NEWS

የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ

By Admin

August 05, 2017

የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ማድረጉን የአገር ዓቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ገለፀ፡፡

የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ደግሞ በመጪው ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም ይፋ እንደሚያደርግ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚያብሔር ለኢዜአ እንዳስታወቁት ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ የተማሪዎች ውጤት ፋይ ሆኗል፡፡

በዚሁ መሰረት ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት 285 ሺህ 628 ተማሪዎች መካከል 117 ሺህ 869 ያህሉ ከ350 በላይ አምጥተዋል፡፡

በተጨማሪም 47ተማሪዎች 600 እና ከዛ በላይ ውጤት ያመጡ ሲሆን ይህ ቁጥር ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ በላይ ጨምሯል፡፡

ውጤቱ በዛሬው እለት ከ8 ሰዓት ጀምሮ ይፋ የተደረገ ሲሆን፥ ተፈታኞችም ውጤታቸውን ከኤጀንሲው ድረ ገፅና በአጭር የፅሁፍ መልክት ማየት ይችላሉ ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ተፈታኞች ውጤታቸውን በድረ ገፅ  ላይ በመግባትና የመፈተኛ ቁጥራቸውን በማስገባት ማግኘት እንደሚችሉ ኤጀንሲው አስታውቋል።

በተጨማሪም በነጻ አጭር የፅሁፍ መልዕክት ቁጥር 8181 ላይ የተፈታኞች መለያ ቁጥርን በማስገባት ውጤታቸውን ማየት እንደሚችሉም አመልክተዋል።

ፈተናውን ከወሰዱት መካከል 178 ሺህ ያህሉ የተፈጥሮ ሳይንስ 107 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ሲሆኑ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው።

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ውጤት የትምህርት ሚኒስቴር በሚያስቀምጠው መሰረት በቀጣይ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡