ethiopian news

Artcles

የወጣቶች ተጠቃሚነት

By Admin

August 03, 2017

የወጣቶች ተጠቃሚነት

                                                     ታዬ ከበደ

መንግስት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። ወጣቶች በመላ ሀገሪቱ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር ራሳቸውን ጠቅመው በሀገሪቱ እድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ እያደረገ ነው። በዚህ ረገድ በቅርቡ ብሔራዊ የሥራ ፈጠራና የምግብ ዋስትና ምክር ቤት ባለፈው በጀት ዓመት ለአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ማንሳት ይቻላል።

ይህም የአገራችን መንግስት ወጣቶች ስራ ፈጣሪ በመሆን ራሳቸውን ጠቅመው የአገራቸውን ልማት እንዲደግፉ በማድረግ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያለውን ፍላጎት የሚያመላክት ነው። በዚህም ባለፈው የበጀት ዓመት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዩችንና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ ሲከፍቱ ከወጣቶች አኳያ ያደረጉትን ንግግር ገቢራዊ እያደረገ መሆኑን የሚያሳይ ነው።  

በወቅቱ እርሳቸው “…የሀገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት ይሰጠዋል” ብለው መናገራቸውን እናስታውሳለን።

ይህ የመንግስት አቋምም ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት ዕድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መግለፃቸው ይታወሳል።

ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።

እርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። አንደኛው በርካታ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት ይፈጠርና ይህ ስራ አጥ ኃይልም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ለሁከትና ብጥብጥ በር የሚከፍት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀገራት ከወጣቱ ማግኘት የሚገባቸውን የልማት ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችሉም። መንግስት ይህን ሁኔታ ስለሚገነዘብ ተባሩን ከዚሁ አኳያ እየተወጣ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወጣቱን አቅም በፈቀደ መልኩ አደራጅቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ይመስለኛል። ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራት ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል።

ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው አገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህን አጠቃላይ እውነታ በመገንዘብ መንግስት ለወጣቱ ተጠቃሚነት ተግቶ እየሰራ ነው።

ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት።

ወጣቱ ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል። በአጭሩ ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል።

ወጣቱ ስራ ክቡር መሆኑን በማወቅ ለየትኛውም ስራ ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል። በዚህም ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን አገሩንና መንግስቱን ሊጠቅም ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማዘጋጀት ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል።

ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው።

እናም አንድነት ኃይል በመሆኑ፤ በቅድሚያ ተደራጅቶ አዋጪ ስራን መምረጥ፣ የተገኘን ባጀት በስራ ላይ ብቻ ማዋል፣ እንደ አንድ ሆኖ ማሰብ፣ በተመረጠው ስራ ላይ በእኔነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዲሁም ከተጀመረው ስራ የሚገኝ ትሩፋትን በቁጠባና አግባብ በሆነ መንገድ ብቻ መጠቀም ከወጣቱ የሚጠበቁ ተግባሮች ናቸው። ስለሆነም ይህ አገር ተረካቢ ትውልድ በመንግስት በኩል የተዘጋጀለትን ስራ አጥነትን የመቅረፍ ተግባር መጠቀም አለበት።

ትናንት አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው።

 

በምሳሌነትም ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። እናም ወጣቱ በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል።

 

እዚህ ሀገር ውስጥ ለማደግ ትልቁ ጉዳይ ስራን አክብሮ መንቀሳቀስ ነው። ይህ ስራን የማክበር ተግባር ዛሬም የሁን ነገ እውን ሊሆን ይገባል። ስራን ማክበር ራስን ማክበር ነው። ቤተሰብን መጥቀም ነው። አገር ያለመችውን የህዳሴ ጉዞ እውን ማድረግ ነው። ስለሆነም የወጣቱ ተጠቃሚነት ከዚህ የስራ ክቡርነት ባህሪ አኳያ መቃኘት ይኖርበታል።