ethiopian news

Artcles

የኤርትራ ባለሟሎች ተፈርተው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አይኖርም

By Admin

August 16, 2017

የኤርትራ ባለሟሎች ተፈርተው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አይኖርም

ኢብሳ ነመራ

ሰሞኑን  በጥቂት የአማራ አካባቢዎች ጤናማ ያልሆኑ ሁኔታዎች ታይተዋል።  በተለይ በባህርዳር ከተማ። ነሃሴ 1፣ 2009 ዓ/ም በባህርዳር ከተማ መደብሮችንና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን የመዝጋት፣ የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት የማቋረጥ አድማ ተካሂዷል። በአድማው ዋዜማ ሌሊት ቦምብ ፈንድቶ ነበር። ለዚህ አድማ ምክንያት እንደሆነ የተነገረን ባለፈው ዓመት በከተማዋ ተፈጽሞ የነበረውን ሁከት መዘከር ነው። አድማው ሌላ ምክንያት አልነበረውም። የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም (ቪኦኤ) ዘገባዎች መንግስትን የሚያስጨንቅ ተቃውሞና አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚሹና አንዳንዴም አለመረጋጋቱን የሚመሩና እንዲባባስ የሚፈልጉ ሰዎችን በዋቢነት ስለሚጠቅስ መረጃወን ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ ነው ብሎ መውሰድ ባይቻልም፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን አንዳንድ ወረዳዎች ነሃሴ 4፣ 2009 ዓ/ም መደብሮች ተዘግተው እንደነበረ ተነገሮናል።  

ቪኦኤ የመኢአድ ዋና ጸሃፊና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ያላቸውን አቶ አዳነ ጥላሁን አነጋግሮ እንዳሰማን፤ በምሥራቅ ጎጃም ሸበል በረንታ፣ ብቸና፣ ደብረ ወርቅ፣ ረቡዕ ገበያ ወይም ስናን፣ መርጦ ለማሪያም፣ ሞጣ ቀራንዮና ፈለገ ብርሃን ወረዳዎች በሙሉ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው ውለዋል።

ቪኦኤ በባህር ዳር ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን የነጋዴዎች አድማ አስመልክቶ ለደህንነታቸው ተብሎ ድምጻቸው የተቀየረ ብሎ ያሰማን ሰው በከተማዋ ስለፈነዳው ቦምብና ስላስከተለው ውጤት ተናግረዋል። ሰውየው ያዩትን ብቻ አልነበረም የነገሩን። ቦምቡ እንዲፈነዳ የተደረገበትን ምክንያትም ጨመረው ነገረወናል። በነጋታው አድማ የሚደረግ መሆኑን ለማስታወስ የተደረገ እንደሆነ ነበር የተናገሩት።  ግለሰቡ ከፍንዳታው ጀርባ ያለውን ዓላማም የሚያውቁ መሆኑ አድማውን ካዘጋጁት የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ትእዛዝ ተቀብለው ከሚያስፈጽሙት አንዱ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንድንገምት አድርጎናል። ይህ ካልሆነ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች ያፈነዱትንና ለምን እንዳፈነዱ በማንኛውም መንገድ ያልገለጹትን የቦምብ ፍንዳታ ዓላማ መናገር አይችሉም ነበር።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ወረዳዎች የተዘጉ ሱቆችን አስመልክቶ በቪኦኤ የቀረበው መረጃም እውነትን ከመናገር ይልቅ ተቃውሞ መኖሩን ማጉላት የተፈለገ መሆኑን ያሳያል። ይሄም አድማው የተፈፀመባቸውን ቦታዎችን ለማመልከት ከተሞቹን መጥራት የሚቀል ሆኖ ሳለ ወረዳዎቹ ከመጠራታቸው የመነጨ ነው። ምናልባት ከተሞቹን ወረዳዎች ብለዋቸው ከሆነ እኔ አካባቢውን ስለማላወቀው በእርግጠኝነት መናገር አልችልም። ይህ ሆኖ ከሆነ ቀላል ስህተት ተደርጎ ሊወሰድ ይችል ይሆናል።

የንግድ መደብሮችን የመዝጋት አድማ መካሄዱን ለመናገር ወረዳዎች ተጠርተው ከሆነ ያለአግባብ ለማጋነን የተፈለገ ነገር መኖሩን በግልጽ መገንዘብ ይቻላል። አንድ ወረዳ አብዛኛው መሬት ገጠርና የአርሶ አደር መኖሪያ ነው። የንግድ መደብሮች ያሉት ደግሞ በከተሞች ውስጥ ነው። እናም የወረዳው መደብሮች ተዘጉ የሚለው የመኢአድ ዋና ጸሃፊ ጥቆማ ከእውነትነት ይልቅ ውዥንብርነቱ ያይላል። የቪኦኤ ጋዜጠኞቹም ችግር መኖሩን ማስተላለፍ እንጂ እውነት እንዲታወቅ ስለማይፈልጉ፣ የወረዳዎች ስም ሲጠቀስ በወረዳዎቹ ውስጥ የትኞቹ ከተሞች? ብለው እርግጡን ማሳወቅ ይገባቸው ነበር። ይህ የውዥንብር አጋፋሪ ያደርጋቸዋል።

መረጃ ተብዬውን ያልጠራ ወሬ ለቪኦኤ ያቀበሉት የመኢአድ ዋና ጸሃፊ፣ አድማው በነጋዴዎች ላይ የተጣለውን ግብር በመቃወም የተነሳ መሆኑን ተናገረዋል። በሁኔታው መንግስትን በጥፋተኝነት ፈርጀው፣ ሃገራቸው ሰላም እንድትሆን እንደሚፈልጉ ነግረውናል። ሰላም መፈለጋቸው ከልባቸው ከሆነ መልካም ነው። ይሁን እንጂ መደብሮቻቸውን የከፈቱ ነጋዴዎችን አስመልክተው ሲናገሩ፣ አንዳንድ ፈርተው ሱቃቸውን የከፈቱ አሉፖሊስ ሲያስፈራራ ነበር ብለዋል።

በአማራም ይሁን ከቀናት በፊት በአምቦ፣ ወሊሶና አካባቢው፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ መርካቶ የተሞከረው አድማ ውስጥ የተሳተፉ አብዛኞቹ ነጋዴዎች አድማ ጠሪዎቹን ፈርተው መሆኑ ነው የሚታወቀው። ብዙዎቹ ሱቃቸውን ያለመዝጋት ፍላጎት ነበራቸው። አድማ እንዲካሄድ የማድረግ ተልዕኮ የተቀበሉ ግለሰቦች፣ ድምጽ አልቦ መሳሪያ ታጥቀው መደብራቸውን የሚከፍቱ ነጋዴዎችን ያስፈራሩ እንደነበረ የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው ነጋዴ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ታዲያ የመኢአዱ ዋና ጸሃፊ  መደብራቸውን የከፈቱት መንግስትን ፈርተው መሆኑ ነው የታያቸው። አሳዳሚዎቹን ፈርተው የዘጉትስ? መረጃዎች የሚያመለክቱት አብዛኞቹ ነጋዴዎች ሱቃቸውን የዘጉት አድማ እንዲካሄድ የማድረግ ተልዕኮ አስፈፃሚዎችን ፈርተው ነው። ይህ እውነታ፣ ቪኦኤ የመኢአድ ዋና ጸሃፊን ጠቅሶ ያስተላለፈው መረጃ  ፖለቲካዊ ቅኝት  ያለው መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

ከላይ የተገለጹት እውነታዎች በተለይ በአማራ ክልል ነጋዴውን የህብረተሰብ ክፍል በመጠቀም ሊቀሰቀስ የተሞከረው አድማ ከሃገር ውስጥ ተቃውሞ ወይም ቅሬታ የመነጨ አለመሆኑን ያመለክታሉ። ከዚህ ይልቅ ከውጭ የመጣ ወኪል አስፈፃሚ ያለው አድማ ነው ነው።

በቅድሚያ ነሃሴ 1፣ 2009 ዓ/ም በባህርዳር የተሞከረው አድማ በንግድ ተቋማትና በከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ይሁን እንጂ የአድማው ዓላማ ተብሎ የተነገረው የባለፈውን አመት ነሃሴ እንቅስቃሴ የመዘከር ጉዳይ፣ ከነጋዴው ጋር በተናጥል የሚያያዝበት አንዳችም ነገር የለም። የባህርዳር ህዝብም ሆነ ነጋዴው ስለአድማው የሰማው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኤርትራ መንግስት የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ እየተሰጣቸው በሚሰሩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ነው። የአድማው ዓላማ በነጋዴውም በባህርዳር ህዝብም ስምምነት የተያዘ አይደለም።

ይህ አድማው በዋናነት የኤርትራ የትርምስ ባለሟል በሆነው ግንቦት 7 የተባለ ቡድን የተጠነሰሰ መሆኑን ያመለክታል። እርግጥ ይህን በኤርትራ ባለሟሎች የተጠነሰሰ አጀንዳ ባህርዳር ተሸሽገው የሚያስፈፅሙና የሚያንገራግሩትን ደግሞ የሚያስፈራሩ ቪኦኤ ያነጋገራቸው እሁድ ሌሊት የፈነዳውን ቦምብ ዓላማ የነገሩን ሰውዬ አይነት ሰዎች መኖራቸው አይካድም።

የኤርትራ የትርምስ ባለሟሎች ይህን የአድማ አጀንዳ የመረጡት ሌላ አጀንዳ ስላጡ ነው። ቀሽም አጀንዳ መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። ነጋዴውን ከአማካይ እለታዊ ገቢ ግምት ቅሬታ ጋር አያይዘው አድማ ሊቀሰቅሱ ሞክረው ይህ ሁሉንም ነጋዴ  ለአድማ ማነሳሳት አልችል ስላለ በግብታዊነት የተያዘ ልክስክስ አጀንዳ ነው። የግብር ቅሬታው የሚመለከተው የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን ብቻ ነው። ከእነዚህ ውስጥም በእለታዊ ገቢ ትመና ላይ ቅሬታ ያነሱት ከግማሽ በታች ናቸው። ከእነዚህም መሃከል የአብዛኞቹ ቅሬታ ምንጭ የግንዛቤ እጥረት ነው። እናም ብዙዎቹ ግንዛቤ ሲኖራቸው ግብራቸውን ከፍለዋል። በሌላ በኩል የተጋነነ የገቢ ግምት የተደረገባቸው ደግሞ ማጣራት ተደርጎ ተስተካክሎላቸዋል። እናም የነቃ የነጋዴ ማህበረሰብ ባለበት ባህርዳር፣ የእለታዊ ገቢ ግምቱን ለአድማ መቀስቀሻነት መጠቀም አይቻልም። ዝክረ ነሃሴ 2008 ወደሚለው አጀንዳ የተሄደው ለዚህ ነው።

እርግጥ ቪኦኤና መኢአድ የምስራቅ ጎጃም ወረዳዎችን እየጠቀሱ ከገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ቅሬታ አድማ የመቱ ነጋዴዎች መኖራቸውን ነግረውናል። ይህን ለማመን ያስቸግራል። ምክንያቱም ከላይ እንደጠቀስኩት አብዛኛው ነጋዴ የእለት ገቢ ግምቱ እንደተነገረ በመደናገጥ ቅሬታ የተፈጠረበት፣ ምናልባትም ወደአድማ የመሄድ አዝማሚያ ያሳየው በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ በማጣት ነበር።

ይህም በዋናነት እለታዊ የገቢ ግምትን መነሻ ያደረገውን አመታዊ ገቢ እንደ ተከፋይ ግብር ከመውሰድ የመነጨ ነው። የሚከፍሉት ግብር ከባለሞያ እንደተነገራቸው ከሚያነሱትም መሃከል፣ አብዛኞቹ ግብር የሚከፍሉበትን ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢ 10 በመቶ (90 በመቶ እንደወጪ ተይዞ) ከግብር በፊት ያለን ገቢ (Income Before Income Tax) እንደ የግብር ተመን የወሰዱ ናቸው። አሁን አብዛኛው ነጋዴ በአዲስ አበባም በኦሮሚያ  በቂ ግንዛቤ በማግኘቱ ግብሩን በሰላም እየከፈለ ነው። በአዲስ አበባ 90 በመቶ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ከፍለዋል።

ያለአግባብ የእለት ገቢ የተተመነባቸውም ባቀረቡት ቅሬታ መነሻነት የግምት ማጣሪያ ተካሂዶ ተስተካክሎላቸዋል። አሁን እለታዊ የገቢ ግምት የቅሬታ አጀንዳ መሆኑ አብቅቷል። መኢአድ በጠቀሳቸው ወረዳዎች ይህ የገቢ ግምትና የግብር ግንዛቤ ካልተፈጠረ ሁኔታው  እጅግ አስገራሚ ነው። አለበለዚያ ነገሩ ሁሉ ውዥንብር ለመፍጠር ጥቂት እውነታን ያለወጉ ጠምዝዞ በማጋነን ውዥንብር ለመፍጠር የተደረገ ነው።

ያም ሆነ ይህ መኢአድ ለቪኦኤ የነገረው የምስራቅ ጎጃም ወረዳዎች ውስጥ የተቀሰቀሰው አድማ የገቢ ግብር ግምቱን መነሻ ያደረገ ከሆነ ጉዳዩ ከግንዛባ ጋር የተገናኘ በመሆኑ በቀላሉ የፈታል። ዘላቂ ሁከት የመሆን ተስፋ የለውም።

እንግዲህ የኤርትራ መንግስት የትርምስ ባለሟሎችና ሃገር ውስጥ ያሉ ጉዳይ አስፈፃሚዎቻቸው ሊቀሰቅሱ የሚፈልጉትን ሁከት መነሻ በማደረግ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት አልነበረበትም ሲሉ ተደምጠዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ አዋጁ በተነሳበት እለት ለምክር ቤቱ የአስር ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ‘አዋጁ ከተነሳ ሁከት እንቀሰቅሳለን’ የሚሉ ቡድኖች ስላሉ አዋጁ መነሳቱ ስጋት ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት አዘል ጥያቄ ያነሱ የምክር ቤቱ አባላት እንደነበሩ ይታወሳል።

በመሰረቱ የአስቸካይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ በጊዜ የተገደበ ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊራዘም የሚችል መሆኑን ቢገልጽም ለስድስት ወር ብቻ እንደሚታወጀ ነው የሚደነግገው። የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የሚታወጀው፣ ሁኔታዎችን በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደረስና አዋጁ ባይታወጅ ሊፈጠር የሚችል አውዳሚ ምናልባትም በቀላሉ የማይቀለበስ ስጋት መጋረጡ በተጨባጭ ሲገመት ብቻ ነው።

አዋጁ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የሚጥለው ገደብ፣ የሚነጻጸረው አዋጁ ባይታወጅ ሊመጣ ከሚችለው አጠቃላይ የሰላምና መረጋጋት መደፍረስና ውድመት ጋር ነው። ሁኔታዎችን በተለመደው የህግ ማስከበር አሰራር መቆጣጣር የሚቻልበት እድል ሲኖር፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አስፈላጊነቱ ስለሚያከትም አዋጁ ይነሳል። አዋጁ ከዚህ በላይ እንዲዘልቅ ማድረግ ከጥቅሙ ይልቅ አፋኝነቱ ይጎላል። የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ህግና ስርአትን ማስከበር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ለመገንባትና አወቃቀር ለመዘርጋት የሚያስችል ፋታ መግዣ ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ያለውን ሁኔታ ከዚህ አኳያ ስንመለከተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ተገቢ ነው። እርግጥ ነው ሁከት የመፍጠር ዝንባሌ ያላቸውና ለዚህ ዓላማ ተደራጀተው የተዘጋጁ ቡድኖች ሊኖሩ ይችላሉ። የኤርትራ መንግስትና በስሩ የሰበሰባቸው ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች መኖራቸው በራሱ ሁሌም የሰላም ስጋት መኖሩን ያመለክታል።

ሰሞኑን በአማራ ክልል የተመለከትነው ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ይህ ብቻ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ በቂ ምክንያት አይደለም። ዋናው ጥያቄ ይህን የሁከት ፍላጎት፣ እቅድና ሙከራ በመደበኛ ህግ መቆጣጣር ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚለው ነው።

አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በመደበኛ ህግ የማስከበር ስርአት የሰላም መደፈረስ ስጋቶችን መቆጣጠር የሚያስችል ነው። እናም የኤርትራ ባለሟሎችና ሃገር ውስጥ የሸመቁ አስፈጻሚዎቻቻው ሁከት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ ተብሎ ሃገሪቱ ወይም የተወሰኑ አካባቢዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንድትዘልቁ አይደረግም።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስር ወር የአፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ በዚሀ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አሁን የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ ስራዎች በየደረጃው ካሉ የመስተዳድር አካላት አቅም በላይ ባለመሆናቸው በመደበኛ ህግ ማስከበር ይቻላል ብለዋል።

አዋጁ እንዲታወጅ መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ተደርጓል ያሉት አቶ ሲራጅ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የቀሩ አነስተኛ ስራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር እንደሚቻል መረጋገጡንም ገልጸዋል። በፌዴራልና በክልል የፀጥታ ኃይሎች መካከል ያለው የቅንጅት፣ የመዋቅርና አስተዳደራዊ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። እናም የኤርትራ ባለሟሎች አሉ ተብሎ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ዘላለም አንኖርም። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ግን መቼም ሊታወጅ ይችላል።