Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ“ዴሞክራሲያውያኑ” ኢ-ዴሞክራሲያዊ ጎዳና

0 315

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ“ዴሞክራሲያውያኑ” ኢ-ዴሞክራሲያዊ ጎዳና

ኢብሳ ነመራ

አሜሪካ አሁን ባለንበት ዘመን የሰው ልጆችን እኩልነት ለመቀበል የቸገራት ሃገር ነች። በአሜሪካ በርካታ ጥቁሮች ቢኖሩም እኩልነታቸውን መቀበል ለነጮቹ ጭንቅ የሆነባቸው መሆኑን በግልጽ የሚያሳዩ አስረጂዎች አሉ። እርግጥ የአሜሪካ ታሪክም ይህን የሚያሳይ ነው። የአሜሪካ መስራች አባት የሚባለውና የአሜሪካን የነጻነት መግለጫ ሰነድ (Declaration of Independence) ያዘጋጀው ቶማስ ጀፈርሰን፣ ይህን ድንቅ የሰውን ልጆች እኩልነትና የሰብአዊ መብት መከበር የሚገልጽ ሰነድ ሲያዘጋጅ በቤቱ እንደእንስሳ በንብረትነት የያዛቸው ጥቁር ባሪያዎች ነበሩት። ስለሰው ልጅ ነጻነት ያን ያህል ሲያስብና ሲጽፍ በቤቱ የነበሩት ጥቁሮች ነጻነት አልታየውም። ወይም በቤቱ የነበሩትን ጥቁር ባሮች ነጻነትና እኩልነት መቀበል ከብዶታል። ነጭ አሜሪካውያን የጥቁሮችን እኩልነት – የመምረጥና የመመረጥ መብት ሞተው ሞተው ከነጻነታቸው ከ2 መቶ ዓመት በኋላ ነው ያከበሩት። ለነገሩ አሜሪካ የሴቶችን እኩልነት በመቀበልም ከበለጸጉ ሃገራት ሁሉ ውራ ሳትሆን አትቀርም።

ነጭ አሜሪካውያን በተለይ የጥቁሮችን የበላይነት የመቀበል ነገር አሁንም ሲከብዳቸው ይታያል። በጥቁሮች ላይ በየወቅቱ የሚፈጸመው ጥቃት፣ ህግ ለማስከበር በተሰለፉ ነጭ የፖሊስ ሰራዊት አባላት ጭምር ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። አሜሪካ አሁንም የሰው ልጅ እኩልነት የሚቀበል ባህል ማዳበር ያልቻለች ሃገር ነች። ሰሞኑን የዘር መድልዎን በመቃወም የተካሄደ ትዕይንት ላይ በአንድ ነጭ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት ልብ በሉ። አንድ የሃያ ዓመት ነጭ ወጣት ለትዕይንት የወጡ ሰዎች ላይ ሆን ብሎ መኪና በመንዳት የአንድ ሰው ህይወት አጥፍቷል። የነጭ የበላይነት (white supremacist) አመለካካት አራማጅ ወሮበሎች መሳሪያ ታጥቀው በአደባባይ ሲሸልሉ ተመልክተናል።

ታዲያ በእነዚሁ የነጭ የበላይነት አመለካካት አራማጆች ድምጽ ለፕሬዝዳንትነት የበቁት ዶናልድ ትራምፕ የነጭ የበላይነት አመለካካት አራማጆችን ድርጊት ማውገዝ ከብዷቸው ነበር። ለውግዘት ብቅ ያሉት ድርጊቱ ከተፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር። እሱንም ተመልሰው አስተባብለዋል። ሁኔታዎች በማባባስ የነጭ የበላይነት አመለካካተ አራማጆችንና የቀለም መድልዎ የሚቃወሙትን እኩል ተጠያቂ አድርገዋል። የ21ኛው ክፍለ ዘመን አሜሪካ ይህን ትመስላለች።

አሜሪካ ሌላ የሚከብዳት ነገር የአመለካከት ልዩነትን መቀበል ነው። አሜሪካ የአመለካከት ልዩነትን የምታከበረው፣ የተለየው አመለካከት የህዝቧን 1 በመቶ ገደማ የሚሆኑትን ባለጸጎች ጥቅም የሚያስጠብቀውን የገበያ አክራሪ ሊበራሊዝም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም እስካልተጋፋ ድረስ ብቻ ነው። ይህን እስካልተጋፋ ደረስ ዜጎቿ ሰማይ የመቧጠጥ መብት አላቸው። አሜሪካ ዓለም በሁለት የርዕዮተ ዓለም ጎራ ተከፍሎ በነበረበት የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን፣ የኮሚኒዝም አመለካካት አራማጆችን አትታገስም ነበር። የዚህ አመለካካት አራማጅ የሆኑ ከአወሮፓ የገቡ ግለሰቦችን፣ ከሃገሯ ታሳድድ እንደነበረ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደአሜሪካ ሄዶ የነበረው ጀርመናዊው ቻርሊ ቻፕሊን ለዚህ አሰረጂነት ይጠቀሳል። ቻርሊ ቻፕሊን የኮምኒዝም አመለካከት አራማጅ ነው በሚል ጥርጣሬ ከአሜሪካ ተባሯል።

የአሜሪካ የተለየ አመለካካትን መታገስ አለመቻል ዓለም አቀፋዊ ነው። በሌሎች ሃገራትም ከገበያ አክራሪ ኒዮ ሊበራሊዝም የተለየ ርእዮተ ዓለም እንዲኖር አትፈቅድም። በሌሎች ሃገራት የሚፈጠሩ የሶሻሊስትና ሌሎች አመለካከቶችን ለማጥፋት እ ኤ አ በ1970ዎቹ አጋማሽ አዲስ የአለም አሰላለፍ ስርአት ስትራቴጂ ማዘጋጀቷ ይታወቃል። ይህም ሶሻሊስታዊና ልማታዊ ዴሞክራሲ አመለካካት በተፈጠረባቸውና መጎልበት በጀመረባቸው ሃገራት፣ በሃይል የስርአት ለውጥ በማምጣት በምትኩ የኒዮሊበራል አመለካካት አሻንጉሊት መንግስት መሰየም ነው።

ይህ የስርአት ለውጥ የሚካሄደው ከአሜሪካ መንግስት ባጀት በሚቆረጥላቸው መንግስታዊ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (Governmental Non Governmental Organaizations/GNGOs) አማካኝነት ነው። እነዚህ በመንግስት የሚመሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በየሃገሩ የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ በሚቀፈቅፏቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን፣ የዴሞክራሲ ተንከባካቢ ነን በሚሉ ሲቪክ ማህበራት አማካኝነት ነው የመንግስት ለውጡን የሚያካሂዱት። ይህ የመንግስት ለውጥ በዘመናችን የቀለም አብዮት የተሰኘ ስያሜ ተሰጥቶታል።

የተለየ የፖሎቲካል ኢኮኖሚ ርእዮተ ዓለም (በተለይ በዘመናቸን ጎልቶ የወጣውን ልማታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት) በሚከተሉ ሃገራት የመንግስት ለውጥ ለማምጣት የሚወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ በመንግስታዊ መንግስታዊ ያልሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን ባይ ድርጅቶች በሚያወጡት የፈጠራ የሰብአዊ መብት ጥሰት ውንጀላ ሪፖርቶች ገጽታቸውን ማበላሸት ነው። የሰብአዊ መብት ተሟጓች ነን ባይ ቡድኖች በአይዞህ ባይነት የስልጣን ተስፋ ሰጥተው ከሚዘውሯቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ጋር በመተባባር ያለማቋረጥ እየተቀባበሉ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን ያወጣሉ።

የምእራባውያን ሚዲያዎች በተለይ ዒላማ በተደረገው ሃገር ላይ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞች (የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራንን የመሳሰሉ) የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚል የተዘጋጀውን ሪፖርት ያራግባሉ። የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት የቀለም አብዮት ዒላማ የተደረገው ሃገር ላይ ጫና የሚያሳድር የውሳኔ ሃሳብ ያዘጋጃሉ። በዚህ አካሄድ በተለይ ምርጫ ቦርድን፣  ተጠሪነታቸው ለሃገሪቱ ፓርላማ የሆኑ የሰብአዊ መብት ተቋማትን የመሳሰሉ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ተቋማትን፣ ፍርድ ቤቶችን እንዲሁም በፓርላማ የጸደቁ የተወሰኑ ህጎችን ተአማኒነት ያሳጣሉ።

የምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤትን የመሳሰሉ ተቋማትን ተአማኒነት ካሳጡ በኋላ፣ በቀጥታ ምርጫን አስታከው በከተማዎች አካባቢ ሁከት ይቀሰቅሳሉ። በምርጫ ማግስት ምርጫ ተጭበርብሯል ብለው ያስወራሉ። ቀድሞውኑ የዴሞክራሲ አራማጅ ነን በሚሉ ሲቪክ ማህበራትና በሚዲያዎቻቸው አማካኝነት የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት በተለየ ከእውቀት ይልቅ በስሜት የሚመሩ ከተሜዎች ዘንድ ተአማኒነት ስለሚያሳጡ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚለው ወሬ እውነት ይመስላል። ምርጫን ያልተቀበለ ወገን ህግ በሚያዘው መሰረት ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ይዞ እንዳይሄድ፣ የፍርድ ቤቶችንም ተአማኒነት በተመሳሳይ ሁኔታ ያረክሱታል።

ከዚህ በኋላ የሚቀረው አማራጭ ሁከት ብቻ ይሆናል፤ በከተማ ሁከት የመንግስት ለውጥ ማምጣት። የቀለም አብዮት ይህ ነው። የቀለም አብዮት አሜሪካ የተለየ አመለካከትን መታገስ የማትችል ከመሆኗ የመነጨ የሃይል የመንግስት ለውጥ ስልት ነው።

ሰሞኑን የቀለም አብዮት እንዲካሄድ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሂደት የጎላ ድርሻ ካለው ምናልባት ለዚሁ ዓላማ ከተቋቋመው የአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) ከተሰኘው መንግስታዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ ላይ የቀለም አብዮት የመጠነሰስ አካሄድን በግልጽ የሚያሳይ አንድ ጉዳይ ሰምተናል። የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ሰሞኑን ባሰራጨው አንድ ፕሮግራም የኢፌዴሪ መንግስት የሾማቸውን አምባሳደሮች መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተአማኒነት ለማሳጣት ሞክሯል። ይህም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት ፕ/ር መረጋ በቃና አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን መነሻ ያደረገ ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጠው የህግ ባለሞያ፣ መንግስት ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ በውጭ ሃገራት አምባሳደር አድርጎ የመሾም መብት ያለው መሆኑን፣ የፕ/ር መርጋ በቃና አምባሳደር ሆኖ መሾምም ምንም ልዩ ነገር እንደሌለው ቢያስረዳም፣ የቪኦኤው ጋዜጠኛ ይህን መቀበል አልፈለገም።  ፕ/ር መርጋ የኢህአዴግ አባል ናቸው፣ ገለልተኛ አልነበሩም፣ እናም ምርጫ ቦርድም ገለለተኛ አይደለም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ብዙ ጥሯል። ጋዜጠኛው ጥያቄውን ሲያቀርብ በጉዳዩ ላይ መልስ የመስጠት ያህል አቋሙን ያንጸባርቅ ነበር። የህግ ባለሞያው የሚሰጠው ምላሽ የሚፈልገውን አላስተላልፍለት ያለው ጋዜጠኛ፣ ምርጫ ቦርድ ገለለተኛ ነው። ፕ/ር መርጋ ደግሞ ገለልተኛ ናቸው ተብለው ነው የቦርዱ ሃላፊ የሆኑት። አሁን አምባሳደር ሆኑ። አምባሳደር የሚሾመው ከመንግስት ወይም ከፓርቲ አባላት ነው። የፕ/ር መርጋ የአምባሳደርነት ሹመት ከህግ አንጻር እንዴት ይሄዳል?” ብሎ ጠይቆ፣ ይህንኑ ሲያብራራ “ከልምድ አንጻር እንደምናውቀው፣ አንድም የፓርቲ አባል ያልሆነ አምባሳደር ሆኖ አያውቅም። የሚል ድምዳሚ አስተያያት ሰጥቷል።

የቪኦኤ ጋዜጠኛ አካሄድ በመሰረታዊነት ከሚያገለግለው መንግስት የአመለካከት ልዩነትን ያለማክበር አቋም የመነጨ ነው። ኢትዮጵያ ከኒዮሊበራሊዝም የተለየ ልማታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የምትከተል ሃገር ነች። የቪኦኤው ጋዜጠኛ፣ ቀጣሪው የአሜሪካ መንግስት ይህን የልማታዊ ዴሞክራሲ ርእዮተ ዓለም ወይም አመለካካት እንደማይታገስ ያውቃል። ቢቻል በዲፕሎማሲ፣ ይህ ካልሆነ በፖሊሲ ኪራይ (ብድርና እርዳታ እንድታገኙ ይህን አቋሟችሁን/ፖሊሲያችሁን ቀይሩ በማለት) ልማታዊ ዴሞክራሲን ሊያስጥል እንደሚሰራ ያውቃል። ይህም ካልሆነ ማዕቀብ በመጣል ጫና ለማሳደር እንደሚሞክር ያውቃል። በመጨረሻ  የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን በሚሉ ድርጅቶችና በበጎ አድራጎት ድርጅትነት መዝግቦ በያዛቸው የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች እንዲሁም በሃገር ውስጥ የህጋዊነት ካባ ለብሰው ባደፈጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማካኝነት በቀለም አብዮት የመንግስት ለውጥ በማምጣት የኒዮሊበራል አሻንጉሊት መንግስት የማምጣት እቅድ ጠረጴዛው ላይ እንዳለም ያውቃል። እናም ፕ/ር መርጋ በቃና አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን መነሻ በማደረግ፣ በሰብሳቢነት ሲመሩት የነበረውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተዓማኒነት በማሳጣት በሩቁም ቢሆን ለቀለም አብዮት አመቺ ሁኔታ ለማደላደል የበኩሉን እየተወጣ ነው፤ ያለውን የወረወረ ንፉግ አይባልም እንዲሉ።

ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው ራሱን ትዝብት ላይ የሚጥል ጉዳይ ነው የመረጠው። በቅድሚያ ጋዜጠኛው አንድም የፓርቲ አባል ያልሆነ አምባሳደር ሆኖ አያውቅም ብሎ የገለጸው አቋሙ ፍፁም ስህተት ነው። የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህ ቀደም የገዢው ፓርቲ አባል ያልሆኑ ህገመንግስታዊ ስርአቱን የተቀበሉና ሃገራቸውን ለማገልገል ፍቃደኛ የሆኑ በርካታ አምባሳደሮችን ሾሟል። አምባሳዶር ዶ/ር ብሩክ ሃይሉ፣ አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ፣ አምባሳደረ ሃንፍሬ አሊሚራ፣ አምባሳዶር ዶ/ር ተቀዳ አለሙ፣ . . . ከበርካታዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። ምናልባት የቪኦኤው ጋዜጠኛ ከእነዚህ የኢህአዴግ አባል ሳይሆኑ ሃገራቸውን በአምባሳደርነት የወከሉ ኢትዮጵያውያን መሃከል የተወሰኑትን የማነጋገር እድል አግኝቶ ይሆናል ብዬም እገምታለሁ። የዘነጋቸው ልቡ የምርጫ ቦርድን ተአማኒነት ማሳጣት ላይ ስለተንጠለጠለ ነው፤ ታማኝ አገልጋይ ጋዜጠኛ ይሏል ይህ ነው።

የፕ/ር መርጋ በቃናን ገለልተኝነት በተመለከተ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምስክርነታቸውን የሰጡበት ጉዳይ ነው። የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት፣ ሰብሳቢው ጭምር የተሰየሙት በምርጫ ህግ አዋጅ 532/1999 መሰረት ነው። ይህ አዋጅ በአንቀጽ 6 የቦርዱ አባላት በሚል ርዕስ ስር በንኡስ አንቀጽ 2 ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሰዎችን ለቦርድ አባልነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከማቅረቡ በፊት፣ በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች እጩ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል በቂ የምክክር መድረክ እንዲኖር ያደርጋል ሲል ይደነግጋል።

ፕ/ር መርጋ በቃናን ጨምሮ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ከመሰየማቸው በፊት በወቅቱ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮችን በአባልነት ይዞ ለነበረው ምክር ቤት ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን እንዲመረምር እድል ተሰጥቷል። የቦርዱ አባላት የተሰየሙት ተቃዋሚዎች ነጻና ገለልተኛ መሆናቸው ላይ አስተያያት ከሰጡ በኋላ ነው። የቪኦኤ ጋዜጠኞች በአቋማቸው ሳይሆን ህገመንግስታዊ ስርአቱን ሊያፈርሱ ይችሉ ይሆናል በሚል ተስፋ የሚደግፏቸው በወቅቱ ህብረት ይባል የነበረው የአሁኑ መድረክ አባላትና አመራሮች የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ ገብሩ ገብረማርያም ሌሎችም፣ የቦርዱ አባላት እጩዎች ከፖለቲካ ፓርቲ ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። እንዲሁም የኦፌኮ መስራች አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ የኢዴፓው መስራችና መሪ አቶ ልደቱ አያሌው ወዘተ በተመሳሳይ ገለልተኝነታቸውን አረጋግጠዋል። በወቅቱ በእጩ የቦርድ አባላቱ ነጻና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ያነሳ አንድም የምክር ቤት አባል አልነበረም።

የቪኦኤ ጋዜጠኛ ከላይ የተጠቀሱትን የኢትዮጵያ መንግስት የአምባሳደር አሿሿምና የምርጫ ቦርድ አሰያየም የሚመለከቱ እውነታዎች ወደ ጎን ገፍቶ ነው የፕ/ር መርጋ በቃናን ገለለተኝነት ጥያቄ ላይ በመጣል ምርጫ ቦርዱን፣ እስካሁን የመራቸውንና ለወደፊትም የሚመራቸውን ምርጫዎች ተአማኒነት ሊያሳጣ የሞከረው። ይህ የጋዜጠኛውን ገለልተኛ አለመሆን ያጋለጠ ድርጊት ነው። ሰውየው ጋዜጠኛ ሳይሆን የአንድ ወገን አመለካካት አራማጅ ነው። እርግጥ ቀጥሮ የሚያሰራው የአሜሪካ መንግስትም የተለያዩ አመለካከቶችን የማስተናገድ ፍላጎት የሌለው፣ በዴሞክራሲ ስም የዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ውጤት የቀለም አብዮት በተሰኘ የመንግስት ለውጥ በመቀልበስ አሻንጉሊቶቹን የማስቀመጥ ስትራቴጂ የሚከተል መንግስት ነው። ጋዜጠኛውም ይህን የቀለም አብዮት ለማሳካት የሚሰራ ጉዳይ አስፈፃሚ ነው። በአጠቃላይ ጋዜጠኛውም፣ ቀጥሮ የሚያሰራውም መንግስት በዴሞክራሲ ስም ዴሞክራሲን ለማጨለም የሚራወጡ “ዴሞክራሲያውያን” ናቸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy