Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአደባባይ በዓላት ለቱሪዝም

0 579

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአደባባይ በዓላት ለቱሪዝም

ብ. ነጋሽ

ሰሞኑን በአማራና በትግራይ ክልሎች በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣት ልጃገረዶች የተሳተፉበት የአሸንዳ፣ ሻደይ ወይም ሶለል የተሰኘው የአደባባይ በዓል ተከብሯል። ይህ በዓል ከነሃሴ 16 እስከ 18 ለሶስት ቀናት ነው የሚከበረው። በትግራይ በዓሉ አሸንዳ ይባላል። በዛው በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች ሌላ ሰያሜ አለው። በአማራ በተለይ በዋግ ህምራ ይሄው በዓል ሻደይ በሚል ስያሜ ይጠራል። በራያ ደግሞ ሶለል ይባላል። በዓሎቹ በተለያየ ስያሜ ይጠሩ እንጂ ተመሳሳይ ናቸው። የአሸንዳ ወይም ሻደይ በዓል ሃይማኖታዊና ማህበራዊ መነሻወች አሉት። ይሁን እንጂ አከባበሩ ላይ ማህብራዊ ገጽታው ጎልቶ ይታያል።

አሸንዳ/ሻደይ/ኮለል የሚከበረው ነሃሴ 16 የፍልስታ ጾም ፍቺ በዓልን አስታኮ ነው። ይህን በዓል አስመልክቶ የተሟላ የተጻፈ ማስረጃ ማግኘት አይቻልም። ወይም መረጃዎቹ ሰዎች በቀላሉ ሊያገኟቸው በሚችሉበት ሁኔታ አልቀረቡም። ይሁን እንጂ በወሬ ደረጃ ያሉ መረጃዎች  የአሸንዳ/ሻደይ በዓል ሁለት መነሻ ምክንያቶች እንዳሉ ያመለክታሉ፤ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ።  ሃይማኖታዊው መነሻ ቅድስት ማርያም ያረገኝበት ዕለትን መዘከርን መነሻ ያደረገ ነው። በአፈታሪክ ደረጃ የሚነገረው ማህበራዊ መነሻ ደግሞ በጥንት ዘመን አባቷ ወደጦር ሜዳ ሄዶባት የነበረች አንድ የ17 ዓመት ልጃገረድ የህይወት ገጠመኝ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህች ልጃገረድ አባቷ በሰላም ከጦር ሜዳ እንዲመለስ በአካባቢው እየተዘዋወረች ትጸልይ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን አባቷ በሰላም ይመለሳል። ይሄኔ ልጃገረዲቱ ከበሮ እየመታች በመዝፈንና በመጨፈር ደስታዋን ገለጸች። ከዚህ በኋላ ልጃገረዶች በየዓመቱ በዚያ ዕለት እየተሰባሰቡ ከበሮ በመምታት ይጨፍሩ ጀመር የሚል ነው።

ያም ሆነ ይህ የአሸንዳ/ሻደይ በዓል ልጃገረዶች አደባባይ ወጥተው በነጻነት ሰሜታቸውን የሚገልጹበት፣ ማህበረሰቡ ሴቶች ላይ ከጫነው ጥብቅ ቁጥጥር ተላቀው የሚፈነጥዙበት ዕለት ነው። በመሆኑም በተለይ በልጃገረዶች ዘንድ እጅግ በጉጉት የሚጠበቅና የሚከበር የአደባበይ በአል ነው።

እርግጥ አሸንዳ/ሻደይ ለኢትዮጵያ ብቸኛው የአደባባይ በዓል አይደለም። የመስቀል ደመራ፣ ጥምቀት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተደፈቀበት ወጥቶ በዩኔስኮ የማይጨበጥ የዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ የበቃው ፊቼ ጨንበላላ፣ የኦሮሞዎች የዘመን መለወጫና የምሳጋና እለት ኢሬቸ መልካ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ናቸው። ሌሎችም እስካሁን ይፋ ያልወጡ የአደባባይ በአላት ይኖራሉ።

የአደባባይ በዓላት በህዝብ ውስጥ ማህበራዊ ትስስር በመፍጠር የማህበረሰብን አንድነት ያጠናክራሉ፤ ያጸናሉ። በአንድነት ውስጥ መተዋወቅ አለ። በመተዋወቅ ውስጥ መከባባር አለ። በመከባባር ውስጥ ደግሞ ሰላም አለ። የአደባባይ በዓላት ለአንድ ማህበረሰብ የኪነጥበብ እድገትና ለከያኒዎች መፈጠር አስሰተዋጽኦ አላቸው። በሃገራችን የአደባባይ በዓላት ላይ የሚታዩት ጭፈራዎችና ዘፈኖች ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ብዙዎቹ የሃገራችን የባህል ዘፈን ተጫዋቾችና ዳንሰኞች አፋቸውን የፈቱት፣ ሰውነታቸውን የፈተሹት ጥምቀትን አሸንዳን/ሻደይንና ፊቼ ጨንበላላን በመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት ነው።

በኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላትን ወቅቱን ጠብቆ ከማከበር ያለፈ፣ ለማጎለበት፣ በቅርስነት ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ የተሰራ ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ ስራ አለ ለማለት አያሰደፍርም። እርግጥ ከቅርብ አመታት ወዲህ በተለይ የመስቀል ደመራና ፊቼ ጨንበላላን በዩኔስኮ ቅርስነት ለማስመዝገብ በነበረው ሂደት ተጠንተው በጽሁፍ ሰነዶች ተዘጋጅተውላቸዋል። በቀጣይነት ይመዘገባሉ ተብለው የሚጠበቁት ጥምቀትና ኢሬቸን በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ መረጃ ማግኘት ይቻላል። ከዚህ ውጭ ስላሉት ግን ምንም መረጃ ማግኘት አይቻልም። ለምሳሌ አሸንዳ/ሻደይን በተመለከተ የጽሁፍ መረጃ ማግኘት አይቻልም።

የተቀረው ዓለም በተለይ የሰለጠኑት ሃገራት የአደባባይ በዓሎቻቻውን (carnivals)  በሚገባ መዝግበው ማስተዋወቅ ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጠረዋል። ሆኖም በዓለም ላይ በታዳሚ ብዛት ከ1ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ያላቸው ተብለው የሚታወቁት አብዛኞቹ የአደባባይ በዓላት ከኢትዮጵያ ጥምቀት፣ አሸንዳ/ሻደይ በታች ሰዎች የሚሳተፉባቸው ናቸው። የኢትዮጵያ የአደባባይ በዓላት ግን እስከ 100ኛ ባሉ የዓለም የአደባባይ በዓላት ተርታም አልተመዘገቡም። ይህ ሁኔታ በዓላቱ በምን ያህል ደረጃ ተደብቀው አካባቢያዊ ሆነው እንደቀሩ በግልጽ ያሳያል።

ይህን ሁኔታ በግልጽ ለመረዳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ እውቅና ካገኙት የአደባባይ በአላት መሃከል የተወሰኑትን እንመልከት።

የብራዚል የሪዮ ዲ ጄኔሮ የአደባባይ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት የቀምጧል። ይህ በአል ከትንሳኤ በዓል 40 ቀናት ቀደም ብሎ የሚውል ሲሆን፣ በሪዮ ጎዳናዎች ላይ ለአራት ቀናት ያህል ነው የመከበረው። በአሉን ለመመለከት እስከ 2 ሚሊን ሰዎች ይገኛሉ። በበአሉ ላይ ከ200 የሳምባ ዳንስ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ በብዙ ሺህ የሚቀጠሩ ወጣት ዳንሰኞች እንዲሁም ከአጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ የጎዳና ሙዚቀኞች የዳንስና የሙዚቃ ትዕይንት ያቀርባሉ።

በአውሮፓ የእንግሊዝ ለንደን ኖቲንግ ሂል የአደባባይ በዓል ተጠቃሽ ነው። በዚህ የአደባባይ በዓል ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች ይታደማሉ። ከ50 ሺህ በላይ ዳንሰኞችና ሙዚቀኞች ትርኢት ያቀርቡበታል። በበአሉ ላይ የተለያዩ የካረቢያን ምግቦችም ለገበያ ይቀርባሉ።

የጀርመን ኮሎኝ የአደባባይ በዓልም በአውሮፓ ተጠቃሽ ከሆኑት አንዱ ነው። በዚህ የአደባባይ በዓል ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች እንደሚታደሙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሚከበረው በዚህ አደባባይ በዓል ላይ ታዋቂ ግለሰቦችና ፖለቲከኞችም ይገኛሉ።

ከዚሁ ከአውሮፓ ሳንወጣ የፈረንሳይ ናይስ የአደባባይ በአል ለ15 ቀናት የሚከበር ሲሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ ታዳሚዎችና ከ1 ሺህ በላይ ሙዚቀኞች ይሳተፉበታል። በዚህ የአደባባይ በአል ላይ ከ1 መቶ ሺህ በላይ አበባዎች የበተናሉ። የጣሊያን ቨኒስ ቬንዚያ የአደባባይ በአል የጥምቀት በአልን አስታኮ ይካሄዳል። በዚህ በዓል ላይ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን ለሃያ ቀናት የሚከበር ነው።

በሰሜን አሜሪካ ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት መሃከል ኒው ኦርሊዮን የሚከበረው የማርዲ ግራስ  የአደባባይ በዓል ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል። ይህ በዓል በየዓመቱ ጃነዋሪ 6 በጥምቀት ጾም 12ኛ ሌሊት ላይ የሚከበር ሲሆን፣ እስከ 300 ሺህ ሰዎች ይታደሙበታል።

የካናዳ ከዩቤክ የክረምት የአደባባይ በአል 5 መቶ ሺህ ያህል ሰዎች ይሳተፉበታል። በአሉ ለ17 ተከታታይ ቀናት በአደባባይ የሚከበር ሲሆን በዓለም አቀፍ አቀፍ ደረጃ ትልቁ የከረምት የአደባባይ በመሆን የታወቃል።

በካረቢያን ሃገራት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ትሪኒዳድና ቶቤጎ የስፔን ፖርት የአደባባይ በአል ተጠቃሽ ነው። ይህ በዓል በኩዊን ፓርክና በሃገሪቱ ብሄራዊ ስታዲየም እስከ 3 መቶ ሺህ በመደርሱ ታዳሚዎች ታጅቦ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ጥምቀት፣ ዳመራ፣ ፊቼ ጨንበላላ፣ ኢሬቻ፣ አሸንዳ/ሻደይ፣ ወዘተ በዓለም አቀፍ የአደባባይ በዓላት ተረታ ተጠቀሰው አይገኙም። የበዓሎቹ ድምቀትና የተሳታፊዎቹ ብዛት ግን ከላይ ከጠቀስኳቸው ዓለም አቀፍ እውቅና ካገኙና በቱሪት መስህብነት ከሚታወቁ የአደባባይ በዓላት ይበልጥ እንደሆን እንጂ አያንስም። በዓላቱን ቱሪስቶች ኢንተርኔት ላይ በቀላሉ ተመልክተዋቸው ሊታደሙባቸው በሚችሉበት ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራ የኢትዮጵያውያን ብቻ ነው። ይህን ማንም ሊሰራልን አይችልም።

ኢትዮጵያ ጥምቀት፣ ዳመራ፣ አሸንዳ/ሻደይ፣ ፊቼ ጨንበላላ፣ ኢሬቻን በመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት ብቻ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን መሳብ እንደምትችል የሌሎች ሃገራት የአደባባይ በዓላት ተሞክሮዎች ያረጋግጣሉ። በዓሎቹ ቱሪስቶችን መሳብ በተለይ ለየአካቢው ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማስገኘት በሚችሉ መልክ የማልማትና የማስተዋወቁ ስራ ብዙ ይቀረዋል። የአደባባይ በዓላቱ በሚከበርባቸው አካባቢዎች የበዓሉ ተሳታፊዎች የሚደምቁባቸውን አልባሳት፣ ጌጣጌጥ፣ የአካባቢውን ባህላዊ ምግቦች ለመጠቀም አመቺ በሆነ አኳኋን አዘጋጅቶ ለገበያ ማቅረብ የአካባቢው ነዋሪዎች ከበዓሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አንዱ መንገድ ነው። በዚህ ረገድ ጅምር ስራዎች ቢታይም፣ አሁንም ገና ነው። ሌሎች ቱሪስቶችን ለመሳብና ለማስተናገድ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ የልማት ተግባራት እንደተጠበቁ፣ የአደባባይ በዓላት ላይ ላይ ያተኮሩ አካባቢያዊ የቱሪዝም የልማት ስራዎች ሊታሰብባቸው ይገባል። የአደባባይ በዓሎቻችንን ለቱሪዝም ልማት እናውል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy