ethiopian news

Artcles

የአፍሪካ የሰላም አምባሳደር

By Admin

August 02, 2017

የአፍሪካ የሰላም አምባሳደር

ዳዊት ምትኩ

አገራችን የአህጉሩ የሰላም አምባሳደር መሆኗን አስመስክራለች። ኢትዮጵያ በዚህ የሰላም አምባሳደርነቷ በቅድሚያ የራሷን ሰላም ያስጠበቀች፣ ቀጥላም የምስራቅ አፍሪካንና የአፍሪካን ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ በርካታ ተግባሮችን አከናውናለች፡፡ አፍሪካ ውስጥ ስለ ሰላም ሲነሳ ቀድማ የምትጠቀሰው አገራችን በምትከተለው ፅኑ የሰላም አቋም በቀጣይም የአፍሪካ የሰላም አምባሳደር መሆኗን ትቀጥላለች፡፡

መንግስት ለሀገራችን ሰላምና ልማት  እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች እንዲሁም ለአፍሪካ ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ጽኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ምርጫው ነው። ለምን ቢሉ የሀገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው፡፡

ታዲያ በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለው የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ዓላማን የሰነቀና ውጤቱም ለሀገራችንም ሆነ ለአካባቢያችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ የሚታበይ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በአካባቢያችንና በአህጉራችን ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት ስኬቶች መካከልም ረጅም ኪሎሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን ቀውስ ለማርገብ የተካሄደው ጥረትና የተመዘገበው አበረታች ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡

ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ለጥ ያለና ውሃ ገብ የሆነው መልከዓ ምድሯ እንዲሁም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል እንደሆነች ብዙዎቹን ያስማማ ሃቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ሀገሪቱ ግን ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለመቆየት ተገዳለች።

በዚህም ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግ በመቻሏ ለተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በጐረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሃገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት፡፡

በእርግጥ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ሀገሪቱ ነፃነቷን ከተጐናፀፈችበት እ.ኤ.አ. በ1956 ነበር። ይህ ሁኔታም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያደረሰው አሉታዊ ተፅእኖ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን በሀገሪቱ ለደረሰው ቀውስ እልባት የመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራዎች የተካሄዱ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ለፍሬ መብቃት አልቻሉም፡፡ ይልቁንም የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ በየጊዜው “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉት ዓይነት ሆኖ እየተባባሰ ሊሄድ ችሏል፡፡

ዳሩ ግን የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነትና መልካም ግንኙነት መስፈን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን መጠናቀቅ  ተከትሎ የሀገራቱ ግንኙነት እያደገ ከመምጣቱ ባሻገር የላቀ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡

ዛሬ ላይም ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፤ የባህል ትስስር፤ የፀጥታና ደህንነትና ሌሎች ተግባራት በመከናወናቸው ጠንካራ ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ ለዚህም ነው በሁለቱ ሃገራት መካከል የመተማመን መንፈስ መፍጠር የተቻለውና የሱዳን መንግስትና ህዝብ ከኢትዮጵያ በላይ ችግሩን ሊፈታለት የሚችል ሃይል እንደሌለ በማመን በዳርፋር ለተከሰተው ቀውስ እልባት ለመስጠት የኢትዮጵያ መከላከያ የሰላም አስከባሪ ሃይል መሰማራትን ቀዳሚ ምርጫ ያደረገው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ውጤት በሆነውና በጥርጣሬ ከመተያየት ይልቅ መተማመንን የፈጠረው የመንግስት ጥረት የሱዳን መንግስት ላቀረበው ጥሪም ከ5ዐዐዐ በላይ ሠላም አስከባሪ ሃይሉን በመላክ ፈጣን ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ይህም የሱዳን ህዝብ በጐ እይታ እንዲኖረው ያደረገ ተግባር ነው::

ታዲያ እዚህ ላይ መንግስት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች እንደሚሉት ሳይሆን የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ እንደሆነ ሊጤን ይገባል፡፡ ለምን ቢሉ እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ በመሆኑ ነው። አዎ! የእነርሱ ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና የላቀ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡

እርግጥም በሀገራችን ሰላም ላይ የቅርብ ተጽዕኖ ያላት የሱዳንን ችግር ለመቅረፍ በመንግስታችን የተካሄደው ጥረት ምንጩ ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሰላሟን ዘላቂ ለማድረግ ምንጊዜም ቢሆን ወሳኙ ነገር  በውስጥ የምታካሄደው የፀረ-ድህነትና ኋላ ቀርነት ትግል ሊሳካ የሚችለው ተጋላጭነታችን ሲወገድ ብቻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጐረቤቶቻችን ላይ የሚያጋጥም ትርምስንና ቀውስን መፈታት ካልተቻለ ጦሱ ለእኛም የሚተርፍ ስለሆነ ነው፡፡

መንግስት በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሀገሪቱ ለጀመረችው የፈጣን ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ይህን መነሻ ታሳቢ ባደረገ መልኩም መንግስታችን ለሰላም ካለው ጽኑ አቋም በመነሳት ለዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ጐረቤት ሀገር ሱዳን፣ በተለይ ደግሞ በቅርቡ ሰላሟ እየደፈረሰ ለምትገኘው ደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ለዘመናት በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ለህዝባቸው ነጻነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተው፣ የናፈቁትን ሰላምና ልማት ማጣጣም የጀመሩት የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ድርጅታቸው “ኤስ ፒ ኤል ኤ” ዳግም ወደ እርስ በርሰ ጦርነት በመግባቱ ለከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት መዳረጋቸው ወቅታዊው ዕውነታ ነው፡፡

እርግጥ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ወቅታዊ ችግር የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ መሳብ ቢችልም እልባት ከመስጠት አንፃር ግን የኢፌዲሪ መንግስትና ኢጋድን ያህል የተንቀሳቀሰ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የዓለማችን አዲስ ሀገር በሆነችው ደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ የአደጋው ተጋላጭ የሚያደርገው በዋነኝነት የሀገሪቱን ዜጎች መሆኑን እስካሁን ከደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መገንዘቡ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ዳፋው ለአካባቢው ሀገራት መትረፉ አይቀሬ ነው፡፡ ኢጋድና የኢፌዲሪ መንግስት የደህንነት መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ሀገራዊ ህልውናን ማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ በማመን፣ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር የማስመስከር እንቅስቃሴያቸውን በመጀመር ግምባር ቀደም ሚናቸውን በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሶማሊያም አሸባሪዎችን ለመደምሰስ ተመሳሳይ ተግባር እየፈፀሙ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ስለ ሰላም ሲነሳ የኢትዮጵያ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሀገር ሆናለች፡፡ ይህም የአፍሪካ የሰላም አምባሳደር እንድትሆን አድርጓታል፡፡