥ ለማምጣት አንድ ግብር ከፋይ ዕቃ ሸጦ ወይም አገልግሎት ሰጥቶ ያገኘውን ዕለታዊ ገቢ መሰረት ያደረገ ግብር አሰባሰብ ተከትሎ ግብር መሰብሰብ መሰረት ያደረገ ነው፤ አዲሱ አሰራር። እርግጥ በየትኛውም አሰራር ውስጥ ሁሉንም ወገን እኩል ማርካት አይቻልም። ይሁንና የአብዛኛውን ነጋዴ ማርካት ይቻላል። በመሆኑም አዲሱ የግብር አሰራር አነስተኛ ነጋዴዎችን ወደ ግብር ከማስገባትና ህጋዊ ነጋዴዎች ሲያቀርቡ የነበሩትን ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የቻለና በዚያውም ልክ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ይደጉማል። በተለይም በ2009 ዓ.ም የሀገሪቱንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሰረት ያደረገ አዲሱ የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ያስቀመጣቸውንና በ2003 የቀን ገቢ ግምት መረጃ ጥናት ላይ የነበሩትን ክፍተቶች በማረም አማካይ የቀን ገቢ ግምቱ የታዩ ችግሮችን ለመሙላት ያስቻለ ነው ማለት ይቻላል።

በአዲሱ ገቢ ግብር አዋጅ መሰረት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በአማካይ የቀን ገቢ መረጃ መሰረት የሚስተናገዱ በመሆናቸው አማካኝይ የቀን ገቢ ግምቱ የግድ ይላል። እነዚህ ዐመታዊ የሽያጭ ገቢያቸው ከ500 ሺህ ብር በታች የሆኑ ግብር ከፋዩች በህጉ መሰረት ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ የለባቸውም። የሚጠበቅባቸውን ግብር እና ታክስ በቁርጥ እንዲከፍሉ ስለሚያደረግ ይህን አሰራር ያስቀረ ነው። ይህም ለግብር ከፋዩም ይሁን ገቢውን ለሚሰበስበው አካል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ታዲያ ከዚህ ቀደም የቀን ገቢ ግምት የነበራቸውና ጥናቱ የተሰራላቸው ግብር ከፋዮች ለንግድ ትርፍ ግብር ብቻ የ2009 በጀት ዓመት ግብር እንዲከፍሉ ተደርጓል። ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስን በተመለከተም ዓመቱን ሙሉ በቀድሞ የቀን ገቢ ግምት መሰረት እንዲከፍሉ የሚደረግ ሲሆን፤ አሰራሩ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የቀን ገቢ ግምት ቀጥታ ላልሆኑ ታክሶች ተግባራዊ ሆኗል።

ሆኖም ከዚህ ቀደም ግምት ያልነበራቸውና በታሳቢም ያልከፈሉ ግብር ከፋዮች ሆነው አሁንም መረጃ ያልተሰበሰበላቸውን በተመለከተ ከተቻለ ለማሳወቅ ሲመጡ ግምት እንዲቀርብ በማድረግ ይህ ካልሆነ በግብር ማስታወቂያ ወቅት እንዲቀርብ በማድረግ ለንግድ ትርፍ ብቻ የ2009 በጀት ዓመትን እንዲከፍሉ በመደረግ ላይ ይገኛል። ይህ አዲስ አሰራር ዓመታዊ ግብርን ለማወቅ የሚያስችል ነው። ታዲያ የቀን ግብር አወሳሰንና ዓመታዊ ግብርን መገንዘብ ይገባል።

በተለይም አብዛኛው ግብር ከፋይ በቀብ ገቢ ግብር ትመና እና በዓመታዊ ግበር መካከል ያለውን ልዩነት አልተገነዘቡም። ግብር ከፋዩቹ የቀን ገቢ ግምቱንና ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑን በማየት ብቻ ያን ያህል ግብር ክፈሉ እንደተባሉ ቆጥረው የመደናገጥና የማማረር ሁኔታዎች ተስተውለዋል። እንዲያውም ይህ ጉዳይ የፅንፈኞች አጀንዳ ሆኖ ግብር ከፋዩን ማህበረሰብ ለማደናገር እየተጠቀሙበት ነው። እናም አሁንም የገቢዎችናጉሙሩክ ባለስልጣን ያገኘሁትን ምሳሌ መሰረት በማድረግ ጉዳዩን ለማስረዳት እሞክራለሁ።

ለምሳሌ ያህል አንድ የባህል ዕቃ ነጋዴ አለ እንበል። ነጋዴው የቀን ገቢ ግምቱ ሁለት ሺህ ብር ተገምቶበታል። ይህ ሁለት ሺህ ብር ግመታ በዓመቱ አጠቃላይ ቀናት በ365 ቀን እንዲባዛ አይደረግም። ይልቁንም የሚባዛው በ300 ቀናት ብቻ ይሆናል። 65 ቀናቱን ነጋዴው ቢሰራባቸውም መንግስት አይቆጥራቸውም።

እናም ሁለት ሺው በ300 ብር ይባዛል። ይኸውም አጠቃላይ ዓመታዊ ሽያጩ 600 ሺህ ብር ይሆናል። የንግዱ ዘርፍ የትርፍ መተመኛ 14 በመቶ ነው። ጠቅላላ ዓመታዊ ሽያጩ በዘርፉ ትርፍ መተመኛ ሲባዛ 84 ሺህ ብር ይመጣል። ግብር የሚከፈልበት ገቢም ይኸው 84 ሺህ ብር ብቻ ይሆናል። የግብር ምጣኔው 25 በመቶ ሲሆን፤ 84 ሺህ ብሩ በ25 በመቶ ተባዝቶ 21 ሺህ ብር ይመጣል። ከዚህ ውስጥ ተቀናሽ ስድስት ሺህ 780 ነው። በመሆኑም ዓመታዊ ግብሩ 14 ሺህ  220 ብር ብቻ ይሆናል።

እንግዲህ ከዚህ አጠቃላይ ስሌት በመነሳት የቀን ገቢ ግብር ማለት የነጋዴው ወጪ ያልተቀነሰለት አጠቃላይ የቀን ሽያጥ ግምት እንጂ በዓመቱ ቀናት ተባዝቶ ነጋዴው የሚከፍለው አይደለም። በዚህ ረገድ የተያዙ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች መታረም ይኖርባቸዋል።

ዜጎች ግብር የሚከፍሉትን መልሰው የሚጠቀሙበት ራሳቸው ናቸው። ለተለያዩ መሰረተ ልማት አገልግሎት ለመሰረታዊ አገራዊ ጥቅም የሚውል ነው። ማንኛውም ዜጋ ግብር በመክፈሉ ኩራት ሊሰማው ይገባል። ‘እኔ የአገሬ ግበር ከፋይ ነኝ’ የሚል ኩራትና የመረጠው መንግስት እርሱ በከፈለው ግብር መልሶ እርሱን የሚያገለግል መሆኑን ማመን ይኖርበታል።

በተለይም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ መንግስት ዘርፈ ብዙ ትልሞችን በመያዙ የፋይናንስ አጠቃቀሙ ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ የተሟላ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን፣ ብክነትን ለማስወገድና በጀቱን በቁጠባ ለመጠቀም ልዩ ትኩረት መስጠቱን እቅዱ ይገልፃል።

ሁሌም እንደሚያደርገው ከህዝቡ በታክስ መልክ የሚሰበሰበው ግብር እንዳይባክንና ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በጥብቅ ቁጥጥር ይሰራል። ለዚህም ነው በቅርቡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ለ2010 የበጀት ዓመት የተመደበው በጀት በጥብቅ ቁጥጥር ስር የሚያልፍ እንደሚሆን የገለፀው። ይህ እንዲሆንም ሁሉም ዜጋ በበጀት ቁጥሩ ላይ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ የመንግስትን ጥረት መደገፍ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy