የዘላቂ ሰላማችን ዋስትናና የህዝብ ተጠቃሚነትን
ያረጋገጥንበት አዋጅ
ዮናስ
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰሞኑ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ወራት በሥራ ላይ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ወስኗል። ምክር ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የ10 ወራት አፈፃጸሙን በመገምገም መሆኑም ተገልጿል። በመሆኑም ለአዋጁ መደንገግ መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች መቀልበሳቸውን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች አንዳንድ ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን የገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት፤ ከሁሉም በላይ ለአዋጁ ተልዕኮ መሳካት ዓይነተኛ ሚና የተጫወተው ህዝቡ መሆኑን አስምሮበት አልፏል። በቀጣይም የሰላም ባለቤትነት ሚናውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉንም ይፋ አድርጓል ።
አዋጁ የተደነገገበት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝብ ያነሳቸው የነበሩትን ህጋዊና ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጽንፈኛ ኃይሎች የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ ወደ ነውጥና ግርግር በመቀየር ሲያካሂዱት የነበረው አፍራሽ እንቅስቃሴ እጅግ አደገኛና በመደበኛ የጸጥታ ማስከበር ሥራ መግታትና መቆጣጠር አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደነበር ይታወሳል። ከአዋጁ በፊት ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ለመመለስ የሚሳቀቁበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ፍጹም የተገፈፉበት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚታወቁበት የመከባበርና የመቻቻል ዕሴት በጸረ ሰላም ሃይሎች ህገወጥ ድርጊት የመሸርሸር ዝንባሌ የታየበት የነበረ መሆኑና ሁኔታው በዚያው ቢቀጥል ኖሮ በአንዳንድ አገሮች የታየው ዕልቂት በአገራችን ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና ያልነበረን መሆኑም ይታወሳል። በአገሪቱ ህገ መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው ይኼ አዋጅ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑ የተለያዩ ክስተቶችም ስለመኖራቸው በመንግስት በኩል በስፋት ተብራርቶ የወጣ መሆኑም በተመሳሳይ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ክስተቶችም የሚጠቃለሉት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና ሃገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥልና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማያስችል መሆኑ ላይ ነው ፡፡
ሰላም እጅግ መሠረታዊ ከሚባሉ፣ ለሰው ልጆች እና ለሃገር ደህንነት ከሚያስፈልጉ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ነው ። ሰላም ከሌለ ልማትና ዕድገት አለመኖራቸው አያከራክርም፡፡ በህይወት የመኖርና ከአካላዊ ደኅንነት የተያያዙ ይልቁንም የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸው ሊያገኙ የሚገባቸውን እና ማንም ከልካይና ነሺ የማይሆንባቸው መብቶች ሁሉ የሚደፈጠጡ መሆኑም አያጠያይቅም፡፡ በዚሁ አግባብ ሃገራችን ባለፈው አመት ላይ ገጥሟት የነበረው የሰላም መደፍረስ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በዚሁ አግባብ የነበረ መሆኑ ታምኖበት አዋጁ በየጊዘው እየተሻሻለ ለ10 ወራት ቆይታ አድርጓል።
ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደሞከርነው፤ በተለያዩ ሥፍራዎች በደረሱ የሕይወት መጥፋቶች፣ የአካል ጉዳቶችና መጠነ ሰፊ የአገር ሀብት ውድመቶች ምክንያት አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ሥጋት ውስጥ መውደቋን መነሻ በማድረግ ታውጆ የነበረው አዋጅ አሁን ተነስቷል።
ከአዋጁ አስቀድሞ በተቀሰቀሰው ግጭት እና ነውጥ ዋነኞቹ ተጎጂዎች ወጣቶች ቢሆኑም፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጉዳቱ ተጋላጭ የነበሩ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ከዜጎች መሞት፣ የአካል ጉዳትና የሥነ ልቦና ስብራት በተጨማሪ፣ በሃገር ሀብት ላይ የደረሰው ውድመት በርካቶችን ለሥራ አጥነት ማጋለጡም በተመሳሳይ ። በሃገራቸው ሠርተው ለመለወጥ በከፍተኛ ፍላጎት ሀብታቸውን ያፈሰሱ ዜጎች ንብረቶቻቸው ወድመው ለተስፋ መቁረጥ መዳረጋቸው በአደባባይ የሆነ እውነት ነው።
የሃገሪቱን ሰላምና ደኅንነት በመተማመን ባህር አቋርጠው የመጡ የውጭ ባለሀብቶች መደንገጣቸውን በይፋ ለአለም ተናግረው የነበረ መሆኑም አይዘነጋም፡፡
ሰላምና የህግ የበላይነት ሲኖሩ ለጠብ፣ ለጭቅጭቅ ብሎም ለግጭት የሚዳርጉ ጉዳዮች በሰላማዊ ውይይትና ምክክር መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግሥት የያዛቸው መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲከበሩ የህግ የበላይነት መረጋገጡ አያጠያይቅም፡፡ ፍትህ መስፈኑና እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት መኖሩም በተመሳሳይ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዴሞክራሲ በተግባር ይታያል፡፡ ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ይለመዳል፡፡ ከአሉባልታ፣ ከሐሜትና ከጥላቻ የፀዳ፤ ልዩነትን ያከበረና የአስተሳሰብ ደረጃው የዳበረ ማኅበረሰብ፤ ምክንያታዊ ትውልድ ይፈጠራል፡፡
ኃይልና አፍራሽ ድርጊቶች የኋላቀርነት ማሳያ ሆነው እንዲቀሩ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነኝ የሚል መንግስት እንዲህ አይነት ነውጥ በገጠመው ጊዜ ተረጋግቶ መልስ መስጠት የሚያስችለውን የጸጥታ እድል መፍጠር ቀዳሚ ተግባሩና ግዴታው ነው፡፡ ስለሆነም አዋጁን በጥርጣሬ ሲመለከቱና ሌላ ስም ሲሰጡት የነበሩ ሃይሎች አሁን አዋጁ ሌላ አጀንዳ ስላለመያዙ መልስ ያገኙ ይመስላል።
ለ10 ወራት የቆየውና አሁን የተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሃገራችን የተያያዘችው የልማትና የሰላም አቅጣጫ እንዳይደናቀፍ ማድረጉ አሁን በተግባር ተረጋግጧል። ለስኬቱ ደግሞ የሰላም ባለቤት የሆነው ህዝብ ንቁ ተሳትፎና የባለቤትነት ሚና ከፍተኛውን ድርሻ እንደወሰደም ተገልጿል፤ በተግባር የታየውና የሆነውም ይኸው ነው። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ10 ወራት ቆይታው የአንዲት ሃገር ሰላም ለዘለቄታው የሚረጋገጠው በሠራዊት ቁጥር ብዛት ሳይሆን የሰላሙ ባለቤትና ተጠቃሚ በሆነው በራሱ በህዝቡ መሆኑንም አጠይቆልናል።
አዋጁ የተነሳው በህዝቡ ተሳትፎና ባለቤትነት በሃገራችን አሁን የተረጋገጠው ሰላም ህዝብ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የልማት፣ የተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር አጀንዳዎቹን ለማስቀጠል ምቹ ዕድል መፍጠሩ ስለተረጋገጠ እንጂ፤ ድብቅ የተባለለትን አጀንዳ ስለጨረሰ አይደለም። በዚህ አዋጅ የተረጋገጠው ሰላም ደግሞ ዝም ብሎ ሰላም ሳይሆን መንግሥት ከህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እያካሄደው ያለውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስገድድ ነው ።
አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሳይታወክ ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማትም ያለአንዳች ስጋት ስራቸውን ማከናወን ችለዋል። በሁከትና ብጥብጡ የተሳተፉ አካላት በፈጸሙት የወንጀል ክብደት ልክ በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ መቻሉን የገለጸው የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት በርካታ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠር እንደቻለ አመልክቷል። በአመጽ ተግባር ከተሳተፉት እጅግ የሚበዙት የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የተደረገ ሲሆን ይህም መንግሥት ለህዝብ ያለውን ተቆርቋሪነትና ወገንተኝነት ያረጋገጠበት ተግባር ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው።