የዓለም የስራ ድርጅት /አይ ኤል ኦ/ በኢትዮጵያ ህግ ወጥ ስደትን ለመከላከል እና ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲኖር የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚደግፍ የአራት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ድርጅቱ ከብሪታንያ የልማት ድርጅት ባገኘው ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ፓወንድ በላይ ገንዘብ ፕሮጀክቱን አንደሚፈፅም አስታውቋል።
ፕሮጀክቱ ከኢፌዴሪ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንዲቻል የሚያግዝ ነው ተብሏል።
እንደዚሁም በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዝ ዜጎች ተገቢ ስልጠና እንዲያገኙ የተጀመረውን ስራ ይደግፋል።
በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገራት የስራ ስምሪት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ ፕሮጀክቱ ዛሬ ይፋ ሲሆን እንደተናገሩት፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲጀመር ለማድረግ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በማጠናቅቅ ላይ ይገኛል።
በስላባት ማናየ