Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሱዳን እና የኢትዮጵያ ግንኙነት

0 884

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሱዳን እና የኢትዮጵያ ግንኙነት

ዮናስ

 

በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተመራ የልኡካን ቡድን ከሰሞኑ በሱዳን የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጉ ይታወቃል። በዚያውም ወደሩዋንዳ ጎራ ማለታቸውም በተመሳሳይ ይታወቃል። ልኡኩ በርካታ አጀንዳዎች ቢኖሩትም የሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሰላምን ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ ስለመጓዙ ዘገባዎች ያስረዳሉ። ሁለቱ ሃገራት በተለይም ሱዳን ከአባይ ተፋሰስ ጋር ካላት ፈርጣማ ግንኙነት፤ ሩዋንዳም ከላይኛው ተፋሰስ ሃገራት አንዷ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የጉብኝቱ ፋይዳ የሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ለመሆኑም ከዘገባዎቹ ተነስቶ መገመት አይከብድም።

 

በጉብኝቱ ወቅት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራህም ሻንዱር ያረጋገጡትም ይህንኑ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያጠይቃል። ሚኒስትሩ እንዳሉት አገራቱ የሚኖራቸው የውሃ አጠቃቀም ላይ የጋራ ስምምነት እንዲኖር አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራች ትገኛለች። በቅርቡ በዩጋንዳ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ግብፅን ጨምሮ ሁሉም የተፋሰስ አገራት የተወሰነ ልዩነት ቢኖራቸውም መሰረታዊ ጉዳዩች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል ብለዋል። በጉዳዩ ላይ የሚሰራው የቴክኒክ ኮሚቴም ጠንክሮ እየሰራ ሲሆን በቅርቡ ጥሩ የሚባል ውጤት እንደሚገኝም ያላቸውን እምነት አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት በቀጠናው አገራት አለምን አያሰጋ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የውሃ ሃብትን አሟጦ መጠቀም የሚቻልበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ጠንክረው እየሰሩ ነው ማለታቸውም በዘገባው ተመልክቷል። የተለያዩ አገራትን የሚያስተሳስሩ ወንዞችንም የጸብ ሳይሆን የወደጅነት ምንጭ እዲሆንና የአካባው የውሃ አጠቃቀም ታሪክ እንዲቀየር ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት እንዳላትና ሱዳንም በዚህ ረገድ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ማድነቃቸውንም በተመሳሳይ።

በዚሁ ሂደትም፣ መሪዎቹ በካርቱም ምክክራቸው ኢትዮጵያና ሱዳን የቀጣናውን ሰላምና መረጋጋትን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት የአገራቱን ሁሉን አቀፍ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከዚህ በፊት ምክክር የተደረገባቸው ጉዳዮች በአግባቡ እየተተገበሩ ነው።

በመሆኑም ሁለቱ አገራት ሰላምና መረጋጋት በማስፈን እና የጋራ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። ለዚህም ከካርቱም አዲስ አበባ የተጀመረው የየብስ ትራንስፖርት በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ ያመጣውን ለውጥ፣ በአገር መከላከያና ደህንነት እንዲሁም የድንበር ጉዳይ ላይ የተሰሩ ስራዎች በአብነት ተጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስት ሀይለማሪያም ሁለቱ አገራትና ለቀጠናው ህዝብ ስትራቴጅካዊ ጥቅም ያላቸው ጉዳዮች ላይ ከሱዳን መንግስት ጋር አብሮ ለመስራት ያላቸውንም ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። በቀጣይም በሁሉም ዘርፍ አብሮ በመስራት በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን በማስፈንም ሆነ በአገራቱ መካከል ኢኮኖሚያ ትስስር ለመፍጠር ኢትዮጵያ የሚቻላትን ሁሉ የምታደርግ እንደሆነም ተገልጿል። የዚህ ሁሉ መነሻ ደግሞ ትናንት የጀመርነው የህዳሴ ግድብ ሳይሆን ለ22 አመታት በስራ ላይ ውሎ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ነው። በውጭ ግንኙነታችን መርሆዎ መሰረት ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በእኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የተመሰረተ፤ ከጠላትነት ፍረጃ የተላቀቀ የመልካም ጉርብትና ግንኙነት ነው ።  

 

የሰላም እና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን መሰረታዊ ማእቀፍ የአደጋ ተጋላጭነታችንን በመሰረታዊነት በመቀነስ ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ ነው። በዚህም አገራችን የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ለበርካታ አመታት አሸባሪዎችና አምባገነን መንግስታት በሚጭሩት ግጭትና ትርምስ የስጋት ቀጣና ሆኖ እያለ በዚህ መሃል የተረጋጋ ሰላምና ተከታታይ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት በማስመዝገብ አለምን ያስደመመ ለውጥ ማረጋገጥ ተችሏል። በዚሁ ፖሊሲ መርሆዎ ከአገሮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በእኩል ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሰረተ፣ የውጭ ሃይሎችን ሳይሆን ውስጣዊ አገራዊ ሁኔታው ዋነኛ የደህንነት ምንጭ እንደሆነ በመቀበል ድህነትና ኋላቀርነትን በማስወገድ፣ ዘላቂና ህዝቡ በየደራጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ልማት፣ ዴሞከራሲና መልካም አስተዳደር እውን እንዲሆን በማድረግ የአገራችንን ህዝቦች ለአደጋ ተጋላጭነት በማውስገድ ለጋራ ተጠቃሚነትና እድገት የሚተጋ ሃገርና ህዝብ መገንባት ነው።

የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን መነሻና መድረሻ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ጥቅም ማስጠበቅና የሀገራችንን ሉአላዊነት ማክበር እንደሆነ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በግልፅ ተደንግጓል። ከማንኛውም ሀገር ጋር የምናካሂዳቸው ግንኙነቶችም የሀገራቱን መንግስታት ሉአላዊነትና እኩልነት በማክበርና በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ባለመግባት ላይ የተመሰረተ ነው። የጎረቤቶቻችን ሰላምና እድገት በቀጥታ እኛንም እንደሚጠቅመንና እንደሚመለከተን ከጋራ መግባባት ላይ በመድረሳችን ጎረቤቶቻችን የየራሳቸው ብቻም ሳይሆን የእኛም ሰላም ደጋፊ የሆኑበት የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠራችን ረጅም ሰላማዊ አመታትን ማሳለፍ ከመቻላችንም በላይ በመግቢያው በተመለከተው አግባብ ያለጋራ ጥረት የትም መድረስ የማይቻል እንደሆነ ጎረቤቶቻችንም አምነው በመቀበል ለተመለከቱት አይነት የሁለትዮሽ ስምምነቶች አብቅቶናል።

አገራችን በተከተለችው ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምክንያት ከጎረቤቶች ህዝቦችና መንግስታት ጋር ለዘመናት የነበረን ያለመተማመን ግንኙነት በመሰረቱ ተቀይሮ በወዳጅነትና በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት መመስረት ችለናል። ከታላላቅ የአለም መንግስታትና አገሮች ጋር ለረዢም ዘመን በሰጪና ተቀባይ፣ በእርዳታ ብድር ላይ የተመሰረተው ግንኙነት በህዳሴው ማግስት ግንኙነቱ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የንግድና ኢንቨስትመንት አጀንዳ ዙሪያ ያጠነጠነ እየሆነ መጥቷል። ሀገራችን ከአፍሪካ ታላላቅ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ችላለች። እነዚህ ስምምነቶች የሚያጠይቁት ከሰጭና ተቀባይ ግንኙነት ተላቅቀን ከሁሉም አገራትና መንግስታት ጋር በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ስኬታማ የውጭ ግንኙነቶችን መገንባታችንን ነው ።  

መነሻችን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳን ጉብኝት ነውና ከአባይ ተፋሰስ አኳያ ነገሩን መመልከት ይገባል። በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚገባውና ስኬታማ ከሆኑት የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ስራዎች መካከል በናይል ተፋሰስ አዲስ የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ሁሉንም የላይኞቹን ተፋሰስ አገራት በብሄራዊ ጥቅማችን ዙሪያ ማሰለፍ መቻላችን ነው፡፡ ከላይ የተመለከተው የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መልእክት የሚያጠይቀውም ይህንኑ ነው። የዲፕሎማሲ ስኬታችን ይበልጥ ደምቆና ጎልቶ የሚታየው በናይል ተፋሰስ ዙሪያ ጊዜ ያለፈባቸውን ኢፍትሃዊ የሆኑና አሮጌ የቅኝ ግዛት የተናጠል ስምምነቶች ውድቅና ፈራሽ እንዲሆኑ ደግፈው የተፋሰሱ የራስጌ ሀገራትን ከጎናችን ማሰለፍ መቻላችን ነው፡፡ ይህ ውጤት የተገኘውም የተፋሰሱ የራስጌ አገራትን በአገራችን ትክክለኛና ፍትሃዊ አጀንዳና መርህ ዙሪያ በብቃት ማሰባሰብና አንድ አይነት አቋም እንዲይዙ ለማድረግ በትክክለኛው አቅጣጫ መንግስት በመንቀሳቀሱ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ያለፈበት የግብፅ ኢፍትሐዊ አቋም ትክክል እንዳልሆነና አግባብነትም እንደሌለው የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲገነዘቡት በማድረጋችን የግብፅ ፖለቲከኞችን ኢፍትሃዊ አቋም ማጋለጥ ችለናል፡፡ በዚህ በናይል ተፋሰስ አጠቃቀም ላይ የሱዳንን መንግሥት የግድቡን ሥራ ከመቃወም ይልቅ እንዲደግፍ ማድረግ የተቻለው፤ በግብፅም በኩል ከጭፍን ተቃውም ይልቅ ጉዳዩን በውይይትና በድርድር መፍታት ይቻላል የሚል መንፈስ እንዲያድርባቸው ማድረግ የተቻለው ለጋራና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ቁርጠኛ መሆናችንን ማሳየት በመቻላችን ነው፡፡ ሀገራችን የሶስትዮሽ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም ሃሣብ ከማመንጨት ጀምሮ የጥናቱን ውጤት ለመተግበር ፍፁም ተባባሪ መሆኗ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራትና በአለም አቀፍ ደረጃ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት እንዳለን ያረጋገጥንበት ነው፡፡  

በሌላ በኩል፤ የፀረ አክራሪነትና የፀረ ሽብርተኝነት ትግላችን ከአካባቢውና ከአለም አቀፍ አገሮችና ተቋማት ጋር የትግል አጋርነት መፍጠር አስችሎናል። በሀገር መከላከልና ደህንነት ጉዳዮች ያለን ትስስር በጎረቤት ሀገሮች ብቻ ሳይወሰን በአለም አቀፍ ደረጃም ሽብርተኝነትን እና ወንጀልን በመከላከል ረገድ በጋራ የምንሰራበት ሁኔታ መፈጠሩን በማረጋገጧ ነው ሱዳን የሰላምና የደህንነት ጉዳዮችን ከላይ በተመለከተው አግባብ አጀንዳዋ አድርጋ ለልኡኩ ያቀረበችው፡፡  

በአለም የዲፕሎማሲ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጦርነት የሚፋለሙ ሁለት ሃይሎች፤ ማለትም በደቡብ እና በሰሜን ሱዳን ኃይሎች አቢዬ የድንበር ግጭት ላይ አገራችንን የጋራ አሸማጋይና የፀጥታ አስከባሪ ሃይል እንድታሰማራ የደረሱት ስምምነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወስኖ የነበረበት የቅርብ ጊዜው ክስተትም የዚሁ ማሳያ ነው።  

ስለሆነም ነው፤ በሰሞንኑ ጉብኝት በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ፣ የአባይ ተፋሰስ አገራት የማዕቀፍ ስምምነት (nile busin initiative) እውን እንዲሆን፤ በባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል የተፈጠረው አለመስማማት እንዲፈታ በጋራ እንተጋለን ሲሉ ሀገራችን እና ሱዳን ያረጋገጡት። እንደኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦመር ሃስን አልበሽር  የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ብሎም ኢኮኖሚያ እድገት እንደሚያስፈልግ እና በሁለቱ አገራት የተጀመሩት የንግድና ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የእስካሁኑ ሚናቸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳሰባቸው ከላይ የተመለከቱት የውጭ ግንኙነት ድሎቻችንን ታሳቢ አድርገው ስለመሆኑ መገመት አይከብድም ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy