ethiopian news

Artcles

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር

By Admin

August 28, 2017

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር

የመልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ምንነት በጣም አከራካሪና ሰፋ ያለ ሙግት የሚካሄድበት መስክ እንደሆነ ይታወቃል፡ በዚህም የተለያዩ የዘርፉ ሙሁራን የተለዪ ሃሳቦች ይሰጣሉ፡፡እንደ ናንዳ (Nanda, 2006: 271) ገለፃ አስተዳደር የሚለው ሃሳብ የትርጉም እልባት ያላገኘ እና ትርጉሙም ልናሳካ በምንፈልገው ዓላማ እና በምንከተለው ዘይቤ እንደሚመሰረት ታብራራለች።

አስተዳደር የነባራዊው ፖለቲካዊ ስርዓት ነፀብራቅ ሲሆን በመጠነ ስፋቱ እና ተዛማጅ ትርጉሙም ከግዜ ወደ ጊዜ እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ ነው። በየትኛውም የዓለም መሪዎችና ሃገራት የመንግስታት አስተዳደር ሊያሳካ የሚችለው ትልቁ ዓላማ የአስተዳደር ገፅታ መገንባት፡ ቢሮክራሲውን በመቀነስ ዲሞክራሲን ማጎልበት ብቁነት፡ ዉጤታማነት እና  ቅልጥፍና ማሻሻል ነው።

በሌላ በኩል ማህበረ – ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገቶችን እና የዴሞክራሲ ጅማሬን ተከትሎ  አስተዳደር የሚለው ሃሳብ መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራስያዊ አስተዳደር የሚሉትን በማካተት መልካም አተደዳደርን የዴሞክራሲ ፀጋ አድርጎ መቁጠር የተዘወተረ ነገር መሆን መጀመሩ መገንዘብ ይቻላል። መልካም አስተዳደር ወይም ዴሞክራስያዊ አስተዳደር ከዉጤታማነት እና ብቁነት የሰፋ እና የገዘፈ ሃሳብ ሲሆን፤ ላጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱ የሚቆምና የዜጎችን ፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ መብቶች እና ነፃነቶች የሚያስከብርና ማንኛዉንም ዓይነት አድልዎ የማይቀበል ሂደት ነው። ግልፅነት እና ተጠያቂነትም በሲቪል ሰርቪሱ ብቻ የማይታጠር በፖለቲካ አመራሩ እና ተቋማት ሊተገበር እሚገባው ቁልፍ የመልካም አስተዳደር አካሎች ናቸው። መተግበር ያለበት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግምባታም ሆነ የመልካም አስተዳደር መወጣጫ መሰላል ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለይም በተባበሩት መንግስታት የኤስያና ፓስፊክ ኮምሽን ትንታኔ ብንወስድ መልካም አስተዳደር በርካታ ባህሪያት አሉት ይላል። ከነዚህም አሳታፊነት፣ መግባባት ላይ ያተኮረ (Consensus oriented)፣ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ መልስ ሰጪ መሆን (Responsive)፣ ዉጤታማ እና ብቁ (ቅልጥፍና)፣ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቃፊ (equitable and inclusive) እንዲሁም የህግ የበላይነት ናቸው። መልካም አስተዳደር የአናሳ የህብረተሰብ ክፍል (Minorities) እና የሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳብ እና ድምፅ በዉሳኔ መስጠት ሂደት ላይ ግምት ዉስጥ መክተትንም ይጨምራል። አሁን ላለው እና ወደፊት ለሚመጣው ማህበረሰባዊ ፍላጎትም ጭምር ዝግጁ የሆነና መልስ መስጠት የሚችል ዓቅም እና መዋቅር መፍጠር ነው ። አንድን ሰርዓት መልካም ነው ወይም መጥፎ አስተዳደር ነው የሚለዉን ለመገንዘብ ከነዚህ መለኪያዎች አንፃር ሊታይ ይችላል ።

በህዝብ አስተዳደርና በፖለቲካል ሳይንስ ሙሁር የሆኑ ናይጄሪያዊ ገብረቭቢ (Gberevibe) ‘Democracy, Democratic Institutions and Good Governance in Nigeria’ በተሰኘው ፁሁፋቸው አልካሊ የተባለ የዘርፉ ምሁር ጠቅሶ እንደሚለው አስተዳደር ማለት የፖለቲካ ስልጣንን ህዝባዊ ጉዳዮችን ለማስኬድ ማዋል እንደሆነ ያትታል፡፡ አስተዳደር የሚዳስሳቸው ጉዳዮች የህግ የበላይነትን፣ ተጠያቂነትና ግልፅነትን፣ ልማት ተኮር አመራርን፣ ራስን የመግለፅና የመደራጀት መብትን፣ መልስ ሰጪነትን፣ ሃላፊነት መዉሰድን፣ ወካይነትን፣ ዉጤታማነት እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠትን እንደሚያካትት ይገልፃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው መልካም አስተዳደር የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በተጨማሪም ሻቢር ቼማ እንደሚለው “መልካም አስተዳደር ያለዉን ሃብት ለጋራ ችግሮች እንዴት መዋል እንዳለባቸውና በምን አኳሃን መመራት እንዳለባቸው የሚመለከት እንደሆነ ይጠቅሳል። መገለጫ መርሆቹም አሳታፊነት፣ ግልፅነት፣ ተጠየቂነት፣ የህግ የበላይነት፣ ዉጤታማነት፣ ፍትሃዊነት እና ስትራቴጅያዊ ራዕይ መጨበጥን ያካትታል ይላል፡፡

ፅንሰ ሃሳቦቹ ከሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አንፃር ሲቃኙ ከላይ የተባሉትን መልካም አስተዳደር ማረጋገጥ አለመቻል፣ ሙስና፣ እና የፍትህ መጓደል ሶስት አደገኛ የስርዓቱ በሽታዎች ናቸው፡፡ የዲሞክራሲ ባህል ሲቀጭጭ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ማክበር ያለመቻል ከቁጥጥር ውጪ የመሆን ዕድላቸው ይሰፋና ማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች ይሆናል፡፡ እነዚህ ከላይ የገለፅኳቸው ሶስት አደገኛ በሽታዎች ለዘመናት ከኛ ጋር የኖሩ እና አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑን የሚገኙ ስለሆኑ ኢኮኖሚያዊ ከሆኑ መንገዶች በተጨማሪ ሌላ መፍትሄ ማበጀት ካልተቻለ በቀጣይነት ግዝፈታቸው እየጨመረ መሄዱ እማይቀር መሆኑ መገንዘብ ግድ ይላል::

የዲሞክራሲ ግንባታ እና እነዚህ በሽታዎች በሁለት ተቃራኒ መንገድ የሚጓዙ ተፃራሪ ክስተቶች ናቸው፡፡ ባልተቋረጠ የመረጃ ፍሰት ወይም ግልፅነትና አሳታፊነት ዲሞክራሲያዊ ሁኔታው ሲሰፋ በሽታዎቹ መጠጊያ እና መሸሸጊያ ፍለጋ ይኳትናሉ፡፡ ምሽግ ፈልገው ወይም ቆፍረው ይደበቃሉ፤ ልክ የወባ በሽታ ከህክምና በኋላም ቢሆን በሆነ የሰውነታችን ክፍል እንደምትደበቀው፤ ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ ሲጠብ ደግሞ በሽታዎቹ ወደ አደባባይ እየወጡ ህጋዊ ልባስ እየተጎናፀፉ መገናኛ ብዙሃንን ጭምር እየተጠቀሙ ይፈነጫሉ፤ ህዝብንና አገሪትዋንም በኋሊት ማርሽ ወደ አዘቀት ይከቷታል፡፡  

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝቦች መብታቸውን ለዘመናት ተረግጠው የኖሩባት፣ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያልታየባት፣ ልማትና ዕድገት ሊረጋገጥ ያልታሰበባት ሀገር፤ ዛሬ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዘርግታ፤ ሰላሟና ልማቷ ተረጋግጦ ማየት መቻላችን ማንኛውንም ዜጋ እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም። ይህም ሊሆን የቻለው የተሸለ ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር መዘርጋት በመቻሉ ነው፡፡

በሌላ በኩል የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው ምርጫ ነው። የምርጫ ጠቀሜታም ህዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ፣ በተጨባጭ በምረጡኝ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ፖርቲዎች ያከናወኑትን ወይም የሚያከናውኑትን ተግባር በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለህዝባቸው ግልፅ ያደርጋሉ፤ አዲስ ፖሊሲ እና ስትራተጂም ይቀይሳሉ ዜጎችም የእገሌ ፖርቲ በቀጣይ ለውጥ ያመጣልናል ብለው ያመኑበት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያላንዳች ተፅዕኖ ካርዳቸውን በመስጠት ተመራጩን ፓርቲ ለስልጣን ማብቃት የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን አውቀው ድምፃቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይህም ህገ መንግስቱ በግልፅ ያጎናፀፋቸውን የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት በመጠቀም ባለቤትነታቸውን ያረጋግጣሉ።

በዚህም ሃገራችን እየተገበረችው ያለው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ባለፋት ጊዜያት የተከናወኑ አምስት ሀገራዊና በርካታ ክልላዊ እንዲሁም የአካባቢና የአዲስ አበባ የምክር ቤቶች የሟሟያ ምርጫዎች የላቀ ሚና ተጫውተዋል። በእነዚህ የምርጫ ሂደቶች የሕዝቡ የነቃ ተሳትፎና ዴሞክራሲውን ወደፊት ለማራመድ የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አይዘነጋም። የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ረገድም የተካሄዱት ምርጫዎች የላቀ ሚና ነበራቸው።

የፖለቲካ ፖርቲዎችም ቢሆኑ በቁጥር ይሁን በአስተሳሰብ ደረጃ የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ግን እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ገና ለጋ መሆኑን ነው። ያም ሆኖ ምንም እንኳን የተሟላ ባይሆንም፤ ገዥውም ፓርቲ ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድ የተቻላቸውን ያህል ጥረት አድርገዋል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባለፋት ዓመታት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በሂደት እየገነባች መጥታለች፡፡ ህዝቧም መንግስት የቀረፀውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ተከትሎ ድህነትን ለማሸነፍ ባደረገችው ርብርብ አንፀባራቂ ሊባል የሚችል ውጤት ማግኘት ጀምሯል።

ሆኖም ሁሌም ልዩነታችን አንድነታችን ሆኖ ሳይቀጥል ቀርቶ በመነቋቆር እንዲሁም የሌሎች አጀንዳ አስፈፃሚዎች ከሆንን እንደ ከዚህ ቀደሙ ለዘመናት ስንዳክርበት ወደነበረው የድህነት አረንቋ መመለሳችን የማይቀር ሐቅ ነው። ይህ እንዳይሆን ሁሉም ፓርቲዎች ከጭፍን ጥላቻ ፖለቲካ ወጥተው ዴሞክራሲ፣ ልማትና ሰላም ለኢትዮጵያ ወሳኝ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለአተገባበሩ መትጋት ይኖርባቸዋል።

ይህን የተገነዘቡት ገዥውና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያደርጋቸው አበረታች ውይይቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ የተያዘው ቁርጠኝነት በሚፈለገው ፍጥነት መጎልበት አለበት። ዴሞክራሲውን ለማስፋት በመንግስት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት ተጨባጭ መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይህን ተግባር በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ወዳልተፈለገ እሰጥ አገባ ውስጥ ሳይገቡ ለጋራ ዓላማና አጀንዳ መሰለፍ  ይኖርባቸዋል።

በመሆኑም አሁን እየታየ እንዳለው መልካም ጅምር ሁሉም በፓርቲዎቹ የሚያካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች መነሻቸውና መድረሻቸው ሃገራዊ ጥቅምን በጋራ ከማስጠበቅ አንፃር በግልፅ ተለይተው የጋራ ድምዳሜ ሊያዝባቸው ይገባል።

ይህም በማድረግ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርባቸዋል። አንዳንዴ አንዳንድ ያልተገባ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብቻ ሲባል የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመፍጠርና በማራመድ ህዝቡ ውስጥ የማይገባ ምስል ከማስያዝ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ከዚህ አኳያ ወጣ ገባ የሚሉትን ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት ተገቢ ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀቱን ለመጨመር በተያዘው ቁርጠኝነት ላይ አንድ እርምጃ መሄድ ጭምርም ይሆናል።

ከዚህም በተጨማሪ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር፤ ፓርቲዎቹ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው ጋር ተያይዞ መንግስት ያለበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ህፀፆቹን በግልፅ እንዲያይ ያደርጉታል። መንግስትም አግባብና ትክክለኛነት ያላቸውን አስተያየቶች በመቀበል ለስራው እንደ አንድ ድጋፍ እንዲጠቀምባቸው የመነሻ ሃሳቦች ሊሆኑት ይችላሉ። ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ለተሸለ ስራ መትጋት አለበት፡፡

ይህ ሁኔታም በአንድ በኩል ዴሞክራሲውን ለማስፋትና የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰሚነት ድምፅ እንዲጨምር ዕድል ይሰጣል። በፓርላማ ደረጃ የሚኖረው የአሳታፊነት ዴሞክራሲም መንፈስና ተግባርም ይጎለብታል። መድብለ ፓርቲ ስርዓቱም የበለጠ እያበበና እያደገ ይመጣል። የመንግስት እና የሃገሪቱን ህዝብም ቀረቤታ ይጨምራል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመልካም አስተዳድር ችግሮችን የሚፈታ አመራርና የህዝብን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማስረፅ መነሻም ይሆናል፡፡ ሰላም!