Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የገዘፈው ግድብ !!

0 360

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

            የገዘፈው ግድብ !!

                                        ይነበብ ይግለጡ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በታላቅ ሀገራዊ ፍቅር ሥራው ቀን ከለሊት ቀጥሏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ግዙፍና አይነተኛ ለውጥ የሚያስገኝ ብዎቹን ብሔራዊ ሕልሞቻችንን ለማሳካት ታላቅ አቅም የሚፈጥር ነው። የሀገራችንን የውሀ ማማነት ከቃላት ባለፈ ሕይወት ባለውና በሚታይ ደረጃ ለአፍሪካም ለአለምም በተጨባጭ ያረጋግጣል፡፡ ከመላው አፍሪካ  ግዙፉና ቀዳሚው በአለም ደግሞ በትልቅነቱ በሰባተኛ ደረጃ የሚገኝ ነው የሚሆነው፡፡ የግድቡ ግንባታ ያለማንም የውጭ እርዳታና ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ገንዘብ ተጀምሮ አሁን ያለበት የ60 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱ በራሱ ታላቅ ብሔራዊ ኩራትን የሚያስጨብጥ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በአባይ ወንዝ ውሀ ተጠቅማ የታላቁን ሕዳሴ የሚያህል ግዙፍና ታላቅ ግድብ ትገነባለች ብሎ ያሰበም የገመተም አልነበረም፡፡ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ከጥንት ጀምሮ በነበረው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ውስጥ የነበሩትን ሕልም ወደተግባር የለወጠና ያሳካ ነው፡፡ ሀገራችን በውጭው አለም የነበራትን የተረጂነትና የተመጽዋችነት ገጽታ ለመቀየር ከድሕነት ጋር በተያዘው ትግል ከፍ ላይ ደረጃ ለመጓዝ የተቻለ ቢሆንም  ገና ብዙ ይቀረናል፡፡

ለዚህም በወሳኝነት የተጀመሩትን ታላላቅ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከዳር ማድረስ የማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን በላቀ ደረጃ ማሳደግ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በአይነትና በመጠን ከተጀመረውም በላይ አስፍቶ መሄድ ይጠበቅብናል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በዚህ ረገድ የገዘፈውን ድርሻ ይወጣል፡፡ ትላንት ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ለመገንባት አትችልም፤ ድሆች ናቸው አቅሙን አያገኙትም የላቸውም ሲሉ የነበሩት ሁሉ አንገታቸውን ለመድፋት የተገደዱበት እንደገናም የራሳቸውን አቅምና አካባቢያዊ ሁኔታ ለመቃኘት እንዲችሉ የተደረገበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡

ግብጾች ከጥንት ጀምሮ በነበራቸው እምነት የአባይን ወንዝ የተቆጣጠረ ግብጽን ተቆጣጠረ ማለት ነው የሚለው አባባላቸው መልሶ ፋታና እረፍት የነሳው ራሳቸውን ነው፡፡ እኛ ሄደን በሰው ሀገር የውስጥ ጉዳይ አልገባንም፡፡ የግዛት መስፋፋት ሕልምና ጥያቄም ያለብን አይደለንም፡፡ በግዛታችንና በራሳችን የተፈጥሮ ሀብት ግን ከማንም ጋር መደራደር አይቻልም፡፡

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ለእኛም ለግብጽም ለሌሎችም የተፋሰሱ ተጋሪ ሀገሮች ተፈጥሮ የሰጠችን የጋራ ስጦታ ስለሆነ በሚገባን መልኩ አንዱ ሌለኛውን ሳይጎዳ ልንጠቀምበት እንችላለን፤ለሁላችንም ይበቃል፤ኢትዮጵያ የጀመረችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ግብጽ ማግኘት የሚገባትን የውሀ መጠን ድርሻ የሚነካ አይደለም፤ እኛ ብቻ እንጠቀም የሚል ስግብግብ አቋም የለንም የሚለውን እምነቷን ትላንትም ዛሬም እየገለጸች ትገኛለች፡፡

ይህ እውነት ባይዋጥላቸውም ወደ ጋራ ድርድርና ውይይት መድረክ መግባታቸውም ለሰላም ያለው ድርሻ ከፍተኘ ነው፡፡ግብጾች የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከጀርባ የሚያካሂዱዋቸው የሴራ ንድፈሀሳቦች እንዳሉ ሁነውም በዲፕሎማሲው መስክ ለአለም እይታ በሚስብ መልኩ ሰላም የደገፉ መስለው ቢታዩም የግብጽ መገናኛ ብዙህን ያልበላቸውን እያከኩ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መገኘታቸው የዚሁ ጉዳይ አብይ ማስረጃ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ታላላቅ ግድቦች የመገንባት አቅም ፈጥራለች፡፡በራስዋ የልማትና የእድገት ጉዳይ  በተፈጥሮ ሀብቶችዋ መወሰን የምትችለው ኢትዮጵያ እንጂ ግብጽ አይደለችም፡፡ይልቁንም የሚሻላቸው በመግባባት አለ ለሚሉት ችግሮች መፍትሄ መፈለግ መቻል ነው፡፡በቅኝ ግዛት ዘመናቸው እብደትና ቅዠት የሰከሩት ግብጾች በአባይ ወንዝ ውሀ ላይ ታሪካዊ መብት የእኛ ነው ብለው ሙግት ሊፈጥሩ መሞከራቸውም አስገራሚ ነው፡፡ታሪካዊ የባለቤትነት መብት ያላት ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡የአባይ ወንዝ ድንበር ዘለልና ተሻጋሪ በመሆኑ አልፎም እነሱን አጥግቦና አብልቶ በማደሩ ሊያመሰግኑን ይገባዋል እንጂ በጠላትነት ሰሜት ተነስተው ሊዘምቱበን አይገባቸውም ነበር፡፡

የግብጽ ሚዲያዎች እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም እየጮሁ ይገኛሉ፡፡መጮህ መብታቸው ነው፡፡ሕዝቡን በተሳሳተ መረጃ እየቀሰቀሱት ይገኛሉ፡፡የዚህ መጨረሻው የተካረረ ውዝግብ መፍጠር ብቻ ነው፡፡ወደዱም ጠሉም የአባይ ወንዝ ምንጭ ኢትዮጵያ ነች፡፡ባለቤትነቱም የእኛ ነው፡፡የሚነሳው ከኢትዮጵያ ነው፡፡የሚፈሰውም ከኢትዮጵያ ማሕጸን በመነሳት ነው፡፡አባይ ወንዝ የሚመነጨው ከካይሮና አሌክሳንደሪያ አይደለም፡፡

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠል በመደናገጣቸውም የተነሳ የተለመደውን ጥንትም ሲያደርጉት የነበረውን የጀርባ ሴራቸውን ቀጥለዋል፡፡ኢትዮጵያን ዙሪያዋን የመክበብ ያህል በአጎራባች ሀገራት እየገቡ የግብጾችን ጦር ሰፈሮች ለማቋቋም እየሰሩ መሆኑን ይታወቃል፡፡ከዚህ ጀርባም የተለያዩ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን በሶማሊያና በየመን በኤርትራ በሱዳን በኩል ጭምር እያደራጁ የጦር መሳሪያ እያስታጠቁ እንደሚልኩና በተደጋጋሚ ያደረጉት ስምሪት እንደከሸፈባቸው እነሱም ያውቃሉ፡፡

ዛሬም ነገም እንደማይተኙም እናውቃለን፡፡ሀገሩን በመጠበቅ ረገድ ተኝቶ የሞያደር ማንም የለም፡፡ ይህም ሁኖ በቅኝ ግዛት ተገዝተን የማናውቅ ለቅኝ ገዢዎችም ያልተንበረከክን እንደሆንን አፍሪካና አለምም ያውቃል፡፡ግብጾች በእንግሊዞች ቅኝ ግዛትነትና ባርነት ሲገዙ ኢትዮጵያ ከራስዋ አልፋ ለአፍሪካ ነጻነት ቀንዲልና ተምሳሌት የሆነች ለአፍሪካ ነጻነት በግንባር ቀደም ቆማ የታገለች የተፋለመች ሀገር ነች፡፡

ግብጾች አፍሪካን አያውቁአትም፡፡አረቦች ነን ባይ ናቸው፡፡ለአፍሪካውያን ያደረጉት ትግልና ተጋድሎ የለም፡፡አሁን ነው ፊታቸውን ወደ አፍሪካ ሀገራ በማዞር ግንኙነታውን ለማጠናከር መስራት የጀመሩት፡፡ድጋፍ ለማግኘት እየሮጡ ያሉት፡፡ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች ነጻነት በመታል ረገድ  በደማቅ የወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ በክብር ያላት ሀገር ናት፡፡ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ባላትን አቅም የደገፈች የቆመች  በአለም አቀፍ መድረኮችም ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ስታሰማ የነበረችና ያለች ሀገር ነች፡፡

ለኢትዮጵያ ምስክርዋ የአፍሪካ ሕዝብ ነው፡፡ምስክሯ ግዜ የማይሽረው ዘመን የማይለውጠው በአፍሪካ ሕዝብ ልብ ውስጥ እንደ ሀውልት ጸንቶ የቆመው ሕያው ታሪኳና ስራዋ ነው፡፡ግብጾች ለአፍሪካ የቆሙበት ለአፍሪካ የታገሉበት ታሪክ የላቸውም፡፡ከዚህ አንጻር እኛ አፍሪካን ነን፡፡አፍሪካም እኛ፡፡

ግብጾች በኢትዮጵያ ላይ ከጀርባ በሚፈጽሙት ተንኮልና ደባ የሚጋጩት መልካም ግንኙነታቸውን የሚያጡት ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ አይደለም፡፡ከአፍሪካ ሀገራትም ጭምር ነው፡፡ይህንን በውል ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡የአፍሪካ አንድነትን ለመመስረት በነበረውም ትግል ውስጥ ግብጾች አልነበሩም፡፡ኢትዮጵያና የቀድሞ መሪዎችዋ ቀዳሚ የሀሳቡ ጠንሳሽና አራማጅ ነበሩ፡፡

አንዱ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ግብጾችን ያስጨነቃቸው ጉዳይ ኢትዮጵያ ተሰሚ ተደማጭና በአካባቢው ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር እየሆነች መምጣትዋ ነው፡፡ቀድሞ ግብጾች የአካባቢው ኃያልና ተጽእኖ ፈጣሪ እኛ ነን የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ዛሬ የአካባቢው የኃይል ሚዛን ከሚጠብቁትም ሆነ ከሚገምቱት ውጪ ሁኔታው ተለውጦአል፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ያስመዘገበችው ከፍተኛ የልማትና እድገት ውጤት ከአሕጉር ደረጃም አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ በአይኤምኤፍና በወርልድ ባንክ እውቅና ያገኝ መሆኑ ፤ሰፊ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብዋ፤በአለም አቀፍ ሰላም የማስከበር ግዳጅ ተመራጭ ሀገር መሆንዋ፤ በዲፕሎማሲው መስክ በአሕጉሩም በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላት ሀገር በመሆን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክርቤት ተለዋጭ አባል ሁና መመረጥዋ ሀገራችን ቀድሞ ከነበራት በላይ በብዙ መስክ ከፍታዋ መጨመሩን ይመሰክራል፡፡ይህ ሁኔታ በተጨባጭ መታየቱ ጭምር ግብጾችን ስጋት ውስጥ አስገብቶአቸዋል፡፡

ለሁሉም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ትርጉም ባለው ደረጃ እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡የግንባታው ሂደት ለአፍታ ሳይቋረጥ ቀጥሎ ዛሬ ያለበት 60 በመቶ ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ሀገራት በሀይል ምንጭነት ያገለግላል፡፡የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠርም ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡ለሀገራቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

በቅርቡ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የግድቡን የሲቪል የሐይድሮ እና ኤሌክትሮ መካኒካል የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ከሁለቱ ተቋራጭ ኩባንያዎችና አማካሪ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር በአሁኑ ወቅት ግድቡ በደረሰበትና በቀጣይ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ዋልታ ዘግቦአል፡፡   

የግድቡ የሲቪልና መካኒካል ስራ በበጋ ወቅት እንደነበረው ሁሉ አሁንም በክረምት ወቅት ተጠናክሮ መቀጠሉን ዶክተር ደብረፅዮን ተናግረዋል፡፡የክረምቱን ስራ ልዩ የሚያደርገው የጎርፉን ሁኔታ አስቀድሞ በመገንዘብ በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን፤ሰራተኛውና ተቋራጮቹ  የግድቡን ስራ በታቀደው ደረጃ በማስኬድ በሕዝብና በመንግስት የተጣለባቸውን አደራ በኃላፊነት በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በጥራትና በብቃት እየተከናወነ ደረጃ በደረጃ ፍጥነቱን ጠብቆ  ኃይል ወደ ሚያመነጭበት ምእራፍ በመሸጋገር ላይ ይገኛል፡፡ኃይል ለማመንጨት አልመን እየሰራን እንደመሆናችን መጠን ወደ ቅድመ ኃይል ማመንጨት ለመግባት ስራው በተፋጠነ መልኩ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ደብረፅዮን ገልጸዋል፡፡በመንግስት ደረጃ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር በተገለጸው መሰረት ይህን በተግባር ለማረጋገጥ ስራው እየተከናወነ ውጤቱ በተጨባጭ እየታየ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክርቤት ጽሕፈት ቤት በ2008 እና 2009 ዓመተ ምሕረት ላካሄዳቸው ሁነቶች ሁለንተናዊ ድጋፍ ላበረከቱ ከ460 በላይ  ልዩ ልዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትና ግለሰቦች እውቅና ሰጥቶአል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ  በአዲስ ሒልተን ሆቴል ባዘጋጀው የምስጋና ፕሮግራም ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሕዳሴ ምክርቤቱ የበላይ ጠባቂ አቶ ደመቀ መኮንን  በሕዝብ ከፍተኛ ተሳትፎ እየተገነባ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ መገኘቱ በእጅጉ ያስደስታል ሲሉ መግለጻቸው የስራውን በትጋት መከናወን ገላጭ ነው፡፡በጥሩ ሁኔታና ሂደት ላይ የሚገኘው ይህ ሀገራዊ ፕሮግራም ወደ ሚቀጥለው ስኬት ሲሸጋገር የሚደረገው ሕዛባዊ እገዛና ድጋፍ የማሰባሰብ ተሳትፎው በጠነከረ መልኩ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን የሚለው ሕዛባዊ መፈክር ዛሬም ጫፍ ላይ ለደረሰው ሀገራዊ ፕሮጀክት ስራ መጠናቀቅ በገንዘብም በሜቴርያልም የሚደረገው መዋጮና ድጋፍ በላቀ ሁኔታ መቀጠል አለበት፡፡

ትልቁን ታሪክ የሚሰራው ሕዝባችን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ የገለጹት  ተገቢም ትክክለኛም ነው፡፡ሀገር ባለውለታዎችዋን አትረሳም፡፡አትዘነጋም፡፡ዛሬም ወደፊትም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy