አዲሱ የ1ኛ ደረጃ ትምህረት ቤት የአፋን ኦሮሞ ማስተማሪያ መጽሃፍ ጥቅም ላይ እንዳይውል መከልከሉን የክልሉ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
አዲሱ የማስተማሪያ መጽሃፍ ላይ በተደረገ ጥናት ችግር እንዳለበት በመለየቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል መከልከሉን የቢሮው ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል።
ምሁራን በመጽሃፉ ላይ ባደረጉት ጥናት መጽሃፊ ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ተለይቷል ያሉት አቶ አዲሱ፥ የክልሉ መንግስት ካቢኔም የጥናቱን ውጤት ሙሉ በሙሉ በመቀበል አዲሱ የአፋን ኦሮሞ ማስተማሪያ መጽሃፍ ጥቅም ላይ እንዳይውል አግዷል ብለዋል።
በ1ኛ ደረጃ ትምህረት ቤት ከሶስት ዓመት በፊት በስራ ላይ የነበረውን መጽሃፍ ወደ ስራ በመመለስ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሳይስተጓጎል እንደሚቀጥልም ሃላፊው ተናግረዋል።
አዲሱ መጽሃፍ የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የአፋን ኦሮሞ “ቁቤን” (LAGIM…) ከሚል ጀምሮ እንዲማሩ የሚያደርግ ነበር።
ይህ መጽሃፍ ጥቅም ላይ እንዳይውል መደረጉን ተከትሎም የ1ኛ ደረጃ ተማሪዎች የአፋን ኦሮሞ ቁቤን ከዚህ በፊት እንደነበረው (ABCD…) ከሚለው በመጀመር እንዲማሩ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።
በሙለታ መንገሻ