የፀረ-ሙስና ትግሉ የስርዓቱ ባህሪ ማሳያ ነው!
የፀረ-ሙስና ትግሉ የስርዓቱ ባህሪ ማሳያ ነው!
ዳዊት ምትኩ
ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ወቅት “የኢትዮጵያን የዕድገት ግስጋሴ አንድ ጋት እንኳን ወደ ኋላ ለመጎተት የሚሞክሩ የአገርና የህዝብ ጠላት ናቸው” በማለት ደጋግመው ይናገሩ እንደነበር አስታውሳለሁ። እኚህ ባለ ራዕይ መሪ በየጊዜው ይህን ሃቅ ሳያሰልሱ ይናገሩ የነበሩት ያለ ምክንያት አልነበረም። የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ምን ያህል የአገርን እንዲሁም የህዝብን ተጠቃሚነት በመሸርሸር የህልውና አደጋ ሊሆን እንደሚችል ለማመላከት አስበው እንደነበር ግልፅ ነው። እናም ሙሰኞችን ለመቆጣጠር የስነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን በማቋቋም እስከ ህለፈተ ህይወታቸው ድረስ ተግባሩንና አስተሳሰቡን ታግለው አታግለዋል።
በአሁኑ ወቅትም መንግስት በፀረ ሙስና ትግሉ እያራመደ ያለው ቁርጠኛ ይዟል። በተለይም ስልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ ነው። ይህም በአገራችን የህግ የበላይነት በአስተማማኝ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንና የስርዓቱም ባህሪ ማሳያ ሆኗል ማለት ይቻላል።
እርግጥም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የሀገራችንን ነፃ ገበያ ሥርዓት እየተፈታተነው ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡን ለማራመድ የተዘረጉት እጆች ሊሰበሰቡ ባለመቻላቸው፤ አደጋው ምጣኔ ሐብታችን አሁን ካለው ፍጥነት በተሻለ ሁኔታ እንዳያድግ ብሎም ለፀረ- ዴሞክራሲያዊነት በር የሚከፍት ሁኔታን ሲፈጥር መቆየቱ የሚዘነጋ አይደለም።
ታዲያ ይህን አደገኛ ሁኔታን በአንክሮ የሚከታተለው መንግስት ድርጊቱ የስርዓቱ አደጋ መሆኑን ከላይ በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት መልኩ ደግሞ ደጋግሞ ሲገልፅ እንደነበርም እናስታውሳለን።
ይህን አገራዊ አደጋ ከመግለፅ ባለፈ በተለይም በ1993 ዓ.ም በተካሄደው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ወቅት የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ አንዱ በሆነው ሙስና ላይ የመጀመሪያውን ተግባራዊ ክንዋኔ በወቅቱ በነበሩት ባለስልጣናቱ ላይ ገቢራዊ ማድረጉ ይታወቃል። ይህም በየትኛውም ደረጃ የተቀመጠ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ስልጣኑን መከታ በማድረግ ከህግ ተጠያቂነት ሊያመልጥ የማይችል መሆኑን በግልፅ ያመላከተ ጉዳይ ነው። ይህ ቁርጠኝነትም ዛሬ ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
እንደሚታወቀው ሁሉ የሙስና ተግባር የተወሳሰበና ጊዜን የሚጠይቅ ቀጣይ ትግል በመሆኑ ሳቢያ መንግስት በየጊዜው ከህዝቡ የሚቀርቡለትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ቃል ሲገባ ቆይቷል።
እናም ይህ እርምጃው ለህዝቡ የሰጠው ምላሽ አካል ይመስለኛል። ሆኖም መንግስት በራሱ ተጠርጣሪ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ሳይቀር የወሰደውን ይህን የተቀደሰ የፀረ-ሙስና ትግል፤ አንዳንድ ወገኖች ‘ዋነኛዎቹ አልተያዙም’ በማለት ትግሉን ለማጠሸት እየሞከሩ ነው። ይህ እሳቤ እጅግ የተሳሳተ ነው።
በአገራችን ውስጥ የተመሰረተው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ ቀጥሎ መላውን ህዝብ በየደረጃው በሁሉም መስኮች ተጠቃሚ ማድረግ ይችል ዘንድ፣ የስርዓቱ እንዲሁም የህዝብና የሀገር ጠላት የሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ከመሰረቱ መናድ ይኖርበታል። ኪራይ ሰብሳቢነት የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም ከባለ ስልጣኖች ጋር ተሳስሮ በገበያ ውድድር ሊገኝ ከማይችለው በላይና ውጪ ትርፍ የሚገኝበት የስራ መስክ ነው፡፡
እርግጥ አንዳንድ ግለሰቦች ኪራይ ሰብሳቢነትን ከዘረፋ ጋር በቀጥታ ያገናኙታል፡፡ ለነገሩ ዘረፋን ከኪራይ ሰብሳቢት ለይቶ መመልከት አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አንድ ግለሰብ ሊኖረው የሚችለው የመዝረፍ ዕድል ሌላውም በእኩልነት ሊያገኘው አይችልም፡፡ በመሆኑም በዚህ የሀገርን ኢኮኖሚ የኋሊት ሊጎትት የሚችል የዘረፋ ዓለም የጥሎ ማለፍ ውድድር ነው ማለት ቻላል፡፡
የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ – ኢኮኖሚ በሌለበት ነፃ የገበያ ሥርዓት፤ እያንዳንዱ ሰው በልማት ውጤቱ መጠን ሀብት የሚያፈራበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ሀብት፣ ጉልበትና ዕውቀት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በልማቱ ላይ እነዚህን አቅሞቻቸውን በላቀ ሁኔታ በተጠቀሙበት መጠን ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡ አይቀሬ ነው፡፡ ሁሉም ሰው በልማቱ ላይ ባዋለው ዕውቀት፣ ጉልበትና ሀብት መጠን እኩል ሀብት የማፍራት ዕድል ይኖረዋል። እርግጥ በዕድሉ በላቀ ደረጃ የተጠቀመ ሰው የተሻለ ገቢ ማግኘቱ አይቀርም። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ከነጻ ገበያ ሥርዓት አንጻር ሲመዘንም፤ ፍትሃዊነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ፀረ – ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ግን በመርሆዎች ላይ በመስማማት ሊሰራ ስለማይችል፤ ያለው አማራጭ የመጠቃቀም ሰንሰለቶችን ከላይ እስከ ታች ድረስ በመፍጠርና ደጋፊን በማብዛት ዝርፊያውን ማጧጧፍ ነው፤ ምንም እንኳን ጠብ የሚል ነገር ለማያገኘውና ታች ላለው አብዛኛው ህዝብ ነገሩ ምንም የማያስገኝለት ቢሆንም፡፡
ከዚህ ነባራዊ ዕውነታ በመነሳት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ- ኢኮኖሚ የበላይነት በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲን ማሰብ፣ በምድረ -በዳ ላይ እህል ዘርቶ የተለየ ውጤት የመጠበቅ ያህል መሆኑን የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘብልኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲን ለማቋቋም ቢታሰብ እንኳን፣ ዴሞክራሲው ፍሬ የሚያፈራ፣ ዘላቂነት የሌለው እንዲሁም በዴሞክራሲ ሽፋን በተለያዩ የመጠቃቀም ትስስሮች መካከል የሚካሄድ የኪራይ ሰብሳቢዎች ፍልሚያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው፡፡ ስለሆነም በሀገራችን ውስጥ ዴሞክራሲን በተሟላ ሁኔታ ለማስፈን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን ማምከን ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡
የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ሀገራችን እንደ ህልውና ጉዳይ የያዘችውን ከድህነት የመውጣት ራዕይዋን የሚያሰናክል አሜኬላ እሾህ ከመሆን በዘለለ፤ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን ላይ የሚፈጥረው አደጋ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ትገነዘባለች።
መንግሰት ከዚህ ሀገራዊ የህልውና ጉዳይ አንድምታ በመነሳት ኪራይ ሰብሳቢነትን በአጠቃላይ፣ ሙስናን ደግሞ በዋነኛነት በመዋቅሩ ውስጥ የሚገኙት የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎቶች ሁለንተናዊ ሁኔታን ተላብሰው ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የህዝብ አገልጋይነት እንዲሰፍን በመታገል የሰሞኑን ዓይነት እርምጃ የወሰደውና ወደፊትም ለመውሰድ ቁርጠኝነቱን እየለፀ ያለው ለዚህ ይመስለኛል።
እዚህ ላይ “መንግስት እስካሁን ድረስ ምን ይሰራ ነበር?” የሚሉ አንዳንድ ፅንፈኛ ሃይሎችን የተሳሰተ እሳቤ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ተገቢም ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነት የሀገራችንና የስርዓቱ አደጋ መሆኑን በማሻማ ሁኔታ ፈርጆ በግልፅ ይፋ ካደረገ ወዲህ፤ ይህን አስከፊ ችግር ከምንጩ ለማድረቅ በርካታ ተግባራትን ከውኗል። ጥላሸት ቀቢዎቹ እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ነበር ዓይነት የቁራ ጩኸት ለማሰማት ቢሞክሩም ሃቁ ግን ይህ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ፣ በዘላቂ ዕድገታችን እንዲሁም በህዝቦች ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያሳርፈውን አደገኛ ጠባሳ እንደሚያሳስበው በማውገዝ ብርቱ ትግል ሲያካሂድ መቆየቱ ከማናችንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። ይህ የሆነበትም ምክንያት የፀረ-ሙድና እና የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የስርዓቱ ባህሪ ስለሆነ ነው።
የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብ የማያስተናግድ ባህሪ ያለው ነው። እናም የተጀመረው የህዳሴና የዕድገት እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ በልማቱ ላይ በሚሳተፈው መጠን ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ መንግስት በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል። እነዚህ እርምጃዎችም ወደፊትም ተጠናክረው መቀጠላቸው አይቀርም።