Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሙስና መሠረታዊያን መገለጫዎች

0 731

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሙስና መሠረታዊያን መገለጫዎች

አባ መላኩ

 

የኪራይ ሰብሳቢነት ወንጀል ከፍተኛ የፍትህ መጓደልን ያስከትላል። በዚህ የወንጀል ተግባር ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ደላላዎች  በህገ ወጥ መንገድ ከጉቦ ሰጪዎች ቋሚ የሆነ ኮሚሽን ወይም ክፍያ በመቀበል ህጋዊ አሠራርን የሚጥሱበት መንገድ ነው፡፡ ይህ በአገሪቱ ፍትሃዊ የሆነ ነጻ የገበያ ውድድር እንዳይኖር በማድረግ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶችን በማቀጨጭ በአገሪቱ የዕድገት ጎዳና ላይ ይህ ነው የማይባል ጫናን ያሳድራል።


የሙስና መሠረታዊያን  መገለጫዎች ከሚባሉት  አንደኛው በየደረጃው ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ሊያገለግሉት ኃላፊነት ከተሰጣቸው ህዝብ ጉዳይ ለማስፈፀም የሚቀበሉት ጉቦ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሙስና በአንድ አገር የፍትህ መጓደል ላይ ያለውን አደጋ ያሳያል። ሁሉም ዜጋ ነጻ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ሲገባው ያለአግባብ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረግበት ሁኔታን ይፈጥራል።

ሁለተኛው አስከፊ ገጽታ ደግሞ በኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች የሚፈፀም ነው። እነዚህ ባለሃብቶች በህገ ወጥ  መንገድ ከሃብት ላይ ሃብትን ለማካበት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው።  እነዚህ ወገኖች ለሚያደርጉት መጠነ ሰፊ ህግን ያልተከተለ የገንዘብ እንቅስቃሴ ህጋዊ  ከለላን ለማግኘት ከመንግሥት አካላት ጋር የሚዋዋሉት ጉዳይ ነው።  ይኼኛው የኪራይ ሰብሳቢነት ገጽታ ወይም  የሙስና መረብ የህዝብ ኃላፊነት የያዙ ግለሰቦችን በገንዘብ ኃይል በማማለል በአገሪቱ ህገ ወጥ እንቅስቃሴን በማስፋፋት ከሀብት ላይ ሀብትን የማደለብ ተግባር  ነው፡፡

 

ሦስተኛው የሙስና ገጽታ ደግሞ  በተቋም መልክ የሚካሄድና ህጋዊ ከለላ ያለው የምዝበራ ዓይነት ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሙስና ተሳታፊ የሆኑ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች  የአገር ንብረት የሚዘርፉበት ሆኖም ህጋዊ የሚመስል ሰነድ እየተዘጋጀ የሚወራረድበት መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የሙስና ተግባር በርካታ ሰዎችን በዝርፊያው ውስጥ የማስገባት ባህሪ ስላለው አንዳቸው ሌላኛውን ከለላ በመሆን የሚጠቃቀሙበት መንገድ ነው፡፡


ኅብረተሰቡ በንቃት ሊከታተለው የሚገባው ሌላው የሙስና ገጽታ ደግሞ በንግድ ሥራ ተሰማርተው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ የንግድ ድርጅቶች የመንግሥትን ግብር በተገቢው መንገድ ባለመክፈል የሚፈፀም ተግባር ነው። 

 

እነዚህን የንግድ ድርጅቶች ልዩ የሚያደርጋቸው በአገሪቱ በተፈጠረው መልካም የነጻ ገበያ ገብተው በከፍተኛ ደረጃ አትራፊና ተጠቃሚ እየሆኑ ለህዝብ መሠረተ ልማት ግንባታ የሚውለውን የመንግሥት ድርሻ ከሙሰኛ ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር የሚሰሩት የማጭበርበር ተግባር ነው። ህገ ወጥ  ነጋዴዎቹ ልማታዊ ባለሃብቶችን  ከገበያ የማፈናቀል ተግባራትንም ይፈጽማሉ፡፡

 

ከጥቅመኛ ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር ወደ ገበያ መግቢያና ንግድ ማስፋፊያ ካፒታል ተገቢነት በሌለው መንገድ ማግኘት፣ የውጭ ምንዛሪን በሚፈልጉት መጠን ለማግኘት የሚያስችላቸውን የግንኙነት መረብ በመዘርጋት ተፎካካሪዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ መንቀሳቀስም ሌላው የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ነው።


በርካታ ልማታዊ ባለሃብቶች ለውጭ ምንዛሪ እጦት ሲዳረጉ ኪራይ ሰብሳቢዎች በዘረጉት መረብ መሰሠረት ተጠቃሚ ይሆናሉ። በአገሪቱ ፍትሃዊ አስተዳደር እንዳይነግስ ከፍተኛ መሰናክል ሆነው የአገሪቱን ዕድገት በተፈለገው መልክ እንዳይሄድ ወደ ኋላ የሚጎትት ተግባር ይፈጽማሉ። እንዲሁም ባላቸው ሰፊ ዕድል በመጠቀም ለሥራው ብቃት ሳይኖራቸው ገበያውን ለመቆጣጠር ይሰራሉ። 

 

ልማታዊ ባለሃብት የበላይነቱን እየያዘ ካልሄደ አገሪቱ እያሰበች ያለው ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገትም ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው። ልማትና የኢ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ደግሞ ለዚህች አገርና ህዝብ የህልውና ጉዳይ ነው። ፈጣን ልማት ካልተረጋገጠና ፍትህና ዴሞክራሲ በተገቢው ደረጃ ካልሰፈነ የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከማንም የተሰወረ አይደለም። ለዚህም ነው  መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት የአገሪቱ ከፍተኛ አደጋዎች በመሆናቸው መገታት እንዳለባቸው በተለያየ መልክ ጥረት እያደረገ የሚገኘው።


መንግሥት እየወሰዳቸው ካሉ ዐበይት ርምጃዎች መካከል አንዱ ልማታዊ ባለሃብቶችን መደገፍ ነው። በነፃ ገበያ ደንብ መሠረት ለመሽቀዳደም በማለም ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ የሚያፈሱትን ኢንቨስተሮች በኪራይ ሰብሳቢ ኢንቨስተሮች ድርጊት ተስፋ እንዳይቆርጡና  ከውድድሩ ውጭ እንዳይሆኑ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የንግድ ተሰጥኦ ያላቸውን ሥራ ፈጣሪዎችን አዲስ ክህሎትን እንዲያዳብሩ የሚያደርግ፣ የነፃ ፉክክርን መንፈስ የሚያጠናክር፣ በአዲስ ግኝት ላይ የተመሠረተን የንግድ እሴት የሚጨምር፣ ጥሮ ተጣጥሮ የሚመጣ የንግድ ትርፋማነት እንዲዳብር የማድረግ አቅጣጫን ይከተላል፡፡


ከዚያ ጎን ለጎን   የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትና ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚፀየፍ ትውልድ ለማፍራት በትምህርት ተቋማትና በመገናኛ ብዙሃን በኩል በርካታ አስተምህሮዎችን እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ይገኛል። ማንኛውም ዜጋ በአገሩ ያለምንም አድልዎ በነጻነት ሰርቶ ሃብት የሚያገኝበት አሠራርም ተዘርግቷል።  ጥሮ ግሮ ሃብትን ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ከባለሥልጣናት ጋር ተሞዳምዶ በማጭበርበር ለመጠቀም በሚሞክር ማንኛውም ወገን ላይ ደግሞ ተገቢውን ክትትልና ምርመራ በማድረግ ለህግ የማቅረቡን ተግባር ከኅብረተሰቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል።


መንግሥት ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነት የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብም ለሚያደርገው  ትግል የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። በቅርቡ መንግሥት በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቢዝነስ ሰዎች እና ደላላዎች ላይ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉ  ለዚህ በጎ ማሣያ ነው።  

 

ርምጃውን ተከትሎ እየመጣ ያለው መነቃቃት የሚያሳየው ሁኔታ የመንግሥት አቋም እንዳለ ሆኖ በሕዝቡ በኩልም ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ቁርጠኝነት መኖሩን ነው። አሁን የሚያስፈልገው ነገር በሁለቱ መካከል ያለውን ቁርኝት ማጥበቅና ማጠናከር ብቻ  ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy