Artcles

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባት የሚለው ስያሜ ይበዛባቸው ይሆን?

By Admin

August 13, 2017

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባት የሚለው ስያሜ ይበዛባቸው ይሆን?

አባ መላኩ

አንዳንዶች የሌላቸውን  ፈጥረው  ወይም  ያላቸውን ጥቂት  ነገር አጋነውው የአገራቸውን መልካም ገጽታ በዓለም ፊት ለመገነባት ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ።  በእርግጥ  በሃሰት ወይም በኩሸት የሚገነባ  መልካም ገጽታ  ከአህያ ቆዳ እንደተሰራ ቤት እንደሚባለው ዓይነት  እንደሚሆን  ይታወቃል። የሌለ ነገርን በመፍጠር ወይም ትንንሽ ነገሮችን እያጎንን የአገራችንን ገጽታ እንገንባ ማለቴ ሳይሆን፤  አገራችን በተጨባጭ ያሏትን እና ያፈራቻቸውን መለካም ነገሮች  ለዓለም  በቅጡ ማስተዋወቅ ብንችል ለአገራችን ገጽታ  መለወጥ ጠቀሜታ እንዳለው ማወቅ ግን ተገቢ ነው እላለሁ። ኢትዮጵያ ለገጽታዋ ግንባታ የሚያገለግል የበርካታ ነገሮች መገኛ ከመሆኗ ባሻገር ስመጥር የሆኑ ግለሰቦችንም ማፍራት የቻለች ናት።

 

እኛ ኢትዮጵያዊያን  ያሉንን  መልካም ነገሮች ለዓለም ከማስተዋወቅ አኳያ  እጥረቶች እንዳሉብን መረዳት ይኖሩብናል።  ለዚህ ጥሩ ማሳያ የቱሪስት መስህቦቻችን ናቸው። አገራችን በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ  የቱሪስት መስህቦች በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ መሰለፍ የምትችል አገር ናት። ይሁንና  እነዚህን ድንቅ የሆኑ ተፈጥሮዊና ታሪካዊ  የሆኑ የቱሪስት መስቦቻችንን   ለዓለም  ማስተዋወቅ ላይ  በአግባቡ አልሰራንም። በመሆኑም እዚህ ግባ የሚባል  የቱሪስት መስህብ ከሌላቸው  የጎረቤት አገሮች ጋር እንኳን  በአንጻራዊነት  ስንመለከተው አገራችን  ከዚህ ኢንዱስት ያገኘችው ገቢ  የሚያኩራራ አይደለም።

 

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለአንድ አገር ስኬትም ሆነ ውድቀት  በመሪነት የሚቀመጥ ሰው ትልቁን ሚና ይጫወታል። ለውድቀት መሪ ተወቃሽ እንደሆነ ሁሉ ለስኬትም  ተመስጋኝ  ሊሆን ይገባል የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ። በአገራችን ይህ አሰራር ብዙም የተለመደ ነገር አይደለም። እንደእኔ እይታ  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ  ለአገራችን መለወጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካበረከቱ ጥቂት ሰዎች በቀዳሚነት የሚነሱ ናቸው። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ከጭቆና አላቀዋል፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተግብረዋል፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን አድርገዋል፣ መሰረተ ልማት በሁሉም አካባቢዎች ፍተሃዊ በሆነ መንገድ እንዲስፋፋ አድርገዋል፣  ፈጣንና ተከታታይ የሆነ የኢኮኖሚ  ዕድገት በማስመዝገብ ሚሊዮኖችን ከከፋ ድህነት እንዲላቀቁ አድርገዋል፣ ወዘተ።  ይህ ተግባራቸው ለእኔ እጅጉን ታላቅነታቸውን ያሳየኛል።

 

ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስና  ታላቁ መሪ አቶ መለስ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁለመናዋ ናቸው።  በርካታ ሰዎች መለስ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መስራች ወይም አባት ሲሏቸው  ይገልጿቸዋል። ይህን ያሏቸው የነበሩት ታግለው ስለመጡነና አገር ስለመሩ ብቻ ሳይሆን  በህይወት በነበሩበት ወርት ባስመዘገቧቸው ተጨባጭ ውጤቶች ነው።  አዎ አቶ መለስ  እንደእኔ እንደኔ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ነገሯ ነበሩ። የእኚህን ታላቅ ሰው  አምስተኛ አመታቸውን መታሰቢያ በመጪው ሳምንት እናከብራለን።

 

አቶ መለስ በበሳልና አርቆ ማሰብ ችሎታቸው ኢትዮጵያን  ከመበታተን ታድገዋታል። ህብረተሰቡን ከእርስ በርስ ዕልቂት አትርፈውታለ።   በ1983 ዓ.ም ደርግ ሊወድቅ  ሲያጣጥር አካባቢ ጀምሮ እስከውድቀቱ  ማግስት  ድርስ  ኢህአዴግን ጨምሮ በርካታ የታጠቁ የብሄር ድርጅቶች በአገራችን እስከአፍንጫቸው  ታጥቀው ነበር። በዚያን ወቅት በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች  ኢትዮጵያ አበቃላ፣  ተበታተነች፣ ወዘተ የሚል አስተያየታቸውን ሲሰጡ ነበር። ይሁንና እኚህ ታላቅ መሪ   በተከተሉት በአግባብ  በተጠናና በታቀደ  በሳል አካሄድ   የሁሉንም ጽንፈኛ አካላት አስተሳሰብ የሚያቀራርብ ብሎም  ጠረጴዛ ዙሪያ የሚያሰባስብ ሃሳብ በማምንጨት አገራችንን ለውድቀት ያበቁ የነበሩ  ክፉ ነገሮች ሁሉ  እንዳይከሰቱ አድርገዋል። ለዚህ ነው በርካቶች እኚህ ታላቅ መሪን  የአዲሲቷ  ኢትዮጵያን አባት፣ የአገራችን ውድቀት ታዳጊ አድርገው  የሚጠሯቸው። እውነት ነው ለእኔ ይህ ስያሜ ይበዛባቸዋል የሚል እሳቤ የለኝም።

 

እኚህ ታላቅ መሪ በተከተሉት የበሰለ አመራር ኢትዮጵያ ያለምንም ደም መፋሰስና  መንግስት አልባ ሳትሆን  ሁሉም  የተወከለበት  የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም አድርገዋል። ከዚያም አገሪቱ  የምትመራበትን የሽግግር  ቻርተር በሁሉም ተሳትፎ እንዲዘጋጅ በማድረግ  መንግስት    በህግና መመሪያ  እንዲተዳደር  አድርገዋል። የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ነው። የሶማሊያው መሪ የነበሩት ጄኔራል ዚያድ ባሬ ከስልጣን ሲባረሩ በሶማሊያ የተከሰተወን ነገር ማስታወስ ይቻላል። አገራችን እንዲያ  ያለ የፖለቲካ  ማጥ ውስጥ እንዳትዘፈቅ አቶ መለስ ታሪክ  የማይረሳው ውለታ ለአገራቸው አበርክተዋል።  

 

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሽግግሩ ዘመኑ በርካታ መሠረታዊ ተግባራት የተከናወኑበት ነበር።  ከሁሉም ልቆ የሚጠቀሰው የአገሪቱ የበላይ ህግ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የማርቀቅና የማፅደቅ ተግባር የተፈፀመበት ጊዜ ነው፡፡  ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት  ህገመንግስታዊ እውቅና እንዲኖረው ታላቁ መሪ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። እንደቀድሞው ስርዓቶች በአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ኢትዮጵያዊነትን  በሃይል  የተጫነባቸው  ነገር ሳይሆን ፈቅደውና መርጠው የተጎናጸፉት ዜግነት እንዲሆን  አቶ መለስ  ትልቅ ሚና ነበራቸው። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አንድነትም በህዝቦቿ መፈቃቀድና መልካም ምኞት ላይ የሚመሰረት እንጂ በኃይልና በግዴታ የሚጫን መሆን የለበትም የሚለው አዲስ አስተሳሰብ  ያፈለቁት እኚሁ ታላቅ መሪ ነበሩ።

 

ታላቁ መሪ ለኢትዮጵያ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች  ህገመንግስታዊ እውቅና እንዲኖረው በመታገላቸው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ማግኘት እንድትችል አድርገዋል። የኢፌዴሪ ህገመንግስት  ህዝቦች  የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳባቸውን  በተለያዩ መንገዶች የመግለፅ እንዲሁም የመደራጀትና የመዘዋወር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ አድርጓል።  በየአምስት ዓመቱ በሚካሄድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ህዝቡ በመረጠው ሃይል እንዲተዳደር መለስ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል። አገሪቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን በመቻሏ ልማትን ማፋጠን ተችሏል። በአገሪቱ  በርካታ ማህበራዊ  መገልገያ  መሰረተ ልማቶች ተስፋፍተዋል። በዚህም የአገሪቱ ህዝቦች አኗኗር እጅጉን እንዲሻሻል አቶ መለስ  ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

 

ታላቁ መሪ  አቶ መለስ ኢትዮጵያ ያልተማከለው አስተዳደር እንዲኖራት ታግለዋል።  የፌዴራል ሥርዓቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊና  ጉዳዮች ላይ  ሥር ነቀል ለውጦችን አስከትሏል። ከሁሉ በፊት የአገራችን ጭቁን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎች የነበሩት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነት፣ ባህልን የማሳደግ፣ ቋንቋን የመጠቀም መብቶች እንዲረጋገጡ የፌዴራል ስርዓቱ  አግዟል። በዚህም አገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ በመቻሏ  ተጨባጭ የሆኑ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ  የታየ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች  ማምጣት ተችሏል።  ይህ የታላቁ መሪ ዋንኛ ስኬት ነው።  

 

ዛሬ ኢትዮጵያ ማስመዝገብ ከቻለቻቸው ድንቅ ስኬቶች ላይ ሁሉ  የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አሻራዎች በጉልህ አርፈውባቸዋል። ኢትዮጵያ  በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ  መድረኮች የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖራት በማድረግ ረገድ  መለስ ወሳኝ ሚና ነበራቸው።  አገራችን ብቻ ሳትሆን  ዓለም የአረንጓዴ ልማት አራማጅ ተከታይ እንዲሆን ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበሩ።  ታላቁ መሪያችንን የዓለም ታላላቅ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ የጥበብ ሰዎች ወዘተ ሳይቀሩ አድናቆታቸውን ቸረዋቸዋል።  እኚህ ታላቅ ሰው  በሞት ሲለዩ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ እንዲሁም የዓለም ህዝብ  በጥልቅ የሃዘን ስሜት እንዲዋጥ አድርገዋል፡፡ የእኚህ ታላቅ ሰው ራዕይ ውጤታማ መሆን በመጀመሩ የአገራችን  ገጽታ  በመቀየር ላይ ነው።

ታላቁ መሪ የኢትዮጵያ ሕዳሴ መሃንዲስና የለውጥ ሀዋርያ በመሆን  በርካታ  ዜጎቻቸውን  ከድህነት አርንቋ አላቀዋታል። እሳቸው በተለሙት መስመር በመጓዝ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ  የአገራችንን ሕዳሴ  ማሳካት እንደሚቻል በእርግጠኝነት መናገር   ይቻላል።   ባለራዕዩ መሪያችን ከወጣትነታቸው ጊዜያቸው ጀምሮ ለህዝባቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ታግለው አታግለው  እንደሻማ ቀልጠዋል። ታዲያ  እኚህን  ታላቅ ሰው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባት ብንላቸው ይበዛባቸው ይሆን?