NEWS

የፍትህና የጸጥታ አካላት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሊሰሩ ይገባል – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

By Admin

August 13, 2017

ህዝብ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን የፍትህና የጸጥታ አካሉ ድርሻ ከፍተኛ መሆን እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ።

አቶ ገዱ ይህን ያሉት ዛሬ በጎንደር ከተማ ከክልሉ የፍትህ እና ጸጥታ አካላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በየደረጃው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍትህ ስርዓቱ ጋር ተይይዞ በርካታ ጥያቄዎችን እንደሚያነሱ ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም የፍትህ መጓተት፣ የሀሰተኛ ምስክርና ፍትሀዊ ያልሆኑ ዳኝነቶችን በመቅረፍ ተዓማኒነት ያለው የፍትህ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ ፍርዱ ቸሩ በበኩላቸው የውይይት መድረኩ የህግ የበላይነትን ለማስፈን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ፥ በፍትህና በጸጥታ አካሉ ከአሁን በፊት የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍና የተሻሉ አፈጻጸሞችን ለማስቀጠል አላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ ለአምስት ቀናት እንደሚቆይ የጎንደር ፋና ኤፍ ኤም ባልደረባችን ሀይሉ ማሞ ዘግቧል።