Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሠላምና መረጋጋት ባለቤቱ ህዝቡ ነው!

0 280

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሠላምና መረጋጋት ባለቤቱ ህዝቡ ነው!

                                                        ታዬ ከበደ

በአገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው የሰላምና መረጋጋት ስራ ዋነኛው ባለቤት ህዝቡ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ሁነኛ አስረጅ ነው። ህዝብ በአገራችን ውስጥ ለሚካሄደው የሰላም ስራ ወሳኝ ከመሆኑም በላይ የአካባቢውን ደህንነት በራሱ ፍላጎት በመጠበቁ ለ10 ዓመታት በአገራችን ገቢራዊ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሳ ምክንያት ሆኗል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በውጭ ሃይሎችና በሀገራችን የውስጥ ተላላኪዎቻቸው ቅንጅታዊ እኩይ ሴራ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። ሁከቱን በቁጥጥር ስር ማዋል እንዲቻልም በህገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል። ይህ አዋጅም በወቅቱ ሰላሙን ተነጥቆ በነበረው የየአካባቢዎቹ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት ድጋፍ ያለው ስለነበረ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ተችሏል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። የሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖችም የተሃድሶ ትምህርት ወስደው በሁለት ዙሮች ተመርቀዋል። በሁከቱ ወቅት የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ቃል በመግባትም ወደየመጡበት አካባቢዎች ተመልሰዋል።

በቅድሚያ እነዚህን አጥፊ ዜጎች በመጠቆምና ለእርምት ወደ ተሃድሶ ማዕከሎች እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የህዝቡ የማይተካ ሚና እዚህ ላይ ሊደነቅ የሚገባው ይመስለኛል። ይህም ማንኛውም አዋጅ ያለ ህዝቡ የእኔነት መንፈስ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው።

ለአዋጁ መነሳት ግንባር ቀደም ተዋናይ ህዝቡ መሆኑ አይካድም። የየትኛውም ሀገር ህዝብ በማንኛውም መስፈርት ሰላሙን ተፃርሮ ሊቆም አይችልም። በመሆኑም ለሰላሙ እውን መሆን አጥፊዎችን በማጋለጥና በመገምገም የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በቡድን ተደራጅተው ሰላምና መረጋጋቱን ሊያሳጡት የሞከሩ አጥፊዎችም ወደ ህግ ፊት እንዲርቡ አድርጓል። በተለያዩ ምክንያት በአጥፊነት የተወሰዱ ግለሰቦች የተሃድሶ ትምህርት ወስደው ሲመለሱም ዕውቀት ገብይተው መመለሳቸውን ስለሚገነዘብም ድጋፍና ክትትል አድርጓል። ይህም ህዝቡ ሰላሙን በራሱ ፍላጎት እንዴት ያስጠብቅ እንደነበር አስረጅ ነው።

እርግጥም በየትኛውም አገር ውስጥ ስለ ሰላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች የህዝቡ ተሳትፎ ፋና ወጊ ነው። የሀገራችንንና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት የማይሹ የውጭ ሃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው የፈፀሙት ፀረ-ሰላም ድርጊት የት ድረስ እንደ ዘለቀ ከህዝቡ የተሰወረ እውነታ አይደለም። ይህን በመገንዘቡም አካባቢውን ባለፉት 10 ወራት በንቃት በመጠበቅ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በየአካባቢው ላለው ሰላምና መረጋጋት ዋነኛ መሰረት ሆኖ ሰርቷል። በአካባቢው የሚከሰት ማናቸው የፀረ-ሰላም ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን በመሆኑ ለሰላሙ ይበልጥ ተግቶ ተንቀሳቅሷል፤ ባለፉት 10 ወራት።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ህዝቡ የተለያዩ ክልከላዎች ደረጃ በደረጃ ለመነሳታቸውም የህዝቡ ሚና ከፍተኛ ነበር። ህዝቡ ከምንግዜውም በላይ የየአካባቢውን ሰላም በመጠበቁ በአዋጁ ላይ የነበሩት ዋና ዋና ጉዳዩች በወቅቱ እንዲነሱ በማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

ለምሳሌ ያህልም በትላልቅ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች አካባቢ በምሽት ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተጥሎ የነበረው ገደብ መነሳቱ፤ በልማት አውታሮቹ ላይ ጨለማን ተገን በማድረግ ሊፈፀሙ የሚችሉ ጥቃቶች እንደ ስጋት እንዳይቆጠሩ በማድረግ የጎላ ሚና ነበረው። ይህም የሰላምና መረጋጋታችን ባለቤት ህዝቡ መሆኑን የሚያስረዳ ይመስለኛል።

እርግጥ ህዝቡ ለሰላሙ ቁርጠኛ የሆነው ከሁለት ጉዳዩች ተነስቶ ይመስለኛል። አንድም ህዝቡ የተከሰተው ችግር የተገኘውን ሰላም የኋሊት የሚቀለብስ መሆኑን መረዳቱን፣ ሁለትም የሁከት ኃይሎች የግጭት አጀንዳ በሂደት ቦታ የሚያጣ ስለሆነ ነው።

ከገዥው ፓርቲና ከመንግስት ጋር ውይይት እያደረገ ያለው ህዝብ ችግሮችን መጠለያ በማድረግ እንዲሁም የተከሰተውን ቅሬታና አለመግባባት እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጥረው ህገ-መንግስቱንና ስርዓቱን ለማፍረስ የተነሱ የሁከት ኃይሎች መኖራቸውን ስለተገነዘበ ለሰላሙ ቀናዒ መሆን ችሏል። የሰላሙ ዋስና ጠበቃ ሆኗል። ህዝቡ ራሱ በትግሉ የፈጠረውን ሰላም ራሱ ጠብቋል። በየማህበራዊ ሚዲያውና በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች እየተከናወኑ ያሉትን የዘረኝነትና ጥላሸት የሚቀባ አሉባልታዎችን መክቷል።

እዚህ ሀገር ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ልማታዊ ተግባራት እንዲሁም የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን እየተረጋገጠ የሚገኘውን ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል የሚያውቀው ራሱ እንደ መሆኑ መጠን፤ ዘረኝነትንና ከእርሱ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ማናቸውም ጉዳዩች በቂ ምላሽ በመስጠት የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች የሚያናፍሱትን የአሉባልታ አጀንዳ ወደ ጎን በማለት ሰላሙን ለማስጠበቅ የቆረጠው ለዚሁ ይመስለኛል። እናም ይህ ህዝብ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የ10 ወራት ቆይታ ላደረገው አስተዋጽኦ ሊመሰገን ይገባል።

በእኔ እምነት ህዝቡ ለሰላሙ ቀናዒ የሆነውን ያህል በአገራችን ለተጀመረው የመልካም አስተዳደር ስራዎችም የበኩሉን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የህዝቡ በመልካም አስተዳደር ላይ ተሳተፎ ማድረግ ለውጤታማነቱ ወሳኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም። እናም ለአገራችን ሰላም መገኘት ቀናዒና ለተጠቃሚነቱ ታታሪ የሆነን ህዝብ ይዞ ከግብ የማይደርስ ልማት አይኖርም።

ይህን ለአገሩ ሰላም የሚተጋን ህዝብ ይዞ የውጭ ኃይሎችን ሴራና የተላላኪዎቻቸውን መልዕክት ሀገር ውስጥ ሳይገባ መንገድ ላይ ማስቀረት የማይቻልበት ምክንያት የለም። የሀገራችንን ሁለንተናዊ ችግሮች ከህዝቡ ጋር በመሆን እየተስተካከሉ ነው። እናም ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ይበልጥ ቢሳተፍ እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

ህዝቡ ባለፉት 10 ወራት ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለች ሳትመስል ማናቸውም ተግባሮች እንዲከናወኑ ማድረግ ችሏል። ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ሌሎች አገራዊ ልማቶች ብዙም ሳንካ ሳይገጥማቸው እንዲከናወኑ ጥረት አድርጓል። ተሳክቶለታልም። ሰሞኑን ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ውስጥ ለሆኑ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች በተደረገው ገለፃ ላይ ዲፕሎማቶቹ በስራቸው ላይ ምንም ዓይነት እንቅፋት አለመፈጠሩን መግለፃቸው ይህን ሃቅ የሚገልፅ ነው።

በአጠቃላይ ህዝቡ ለአገሩ ሰላምና መረጋጋት ያደረጋቸው ተሳትፎዎች ከፍተኛ ናቸው። እነዚህን ተሳትፎዎቹን ማጎልበትና ለልማታችን ይበልጥ ጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መቀየስ ይገባል። ይህን ማድረግ ከተቻለ፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር ማሳካት የምትፈልገውን ራዕይ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy