Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የት ደረሰ?

0 341

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የት ደረሰ?

ብ. ነጋሽ

ኢህአዴግ ህጋዊ ሆነው በሃገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳለው በይፋ ያሳወቀው በ2002 ምርጫ ማግስት ነበር። ኢህአዴግ በ2002 ምርጫ ለሁሉም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በተወዳደረባቸው አራት ክልሎች (ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልለች) እና አዲስ አበባ፣ እንዲሁም ለአንድ አንድ መቀመጫ በተወዳደረባቸው ሃራሪ ክልልና ድሬደዋ ከተማ ከሁለት መቀመጫዎች በስተቀር ሁሉንም አሸንፎ እንደነበረ ይታወሳል። በአዲስ አበባ 1 መቀመጫ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲ አንድነት መድረክ፣ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል 1 መቀመጫ የግል ተወዳዳሪ አሸንፈው እንደነበረ ይታወሳል። በዚህም ከ547ቱ የፌደራል የህዝብ ተወካዮች የምክር ቤት መቀመጫዎች 499 ያህሉን አሸንፎ ነበር። የተቀሩትን ክልሎች ማለትም አፋር፣ ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ እንዲሁም ሃራሪና ድሬደዋ በከፊል ኢህአዴግ አልተወዳደረም ነበር። የእነዚህን ክልሎች መቀመጫዎች የየክልሎቹ ገዢ ፓርቲዎች ነበር ያሸነፉት። በዚሀ ምርጫ ኢህአዴግ ከአጠቃላይ መራጭ ህዝብ 85 በመቶ ገደማ ድምጽ አግኝቶ ነበር።

ታዲያ ኢህአዴግ በዚህ ምርጫ አሸንፎ ስልጣን እንደሚረከብ ሲያረጋግጥ፣ የወቅቱ ሊቀመነበሩ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በመስቀል አደባባይ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር፣ ድምጽ ያልሰጣቸው ህዝብ መኖሩን አስታውሰው፣ ይህ ድምጹን ያልሰጣቸው ህዝብም እንዲደመጥ በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።

ይህን መነሻ በማድረግ የምርጫ ስነምግባር ደንቡን ለማዘጋጀት ወራት የፈጀ ድርድር አካሂደው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መስርተው ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተሞክሯል። ይህ ሁኔታ ኢህአዴግ በተወዳደረባቸው ክልሎች ሁሉንም መቀመጫዎች በአብላጫ ድምጽ ካሸነፈበት የ2007 ምርጫ በኋላም ቀጥሏል።

መጋቢት 14፣ 2008 ዓ/ም የኢህአዴግ ሊቀመነበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይተው ነበር። በዚህ ወቅት የምክር ቤቱ አባላት የፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልና ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር የህግ ማሻሻያ ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ህጎችን ማሻሻል የራሱ ሂደት አለው፣ በጋራ ምክር ቤቱ አጥንተን ተወያይተን በመስማማት እንዲሆን ከወዲሁ እንቅስቃሴ እንጀምራለን ብለው ነበር።

ይህ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየትና በመደራደር ፓርቲዎቹ በፓርላማ ውክልና እንዲኖራቸው የማድረግ ፍላጎት ያለው መሆኑን ያሳያል። የ2009 የስራ ዘመን ሲጀመር የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የዓመቱን የመንግስት የስራ ክንውን እቅድ የሚገልጽ የመክፈቻ ንግግር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በዚህ መሰረት ኢህአዴግ ጥር፣ 2009 ዓ/ም በሃገር አቀፍ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይድርድር ጥሪ አቀረበ። በዚህ ጥሪ መሰረት 22 ገደማ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተው ነበር። ይሁን እንጂ በድርድር ከሚገኘው ፖለቲካዊ ፋይዳ ይልቅ፣ የሆነ ያልሆነ ሰበብ አቅርቦ ድርድሩን ጥሎ መውጣት ትኩረት ያስገኛል ብለው ያሰቡ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከድርድሩ ውጭ አድርገዋል። ድርድሩ ግን ቀጥሏል፤ ኢህአዴግን ጨምሮ በ17 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል።

ፓርቲዎቹ አስራ ሁለት የመደራደሪያ አጀንዳዎች ላይ ተስማምተዋል። ከያዟቸው አስራሁለት አጀንዳዎች መሃከል በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ ድርድር አካሂደው ነሃሴ 6፣ 2009 ዓ/ም አጠናቅቀዋል። ከመስከረም 2010 ዓ/ም በኋላ የተቀሩት አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል። በአጠቃላይ በአስራሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ለመደራደር 90 ቀናት ያህል እንደሚፈጅባቸው ገምተዋል።

ያም ሆነ ይህ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመጀመሪያው አጀንዳው – የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ ተደራድረው በአብዛኛው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህ እስካሁን በነበረው የድርድር ሂደት እመርታዊ ሊባል የሚችል ነው። በመሆኑም በዚህ ጽሁፍ የድርድር አጀንዳዎችንና በመጀመሪያው የድርድር አጀንዳ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች መለስ ብለን እንመልከት።

የምርጫ ህጎችና ተያያዥ ጉዳዮች በድርድር አጀንዳነት ከተያዙት መሃከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። እነዚህም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2000፣ የተሻሻለው የምርጫ ህግ 532/1999 እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነምግባር አዋጅ 662/2002 ናቸው። ሌሎች አዋጆችና ተያያዥ ህጎችም በድርድር አጀንዳነት ተይዘዋል። የፀረ ሽብርተኝነት ህግ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ህግ፣ የበጎ አድራጎትና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ፣ የታክስ አዋጅ፣ የመሬት ሊዝ አዋጅ በዋና የድርድር አጀንዳነት የተያዙ ናቸው። የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታ በንኡስ የድርድር አጀንዳነት ተይዟል።

ከዚህ በተጨማሪም የዴሞክራሲና ሰብዓዊ ተቋማት አደረጃጃት፣ የዜጎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመስራት መብት፣ የክልል መንግስታት ህጎች፣ ወቅታዊና ኢኮኖሚ ወለድ የህዝብ ጥያቄዎች፣ ብሄራዊ መግባባት፣ የፍትህ ተቋማት አደረጃጀትና የአፈጻጸም አዋጆችም በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር ከተያዙ አጀንዳዎች መሃከል ይገኙበታል።

እነዚህን አጀንዳዎች መነሻ በማደረግ ከሃምሌ 25፣ 2009 ዓ/ም ጀምሮ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ አንቀጽ በአንቀጽ ተደራድረዋል። በዚህ ድርድር በርካታ የአዋጁ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ተጨማሪ ጉዳዮችም እንዲካተቱ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

በድርድሩ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት በሚያስፈልጉት የመስራች አባላት ቁጥር ፣ የሰነድ አያያዝና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ስለማቋቋምና በመንግስት ሊደረግ የሚገባው የፋይናንስ ድጋፍን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል። ሃገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲ ለመመስረት መሟላት ያለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ፣ ፓርቲዎቹ፣ በምዝገባ አዋጁ አንቀጽ 5፣ ሃገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት 1 ሺህ 500 መስራች አባላት ያስፈልጋሉ የሚለው ድንጋጌ እንዲሻሻል ተሰማምተዋል። ተደራዳሪዎቹ አዲስ የሚቋቋም ሃገራዊ ፓርቲ መስራች አባላት ቁጥር 2 ሺህ 500፣ 3 ሺህ፣ 5 ሺህ ሊሆን ይገባል የሚሉ አማራጭ ሃሳቦች አቅርበው ድርድር አካሂደዋል። በተመሳሳይ በአዋጁ አንቀፅ 6 የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት 750 መስራች አባላት ያስፈልጋል በሚል የተደነገገውን እንዲሻሻል ተስማምተዋል።

በዚህም፤ ሃገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት 3 ሺህ ፣ የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ 1 ሺህ 500 መስራች አባላት ያስፈልጋሉ በሚል አንቀፆቹ እንዲሻሻሉ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም ይዘው መግባባት ላይ ተደርሷል።

በአዋጁ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የፖለቲካ ስራውን ለማካሄድ በሃገር ውስጥ በየትኛውም ቦታ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ሊያቋቁም ይችላል የሚለውን አንቀጽ 17 እንዲሻሻል መግባባት ላይ ደርሰዋል። በዚሁ መሰረት በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋም የፖለቲካ ፓርቲ፣ ዋና ፅህፈት ቤቱን ጨምሮ በፌዴራል ደረጃ ሁለት፣ ቢያንስ በአራት ክልሎች አንድ አንድ ጽህፈት ቤት፣  በድምሩ 6 ጽህፈት ቤቶች ሊኖሩት ይገባል  በሚል እንዲሻሻል ሃሳብ ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቷል። ክልላዊ ፓርቲዎችም በክልሎች በሚገኙ 10 በመቶ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲኖራቸው የሚል አዲስ አንቀጽ እንዲጨመር መግባባት ላይ ደርሰዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጁ፣  በማንኛውም የፓርቲዎች ውስጣዊ እንቅስቃሴ የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብር መከታተል የሚያስችሉ አንቀጾች እንዲካተቱበት በሚል ሃሰብም  ላይ ተስማምተዋል። ከዚህ በተጨማሪ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ከማካሄዳቸው 30 ቀናት አስቀድመው ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቅ እንደሚኖርባቸው የሚያዝ አንቀጽ እንዲካተትም ከስምምነት ላይ ተደርሷል። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ በሚያዘጋጅበት ጊዜ የአባላት ብዛት፣ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሄድበትን አማካይ ጊዜ በግልጽ መያዝ እንደሚገባው የሚያመለክት አዲስ አንቀጽ እንዲካተትም መግባባት ላይ ተደርሷል።

ፓርቲዎቹ ለቢሮ አገልግሎት የሚሆን ቤት ለመከራየት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ማደናቀፍ የተከለከለ መሆኑን የሚደነግግ አንቀጽ እንዲጨመር  ተግባብተዋል። ፓርቲዎች ጽህፈት ቤት እንዳይኖራቸው የሚያደናቅፉ አካላት በህግ የሚጠይቁበት አንቀፅ እንዲካተትም ተስማምተዋል።

ፓርቲዎቹ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ ባካሄዱት የመጨረሻ ቀን ድርድራቸው፣ መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ የሚውል ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችለው አዲስ ንኡስ ንቀጽ እንዲካተት ተስማምተዋል። 

በዚህ መሰረት ከአባላት መዋጮ፣ ከዜጎች፣ ከሃገር በቀል ኩባንያዎች የሚሰጥ ድጋፍና ፓርቲዎቹ በሚያካሄዱት ባዛር ከሚገኝ ገቢ በተጨማሪ፣ በአዋጁ አንቀጽ 45 ንኡስ አንቀጽ 2 ስር ተጨማሪ ሃሳብ እንዲካተት ተስማምተዋል። በዚህ ንኡስ አንቀጽ ስር እንዲጨመሩ በተስማሙባቸው ‘ሐ’ እና ‘መ’ የፊደል ተራ ድንጋጌዎች መሰረት፣ መንግስት የሚሰጠውን የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ ድጋፍ ለማግኘት ተስማምተዋል።

ፓርቲዎቹ መንግስት የሚመድበው የፋይናንስ ድጋፍ  በምርጫ በሚያገኙት ድምፅ፣ በሚያስመዘግቡት እጩ ብዛትና በፌዴራልም ሆነ በክልል ምክር ቤት ባላቸው የመቀመጫ ብዛት መሰረት እንዲደለደል ተስማምተዋል። የሚሰጠው ድጋፍ የሚከፋፈልበት ሁኔታና ጊዜ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎቹ ጋር ተመካክሮ በሚያወጣው መመሪያ እንዲወሰን የሚደነግግ ንዑስ አንቀፅ እንዲካተትም ተስማምተዋል።

በአጠቃላይ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት ድርድር የእስካሁን ሂደት በሃገሪቱ የዴሞክራሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። በሌሎቹም አጀንዳዎች ላይ የሚካሄዱት ድርድሮች እንደመጀመሪያው ሁሉ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችል ከወዲሁ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy