ethiopian news

Artcles

የዛለ ስትራቴጂ የተመረኮዘ ሰነድ – H. RES. 128

By Admin

August 07, 2017

የዛለ ስትራቴጂ የተመረኮዘ ሰነድ – H. RES. 128

ክፍል ሁለት

ኢብሳ ነመራ

በዚሁ ርዕስ በቀረበ ክፍል አንድ ጽሁፍ የአሜሪካ ኮንግሬስ አባል የሆኑት ክሪስ ስሚዝ የተባሉ ግለሰብ በኢትዮጵያ ላይ ያዘጋጁትን H. RES. 128 የተሰኘ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሰነድን መነሻ በማርደግ፣ ሰነዱ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በሚፈልጉና ከኤርትራ መንግስት ጋር በሚሰሩ ቡድኖች እገዛ ጭምር የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁሜ የዚህን አስረጂዎች በቀጣይ ጽሁፍ እንደማነሳ አመልክቼ ነበር የተለያየነው። ቀጣዩ ጽሁፍ እነሆ፤

ከሰነዱ ላይ ይህን የሚያሳዩ ጥቂት ጉዳዮችን እንመልከት። ክሪስ ስሚዝ ሰነዱን ለመቸክቸክ ያነሳሳቸውን ሁኔታ በገለጹበት መግቢያው ላይ በ1997 ዓ/ም የተካሄደው ምርጫ ሁከት እንደገጠመውና ተጽእኖም እንደተደረገበት፣ በሺህ የሚቆጠሩ የተቃዋሚ አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ የሲቪክ ማህበራት አባላት የታሰሩበት መሆኑን ያስታውሳል።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የምርጫ 97 ሂደት ፍጹም ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሃዊ ነበር። ከምርጫው አስቀድሞ የሂደቱ ነጻ፣ ፍትሃዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ላይ ጥያቄ ያነሳ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የምርጫ ታዛቢ አልነበረም። የምርጫው ውጤትም ከዚያ ቀደም ከተካሄዱ ሁለት ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ ተቃዋሚዎች ከፍተኛ መቀመጫ ያገኙበት ነበር። የቀድሞው ቅንጅት በተለይ በአማራ ክልልና በአንዳንድ የሃገሪቱ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠር መቀመጫዎችን አሸንፎ ነበር። አዲስ አበባን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር የሚያስችለው ድምጽ አግኝቶ ነበር።

ይሁን እንጂ የቀድሞው ቅንጅት አመራሮች ቀድሞውኑም ሃገሪቱን መምራት የሚያስችላቸው ድምጽ ካላገኙ ምርጫው ተጭበርብሯል  በሚል ወሬ የከተማ ደጋፊዎቻቻውን አነሳስተው በቀለም አብዮት ስልጣን በሃይል ለመውሰድ አስበው ስለነበረ ይምርጫውን ውጤት አንቀበልም አሉ። አንዳንድ የውጭ ሲቪክ ማህበራትም ቅንጅት ሊያካሂድ ላሰበው የቀለም አብዮት የመንግስት ለውጥ የታክቲክ ምክር ድጋፍ ያደርጉ እንደነበረ በተጨባጭ ተረጋግጧል። ምርጫውን አስመልክተው ባወጧቸው የታዛቢነት ሪፖርቶች ውጤቱን ተዓማኒነት በማሳጣት ህዝብን ለማነሳሳት መሞከራቸውም ጸሃይ የሞቀው እውነት ነው። የቀድሞው ቅንጅት ሌሎች ተቃዋሚዎች ባሸነፉበትና ባልተወዳደረባቸው አካባቢዎች ጭምር ህዝብ የሰጠኝ ድምጽ ተሰርቋል ብሎ ወደሁከት መግባቱ ይታወቃል።

በመሰረቱ ዋነኛው የሁከት ቀስቃሽ የነበረው የቀድሞው ቅንጅት በአፈጣጠሩም የፌደራል መንግስቱን ስልጣን ለመረከብ የሚያስችል የህዝብ ድምጽ ሊያገኝ የሚችል ፓርቲ አልነበረም። ምክንያቱም ፓርቲው አሃዳዊ ስርአት የመመስረት ፖሊሲ ስለነበረው፣ በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቀባይነት አልነበረውም። የቀድሞ ቅንጅት ደጋፊዎች በአማራ ክልል የተገደቡ ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባን ጨምሮ በጥቂት የሃገሪቱ ትልልቅ ከተማዎችም ደጋፊዎች እንደነበሩት አይካድም።

ከዚህ ውጭ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ደጋፊ አልነበረውም። በኦሮሚያ፤ ትግራይ፤ አፋር፤ ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ ኢትዮ ሶማሌ፤ ጋምቤላ፤ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፤ ሃራሪ ክልሎች የቀድሞው ቅንጅት ደጋፊዎችም መራጮችም አልነበሩትም። በተጨባጭም የታየው ይህ ነው። በኦሮሚያና በደቡብ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ደጋፊ የነበረውና የኢህአዴግ ተፎካካሪ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራቶች ሃይሎች ህብረት ወይም ህብረት ነበር። የምርጫው ወጤትም ይህን አሳይቷል። ህብረት በሁለቱ ክልሎች ከገዢው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ መቀመጫ አግኝቷል። ቅንጅት ህብረት ባሸነፈባቸው የምርጫ ክልሎች ጭምር ኢህአዴግ አጭበርብሮኛል ሲል እንደነበረ ይታወሳል።

ይህ ሁኔታ ድርጅቱ ቀድሞውኑም ስልጣን የመመንተፍ እንጂ በህዝብ ድምጽ የተሰጠውን ያህል የመቀበል ዓላማ እንዳልነበረው ያመለክታል። ሁከቱን ያስነሳውም ለዚህ ነበር። ሁከት ያነሳሳውና በመጨረሻም የሁከት ክተት ያወጀው ደግሞ በድብቅ ሳይሆን ራሳቸውን ተቃዋሚ ፕሬስ ብለው በሚጠሩ በነጻ ፕሬስ ሽፋን በሚንቀሳቀሱ ጋዜጦች ነበር። ጋዜጦቹ ያወጁትን የሁከት ጥሪ አሁንም ከቤተመጻህፍት ክምችት አውጥቶ መመልከት ይቻላል። በዚህ ሁከት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዋህ ኢትዮጵያውያን ህይወት ጠፍቷል፤ የጸጥታ አስከባሪ ሃይል አባላትም ተገድለዋል። በሚሊየኖች ብር የሚገመት የግለሰቦች፣ የህዝብና የመንግስት ንብረት ወድሟል።

ይህ ምርጫውን ተከትሎ ቅንጅት የገባበት አካሄድ ዴሞክራሲያዊ አልነበረም። የህግ የበላይነትንም የሚጻረር ነበር። መንግስት ይህን ሁከት በመቀልበስ የህግ የበላይነትን የማስከበር ህገመንግስታዊ ግዴታ አለበት። በዚህ መሰረት አቃቤ ህግ  ሁከቱን በመጠንሰስ፣ በመምራትና በመፈጸም ወንጀል የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውሎ በይፋ የፍርድ ሂደት ጉዳያቸው እንዲታይ አድርጓል። የፍርድ ሂደቱ በእንግሊዘኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋ እየተተረጎመ የውጭ ታዛቢዎች በተገኙበት ነበር የተካሄደው። ክሪስ ሰሚዝ ይህን ጉዳይ ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን በተመለከተ የቸከቸኩት ሰነድ ላይ የሰዎችን መታሰር ከማንሳት ያለፈ፣ ስለሁከቱ አነሳስና ስለፍርድ ሂደቱ አንዲትም ቃል አላሰፈሩም።

የክሪስ ስሚዝ ሰነድ በመቀጠል ወደምርጫ 2002 እና 2007 ይሸጋገራል። ሰነዱ ኢህአዴግ 99 ነጥብ 6 በመቶ የምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፌበታለሁ ያለው የ2002 ምርጫ እንዲሁም 546 መቀመጫዎችን አሸንፌበታለሁ ያለው (አንዷን መቀመጫ ለማን ሰጥተው እንደሆነ አይታወቅም) የ2007 ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ አልነበረም፤ የኢህአዴግን ብቸኛ ገዢነት ያረጋገጠ ነው ይላል።

በቅድሚያ የአንድ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ መሆን የሚለካው በውጤቱ ሳይሆን በምርጫው ሂደት ነው። ክሪስ ስሚዝ ይህን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይሁን እንጂ በ2002 እና 2007 የተካሄዱት ምርጫዎች ሂደት ነጻና ፍትሃዊ አለመሆኑን የሚያሳይ አንድም አስረጂ አልጠቀሱም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው ምርጫው እስኪጠናቀቅ የነበረውን ሂደት በተመለከተ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሂደቱ እንከን የለሽ መሆኑን መስክረው ነበር። ሂደቱ ችግር አለበት ያለ የምርጫ ታዛቢም አልነበረም።

ሁሉም የምርጫ ታዛቢዎች የሂደቱን ነጻና ፍትሃዊነት አረጋግጠው ምስክርነት ሰጥተዋል። የምርጫ ሂደት ነጻና ፍትሃዊ ከሆነ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ትክክልና ተገቢ ነው። ታዲያ፣ ክሪስ ስሚዝ በ2002 እና 2007 የተካሄደው ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ አለነበረም ያስባላቸው ምን ይሆን? መልሱ ቀላል ነው። አሜሪካ የተጠጉ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ቡድኖች የነገሯቸውን እንደወረደ ስለቸከቸኩት ነው፤ በቃ።

ክሪስ ስሚዝ ያዘጋጁት የህግ ሰነድ ረቂቅ ነው፤ የፖለቲካ ፓርቲ መግለጫ አይደለም። ይሁን እንጂ የሰነዱ አገላለጽ  የህግ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው። ኢህአዴግ በ2002ም ይሁን በ2007 ምርጫ ለሁሉም የምክር ቤት መቀመጫዎች አለመወዳደሩ ይታወቃል። ኢህአዴግ የተወዳደረው በኦሮሚያ፤ በአማራ፤ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ለሁሉም መቀመጫዎች፣ በሃራሪና ብድሬደዋ ከተሞች ለተወሰኑ መቀመጫዎች ነበር። በአፋር፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምቤላ ለአንድም መቀመጫ አልተወዳደረም። በሃራሪና በድሬደዋም ለሁለት መቀመጫዎች ብቻ ነው የተወዳደረው። ያልተወዳደረበትን ድምጽ ደግሞ ማግኘት አይችልም።

ስለዚህ ኢህአዴግ 99 ነጥብ 6 ወይም ሁሉንም የምክር ቤቱን መቀመጫዎች ሊያሸንፍ አይችልም፤ አሸንፎም አያውቅም። የህግ ሰነድ ላይ ይህ በትክክል መቀመጥ አለበት። 99 ነጥብ 6 በመቶ፣ ሁሉንም የምክር ቤት መቀመጫ አሸነፈ የሚለው ወሬ፣ የምርጫው ውጤት የጎመዘዛቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎችና አሜሪካ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅትነት መዝግባቸው ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚሰሩ ተቃዋሚ ነን ባዮች የሚያወሩት ፖለቲካዊ አገላለጽ ነው። ይሀ ሁኔታ ክሪስ ስሚዝ ሰነዱን ሲያዘጋጁ ጉዳዩን በቅጡ ለማጥናት እንኳን ሳይጨነቁ ተቃዋሚዎቹ የነገሯቸውን እንደወረደ የቸከቸኩት መሆኑን ያሳያል። ይህን ያደረጉት ምናልባት የሰጧቸው ህጋዊ ጉቦ ልባቸውን ነስቷቸው ይሆን?

የክሪስ ስሚዝ ሰነድ በዚህ አያበቃም። ባለፈው ዓመት በአማራና በኦሮሚያ ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከትና በሁከቱ የጠፋውን የሰው ህይወት ይጠቀሳሉ። ተገፍተናል (marginalized) በሚሉ የኦሮሞና የአማራ ብሄሮች የተቀሰቀሰ እንደሆነ አድርገው ነው ያቀረቡት። ሚ/ር ስሚዝ ሊነገሩን የፈለጉት የኢትዮጰያ መንግስት የአንድ ብሄር የበላይነት የሰፈነበት፣ ሌሎች ብሄሮች የተገፉበት መሆኑን ነው።

በመሰረቱ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት ይህ ሊሆን አይችልም። ክልሎችና ሌሎች የአስተዳደር እርከኖች በብሄር ላይ በመመስረት ነው የተዋቀሩት። ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች ወይም ብሄረሰቦች በየአካባቢያቸው ራሳቸውን በራሳቸው ነው የሚያስተዳድሩት። ኦሮሚያን ትግሬ ወይም አማራ ሊያስተዳደር አይችልም። አማራን ትግሬ ወይም ኦሮሞ በበላይነት ማስተዳደር የሚያስችለው ምንም ክፍተት የለም።

የፌደራል መንግስቱ ከፍተኛው የስልጣን አካል በሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በህዝባቸው ቁጥር ልክ ውክልና አላቸው። በፌደራል ምክር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ውክልና ያለው የኦሮሞ ብሄር ሲሆን ቀጣዩ የአማራ ብሄር ነው። በፌደራል መንግስት አስፈፃሚ ውስጥም ብቃትንና የብሄር ተዋጽኦን መሰረት ያደረገ ሹመት ነው የሚሰጠው።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ ክሪስ ስሚዝ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልል ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት ከመገለል ጋር ማገናኘት ለምን አስፈለጋቸው? መልሱ ቀላል ነው። ክሪስ ሰሚዝ ኢትዮጵያን ብሎም ቀጠናውን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሰው የኤርትራ መንግስት ጉዳይ አስፈጻሚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር የሚያወሩትን የትግሬ የበላይነት አለ የሚል ወሬ እንደወረደ ስለተቀበሉ ነው። እውነታው ምንም አላሳሰባቸውም። ይህ ክሪስ ስሚዝን የግጭት አጋፋሪ ያደርጋቸዋል።

በመሰረቱ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞ ዋና መንስኤ የመልካም አስተዳደር መጓደልና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ነው። እርግጥ ክሪስ ስሚዝ እንደጠቀሱት ተቃውሞው የአንድ ብሄር የበላይነት ያለ በማስመሰል የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ባካሄዱት ቅስቀሳ ወደአውዳሚ ሁከትነት ተቀይሯል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የዘር ማጥራት ባህሪ ያለው እርምጃ እስከመውሰድ የዘለቀ ጸያፍ ድርጊት ተፈጽሟል።

አሜሪካ ተቀምጠው ለክሪሰ ስሚዝ ወሬ የሚያቀብሏቸው ወገኖች ኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜን ጎንደር ዞን የዘር ማጥራት እርምጃ እንዲወሰድ ማስደረጋቸውን ለምን ዘነጉት? የክሪስ ስሚዝ ወሬ አቀባዮች የቀሰቀሱት ሁከት በህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ያስከተለውን መስተጓጎል፤ በግል ባለሃብቶች (በውጭ ባለሃብቶች ጭምር) ኢንቨስትመንቶች ላይ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ፣ በሃይማኖት ተቋማት ላይ ያስከተለውን ውድመት፣ ሰላም ለማስከበር በተሰማሩ የፖሊስና የሚሊሻ አባላት ህይወትና አካል ላይ ያደረሰውን ጉዳትስ ለማን ይሆን የተዉት?

ይህን አሜሪካ የሚገኙ የክሪስ ስሚዝ ወዳጆች የቀሰቀሱትን ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለ፣ ህገመንግስታዊ ሥርአቱን ለአደጋ ያጋለጠ ሁከት በተለመደው ህግን የማስከበር እርምጃ መከላከል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ መንግስት ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አወጀ። በቅድሚያ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ ህገመንግስታዊ መሆኑ መታወቅ አለበት። ክሪስ ስሚዝ ግን እንደችግር ብቻ ነው ያዩት። ይህን መነሻ በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ጠይቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሁኔታዎች ተረጋግተው በተለመደ የህግ ማስከበር አሰራር ሰላምና መረጋገትን መጠበቅ ወደሚቻልበት ደረጃ በመደረሱ ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት ተነስቷል። በመሆኑም በዚህ ላይ ብዙ ማለት አልፈልግም።

ክሪስ ስሚዝ ሌላ ያነሱት ጉዳይ የፀረ ሽብርተኝነት ህጉንና የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጆችን የሚመለከት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስለተባለ ደግሜ ባላነሳው እመርጣለሁ። ይሁን እንጂ ክሪስ ስሚዝ የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጠየም ያዘጋጁት ሰንድ ዋና አጀንዳ ስላደረገው ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በመጠኑ እመለከተዋለሁ።

ክሪስ ስሚዝ አዋጆቹ ይሰረዙ ወይም ይሻሻሉ ሲሉ እንደመጣላቸው ወይም ብር የከፈሏቸው ሰዎች በሉ እንዳሏቸው ነው የቸከቸኩት። በመሰረቱ ኢትዮጵያ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ያወጣችው ግልጽና ደራሽ የሽብር ጥቃተ አደጋ ሰላለባት ነው። ኢትዮጵያ በ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ቡድኖች የሽብር ጥቃት ተፈጽሞባታል። በይፋ የሽብር ጥቃት ኢላማቸው መሆኗን ያወጁትም ቁጥር ቀላል አይደሉም።

ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ እይተስፋፋ የመጣውንና ዓለም አቀፍ ባህሪ ያለውን የሽብር ጥቃት ለመከላከል የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት ስምምነቶች፣ ሃገራት የጸረሽብርተኝነት ህግ እንዲያወጡ ያስገድዳሉ። አዋጁ በእነዚህ መሰረታዊ ምክንያቶች ነው የወጣው። ፈጽሞ ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴን የማፈን ዓላማ የለውም። ይህን ማድረግ የሚያስችል ድንጋጌዎች አለው የሚልም እምነት የለኝም።

የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ ችግር አለበት ከተባለም የሚሻሻለው በአሜሪካ ጥያቄ ሳይሆን፣ ጉዳት ያደርስብናል በሚሉ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላት ብቻ ነው። እርግጥ እስካሁን የትኛው የጸረሽብርተኝነት ህጉ አንቀጽ ችግር አለው እንደሚሉ በግልጽ ባይናገሩም፣ ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም አዋጁን ሲቃወሙት ይሰማል። በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲና በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎቸ በማካሄድ ላይ በሚገኙት ድርድር ህጉን ለማስተካካል ጉዳዩን በአጀንዳነት ይዘውታል። ወጤቱን አብረን እንመለከታለን።

የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምዝገባ አዋጅን በተመለከተ፣ አዋጁ በመሰረቱ የሲቪክ ማህበራትንና በጎ አድራጎት ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የመገደብ ዓላማ የለውም። የአዋጁ ዓላማ ማህበራቱ የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ማጎለበት በሚያስችል፣ ከማህበራቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚጠብቀውን ህዝብ ተጠቃሚነቱን በሚያረጋግጥ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱበትን ስርአት ማበጀት ነው። አዋጁ ሃገር በቀል ሲቪክ ማህበራት በሃገሪቱ ፓለቲካዊ – ዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳዮች ላይ ያለምንም ገደብ መሳተፍ እንደሚችሉ ይደነግጋል። የውጭ ማህበራት ግን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ውስጥ የመሳተፍ መብት ብቻ ነው ያላቸው። ይህ የሆነው  የሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳይ የመንግስት ስልጣን ብቸኛ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ ብቻ በመሆኑ ነው። ዴሞክራሲውን ማሳደግ፣ ሰብአዊ መብትን ማረጋገጥ፣ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን . . . የሚቻለውም በራስ አቅም ብቻ መሆኑ ስለታመነበት ነው።

የውጭ ሲቪክ ማህበራት በገንዘብ የሚደግፋቸውን አካል ወይም መንግስት ጥቅም ከማስጠበቅ ነጻ ሊሆኑ ስለማይችሉ፣ የህዝቡን ዘላቂ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ የዴሞክራሲ ግንባታ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ ወዘተ ተግባራትን ማከናወናቸው ዋስትና የለውም። ዴሞክራሲን በመገንባት ሰበብ በተለያዩ ሃገራት ጥቂቶች በተሳተፉበት የከተማ ሁከት የመንግስት ለውጥ የማድረግ ሙከራዎች የተካሄዱት በውጭ ሲቪክ ማህበራት አማካኝነት መሆኑ ምስጢር መሆኑ ያበቃበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ ማስታወስም ተገቢ ነው። ዴሞክራሲን በማስፋፋትና ሰብአዊ መብትን በማስከበር ሽፋን የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሲቪክ ማህበራት በመሯቸው የቀለም አብዮቶች የተፈጸሙት የመንግስት ለውጦች ሃገራቱን ትርምስ ውስጥ ከማስገባት ያለፈ አንድም ቦታ ላይ ዘላቂ ሰላም አላመጣም።

ከዚህ በተረፈ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያነሱት ጉዳይ፣ አስተዳደራዊ ወጪን የሚገድበውን የአዋጁ ድንጋጌ የሚመለከት ነው። የዚህ ድንጋጌ ዓላማ በጎ አድራጎት ድርጅቶቹ በህዝብ ስም የሚያመጡትን ሃብት ለራሳቸው ተቀራምተው እንዳይጨርሱት መከላከል የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ነው። በርካታ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በድሆች ስቃይ ከለጋሾች ሰብስበው የሚያመጡትን የእርዳታ ገንዘብ ለራሳቸው ተቀራመተው ጥቂት የተንደላቀቁ ቱጃሮችን ያፈሩ መሆናቸውን ማስታወስ ይገባል። ያም ሆነ ይህ፣ ከዚህ አስተዳደራዊ ወጪ ጋር በተያያዘ በትክክል ስራቸውን እንዳይሰሩ እንቅፋት የፈጠረ ሁኔታ ካለም ይህን በውይይት ማስተካካል ይቻላል። ይህ ሂደት የተጀመረ ይመስለኛል። በመሆኑም ከሪስ ስሚዝ የቸከቸኩት ኢትዮጵያን የሚመለከት ረቂቅ የውሳኔ ሰነድ በሃገራቸው የተሸሸጉ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች የነገሯቸው መሰረተ ቢስ ወሬ እንደወረደ የሰፈረበት፣ ከእውነታ የራቀ ነው።

ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጵያ ላይ ያዘጋጁት ሰነድ ተቀባይነት አግኝቶ ይጸድቃል የሚል ግምት የለኝም። ቢጸድቅም ኢትዮጵያ የተያያዘችው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ አይኖርም። አሜሪካና ኢትዮጵያ የሰላምና የልማት አጋረነት ቢኖራቸውም፣ አሜሪካ ብቸኛዋ የኢትዮጵያ አጋር አለመሆኗንም ማስታወስ ተገቢ ነው።

በአጠቃላይ ክሪሰ ስሚዝ ሰነዱን ለማዘጋጀት ድፍረት የሰጣቸው የሃገራቸው መንግስት የሚከተለው በ1970ዎቹ የተነደፈ አዲስ የዓለም አሰላላፍ/New Worled Order የተሰኘ ሃገራትን በተዕእኖ ስር የመጣል ስትራቴጂ ነው። ይህ ስትራቴጂ ያረጀና ያፈጀ በክፍል አንድ ጽሁፍ ላይ እንደተገለጸው በራሷ በአሜሪካም ላይ ጭምር አደጋ ያስከተለ፣ ባለንበት ዘመን አሜሪካን የዓለማችን አደገኛ ሃገር ያሰኘ ነው። አዲስ ብቅ ያሉ የኢኮኖሚ ልዕለ ሃያላን ሃገራት፣ የጋራ ጉዳዮች ላይ በመመሰረት መጠቃቀም ላይ የተመሰረተ አዲስ የዓለም አሰላለፍ ስትራቴጂ ነድፈው ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑም መስተዋል አለበት።

የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት መጠቃቀም ላይ የተመሰረተ የዘመናችን የዓለም አሰላለፍ ስትራቴጂ መሆኑን ልብ ይሏል። ክሪስ ስሚዝ የተመረኮዙት የአሜሪካ የዓለም አሰላለፍ ስትራቴጂ ዝሏል። ክሪስ ስሚዝ ይህን ቢያስተውሉ ተገቢ ይመስለኛል። ያረጀውና የዛለው የአሜሪካ የዓለም አሳለፍ ስትራቴጂ አሜሪካን ከዓለም ከመነጠልና እንደስጋት እንድታይ ከማድረግ ያለፈ የትም የማያደርስ ነው።

ያም ሆነ ይህ ክሪስ ስሚዝ አሁን ኢትዮጵያ ላይ ለቸከቸኩት ሰነድ የቅርብ አነሳሽ ምክንያት የአሜሪካ መንግስት ያለአግባብ ኢትዮጵያን እንዲጫን የሚፈልጉ በአሜሪካ በመንግስታዊ ድርጅትነት የተመዘገቡ የኤርትራ መንግስት ምስራቅ አፍሪካን የማተራመስ ስትዳቴጂ አስፈፃሚዎች በሎቢ ክፍያ ሽፋን ያቀረቡላቸው ህጋዊ ጉቦ ነው። ሰነዱን በተዘዋዋሪ መንገድ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን የማተራመስ ስትራቴጂ አስፈጻሚ ቡድኖች ያዘጋጁት እንደሆነ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ክሪስ ስሚዝም ሆኑ አሜሪካ በሃገራት ሉዓላዊነት ውስጥ ጣልቃ እንድተገባ ህጋዊ ጉቦ እየከፈሉ የጫና የውሳኔ ሰነድ የሚያስጽፉ ቡድኖች፣ አሜሪካ የምትከተለው የዓለም አሰላለፍ ስትራቴጂ የትም የማያደርስ የዛለ መሆኑን ማስታወስ አለባቸው። እናም የዛለ ስትራቴጂ የተመረኮዘው H.RES.128 እዳው ገብስ ነው።