Artcles

የታላቁ መሪ መንገድ

By Admin

August 17, 2017

የታላቁ መሪ መንገድ

ዳዊት ምትኩ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የአገራችንን ብሎም የምስራቅ አፍሪካን ችግሮች ለመፍታት የተጓዙባቸው መንገዶች ሰፋፊ ናቸው። አቶ መለስ በአገራችን ሚሊዮኖችን ከድህነት ማውጣት የቻሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን የነደፉ ከመሆናቸውም በላይ፤ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሰላማቸው እንዲጠበቅና ወደ ጋራ የትብብር ማዕቀፍ እንዲመጡ ጉልህ ሚና ተጫውተው ያለፉ መሪ ናቸው። እንዲሁም የአፍሪካ ልሳን በመሆንና ጥቅሞቿ ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ የሰሩ አፍሪካዊ አባት ናቸው። በአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃውልታቸው እንዲም ህብረቱ በቅርቡ ያሰለፈው ውሳኔ ይህን እውነታ የሚያረጋግጥ ነው።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል በተደረገው እጅግ መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል ወቅት የአሸናፊነትን ምስጢር በመጠንሰስ፣ ትግሉ የሚመራባቸውን ወታደራዊ ፍልስፍናዎችንና የፖለቲካ ሳይንሶችን በመተንተን ብሎም በሳል አመራር የሰጡ መሪ ናቸው።

አምባገነኑ የደርግ ሰራዊት የሰው ሃይሉ ከግማሽ ሚሊዩንን ያልተናነሰ ነበር፡፡ ይሁንና ይህን ግዙፍና አደገኛ ሰራዊት በታላቁ መሪያችን ስትራቴጂና ታክቲክ ቀማሪነት ከ70ሺህ በማይበልጥ ሰራዊትና ህዝብን ባማከለ ትግል ለአስራ ሰባት ዓመታት በተካሄደ መራር ትግል ማንኮታኮት ተችሏል።

ምርጡ የወታደራዊ ስትራቴጂና ታክቲክ ቀማሪው ታላቁ መሪ አቶ መለስ በተለይም በትግሉ ወቅት ወሳኝ የስትራቴጂ ጥያቄዎች ከተመለሱበት ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ በነደፏቸው ስልቶች የደርግ ስርዓት በአጭር ጊዜ እንዲደመሰስ ምክንያት መሆኑን ድርሳኖች ያስረዳሉ። ባለ ምጡቅ አዕምሮው መሪያችን በወቅቱ ባከናወኑት የፖለቲካ ስትራቴጂና ታክቲክ እንዲሁም የወታደራዊ ንድፈ ሐሳብ ስራዎች በትግሉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የህዝባዊ ጦርነት ባህሪ እንዲላበስ ማድረግ ችለዋል።

በዚህም ሠራዊቱ የህዝቡ የታጠቀ ግንባር ቀደም ኃይል ሆኖ ህዝቡም በደጀንነት እንዲሳተፍ ተደርጐ አምባገነኑን ኃይል ተዋግቶ በመበታተን ብሎም የተበተነውን ኃይል ህዝቡ በሚሊሻና በልዩ ልዩ ማህበራት ተደራጅቶ እንዲለቃቅመው በማድረግ ፈጣንና አስተማማኝ ድል ተገኝቷል። እናም ይህን በመለስ የጠራ የትግል አቅጣጫ የተመራው ትክክለኛው ህዝባዊ ጦርነት አምባገኑኑን የደርግ ስርዓት ከስድስት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ ማድረግ ተችሏል።

ከደርግ ውድቀት በኋላ አዲሲቷ ኢትዮጵያ በዜጎቿ እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ በተመሰረተ ህገ መንግስታዊ ፌዴራላዊ ስርዓት ላይ እንድትፀና በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ውድ የህዝብ ልጅ ናቸው። ሚሊዮኖችን ከድህነት ጠርዝ ላይ መንጥቀው ማውጣት የቻሉ አገራዊ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን የቀረፁ እንዲሁም ኢትዮጵያ በፈጣንና ተከታታይ የዕድገት መሰላል ላይ እንድትወጣ ያደረጉ የልማት አርበኛ ነበሩ።  

አቶ መለስ ዜናዊ ሀገራችን የአስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ባለቤት እንድትሆን ጽኑ መሰረት ገንብተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሌሎች ሀገራት በተለይም በጎረቤት ሀገራት አካባቢ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እጅግ የለፉና ውጤታማ  ለመሆን የበቁ አፍሪካዊ መሪ ናቸው።

ታላቁ መሪ በህይወት ዘመናቸው ሁሉ በጽኑ ያምኑና በተግባርም ያረጋገጡ የነበረው፤ የመንግስታችንና የመላው ህዝባችን የፀረ- ድህነት ትግል ግለቱን ጠብቆ ወደፊት ሊጓዝና ከስኬት ማማ ላይ ሊደርስ የሚችለው በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ሲኖር ነው፡፡

በመሆኑም ከሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተውጣ፣ ጠንካራ ህዝባዊ አመለካከት ያለው፣ በሥነ – ምግባሩ የታወቀ፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የመፈጸም ብቃት ያለውና ይህንንም ያለማቋረጥ እያሳደገ የሚሄድ ዘመናዊ ሰራዊት እንዲፈጠር መሰረቱን አኑረዋል።

በሌላም በኩልም ታላቁ መሪ በአገራችን ለመገንባት የተቻለው አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም በሌሎች አፍሪካዊ ወንድም ህዝቦች ዘንድ እንዲኖር ታላቅ ራዕይን ሰንቀው እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ትግል አካሂደዋል።

የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና ለማረጋገጥም አሸባሪነትንና አክራሪነትን በመዋጋት ጉልህ ሚና ያበረከቱ አባት ናቸው። በተለይም በሶማሊያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን ፅንፈኞችን በመዋጋትና ክፍለ አህጉሩ በሰላምና በልማት እንዲተሳሰር ያደረጉት ጥረትና ያስገኙት ውጤት ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ነው።

አቶ መለስ በተለያዩ ወቅቶች አገርን፣ ቀጣናውንና አፍሪካን እንዲሁም ዓለምን ሊጠቅሙ የሚችሉ ሃሳቦችን በማመንጨት ይታወቃሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ዓለምን ያስደመመው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያቸው ነው።

በዚህ ስትራቴጂያቸው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ትርፍ ካርቦንዳይኦክሳይድ የማትለቅበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ሲያልሙ የነበሩ መሪ ናቸው። በረጅሙ የአረንጓዴው ልማት ዕቅዳቸውም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በሰፊው አምርታ ከሚያስፈልጋት በላይ የሆነውን ኃይል ለጎረቤት ሀገር የመሸጥ፣ ነዳጅን ከዕፅዋት የማምረት ስትራቴጂን እንድትከተል እንዲሁም ካርቦንን ከአየር የመምጠጥ አቅሟ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ለማድረግ ያለመ ነው።

እርሳቸው የነደፉት የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ በአፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ፤ በርካታ አገሮች ሞዴሉን በመውሰድ እየተጠቀሙበት ነው። የታላቁ መሪያችን ብሩህ አዕምሮ ያፈለቀው ይህ የልማት አቅጣጫ ትናንት በረሃብና በድርቅ የምትታወቀውን አገራችንን፣ ለድርቅና ለረሃብ መባባስ ምክንያት የሆነውን የካርቦን ልቀት ለመቋቋም የመፍትሔው አካል ሆና እንድትታይ ያደረገ ወደር የማይገኝለት ተግባር ነው። ይህ ወደር የማይገኝለት ጭንቅላት ያፈለቀው ስትራቴጂ አገራችን የዓለምና የራሷ ችግሮች መፍትሔ አፍላቂ ሆና እንድትታይ ያደረገ በመሆኑ የምንኮራበት ምርጥ የዲፕሎማሲ ተግባራቸው ነው።

ስለ አቶ መለስ የዲፕሎማሲ ስኬት ካነሳን ዘንድ ታላቁ መሪ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ሀገራችንን በመሩባቸው ጊዜያት ያስተማሩን ታላቅ ጥበብ መኖሩን አንዘነጋም። ይኸውም በማንኛውም ወቅት ሁሉም ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር በመሆን  በግለሰብ ደረጃ የሀገራችንን ገፅታ መገንባት የሚችል መሆኑን ነው።

ማንኛውም ዜጋ በሚሰማራባቸው የስራ አካባቢዎች ሁሉ የብሔሩ ብሎም የሀገሩ አምባሣደር በመሆን የሀገራችንን ገፅታ መገንባት ይችላል፡፡ ስራውን በሚያከናውንበት ወቅት እንደ ግለሰብ የምንፈፅማቸው ማናቸውም ተግባራት የሀገራችን መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡ ባህላችንን፣ ወጋችንን፣ ትውፊቶቻችንን በየተሰማራንበት ቦታ ስናስተዋውቅ ደግሞ እግረ-መንገዳችንን እኛነታችንን እንገልፃለን፡፡

እኛነታችንን ስንገልፅም ሀገራችንን የቱሪስት መዳረሻ እናደርጋለን። ይህም ገቢያችን እንዲጨምር ያደርጋል። በዚያው ልክም ወደ መካከለኛ ገቢ የምንደረደርበት አቅም ይጨምራል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚያከናውን ማንኛውም ግለሰብ የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሁነኛ የዲፕሎማሲ  ተዋናይ ይሆናል።

የዕድገታችን ዋስ ጠበቃ መሆኑም እንዲሁ። አቶ መለስ እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ መሪ ያስተማሩን ይህንኑ ነው። እናም ‘እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ አምባሣደር ነው’ የሚለውን አባባል ሁሌም በማስታወስና በመተግበር፣ ታሪካቸው ለዝንተ ዓለም የማይፋቀውን የታላቁን መሪ መንገድ በየፈርጃችን እውን ማድረግ እንችላለን።