Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት

0 286

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት

                                                         ታዬ ከበደ

ታላቁ የኢትዩጵያ ህዳሴ ግድብ የአገራችንን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱን አገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ የሚገነባ ፕሮጀክት ነው፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ እንደመሆኑ መጠን፤ የሚያስበው ለአገሩ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ አገራት ህዝቦች ጭምርም ነው፡፡ የህዳሴው ግድብም ይህን የመንግስትን ዕኑ አቋም መሰረት በማድረግ በመገንባት ላይ ያለ ነው፡፡

መንግስት በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን ሰንቆ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዟል። በሂደቱም የህዝቡን ልማታዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ለውጤት መብቃት ችሏል።

በዚህም ህዝቡን ከጫፍ እሰከ ጨጠጫፍ በማንቀሳቀስ ሀገራችን የያዘቻቸውን ፕሮጀክቶች በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል።

ይህም ሀገራችን ትናንት የነበራትን የአቅም ውስንነት የቀረፈና የተለየ የአስተሳሰብ ዘውግ በመፍጠርም የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራት በአመዛኙ ወደ እኛ እሳቤ ማቅረብ የቻለ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል፡፡

ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ውጭ አሮጌና ዘመን ያለፈባቸው አስተሳሰቦች ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ያደረገና ግብፆች አሁን ለደረሱበት የአቋም ለውጥ መሰረት የጣለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ አሮጌው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት የተፋሰሱ ሀገራትን በውሃው እኩል ተጠቃሚነት እንዲሆኑ በሚያደርገው የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መተካት ለአማራጭና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች ስትገልፅ ቆይታለች፡፡ እርግጥ ሀገራችን የኢንቴቤውን ስምምነት ስትቀበል በምክንያታዊነት ላይ ተመስርታ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡

ይኸውም በመጀመሪያ ደረጃ የኢንቴቤው የትብብር ስምምነት የሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት መብት የሚያስጠበቅና እኩል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ እንጂ፤ ልክ እንደ ቅኝ ገዥዎቹ ስምምነት በጣት ለሚቆጠሩ ሀገሮች መብት የቆመ አለመሆኑን ስለምትገነዘብ ነው።

በዚህ የግንዛቤ መነሻዋም የተፋሰሱ ሀገራት የኢንቴቤውን ስምምነት እንዲፈርሙ ለዓመታት ያላሰለሰ ጥረቶችን አድርጋለች። ይህ ጥረቷም ቀደም ሲል ስምምነቱን ላለመቀበል ስታንገራግር የነበረችውን ግብፅን ጭምር በቅርቡ ‘ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ስምምነት ልመለስ’ የሚል ጥያቄ እንድታነሳ ጭምር አድርጓታል። ይህም ሀገራችን በግድቡ ዙሪያ በፊትም ይሁን አሁን የያዘችው አቋም ፍትሐዊና ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

የሀገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል።

ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው። ግድቡ የቀጣናውን ሀገራት የሚጠቅም ነው። የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኤሌትሪክ ሃይልን ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ ይቻላል። ይህም በድህነት ለሚሰቃየው ህዝባችን ህይወትና ኑሮ መሻሻል የሚረዳ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡

እናም ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ለዜጎች ኑሮ መለወጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ በመሆኑም የግድቡ ግንባታ በድህነትና በኋላቀርነት የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ስለሆነ የህልውናችን መሰረት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው ነገር ቢኖር፤ ሀገራችን ምንም እንኳን ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምትከተልና ውጤታማ መሆኗ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ወደ ኢንዱስትሪው መር ኢኮኖሚ መሸጋገሯ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የኤሌትሪክ ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡

እናም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተስተዋለ ከሚታየው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር ተያይዞ ለቀጣይነቱ የህዳሴው ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ የሚሰጠው ምላሽ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

ስለሆነም ወቅታዊውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከማስቀጠል ባሻገር፤ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞ መፋጠን አስተዋጽኦው የላቀ ነው። ለዚህም ነው ግድቡ ለሀገራዊው የህዳሴ ጉዞ ስኬት ዕድገትን የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የመቀጠልና ያለመቀጠል የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተደጋግሞ በመገለፅ ላይ የሚገኘው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም። የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምር እንጂ፡፡

እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ በጥቅሉ በኢትዮጵያ ህዝቦች ሙሉ አቅም በመገንባት ላይ የሚገኘው የህዳሴው ግድብ የአገራችንን ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን የተፋሰሱን አገራት ጥቅምንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy